ትግሉ የኛ ድሉም የኛ ነዉ

የአገራቸዉ የኢትዮጵያ በግፍ መወረርና የህዝባቸዉ በጋዝ መርዝ መጨፍጨፍ እጅግ ያሳሰባቸዉ ቀዳማዊ ኃ/ሥለሤ ጄኔቫ ድረስ ተጉዘዉ ለሊግ ኦፍ ኔሺንስ አቤቱታቸዉን ሲያሰሙ ቀን የማይደርስ መስሏቸዉ የግርማዊነታቸዉን አቤቱታ ካንቋሸሹት አገሮች ዉስጥ እንግሊዝና ፈረንሳይ ዋና ዋናዎቹ እንደነበሩ ታሪክ በሚገባ ዘክሮታል። እነዚህ ሁለት አገሮች አባቶቻችን በጋዝ መርዝ ሲቃጠሉ ማፌዛቸዉ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እራሷን እንዳትከላከል የመሳሪያ ሺያጭ እገዳ ማድረጋቸዉና የኋላ ኋላ ከናዚ ጎን ተሰልፎ እነሱኑ ካስጨነቀ ኃይል ጎን መሰለፋቸዉ ታሪክ በቆሻሻነቱ የሚዘክረዉ ዘግናኝ ታሪክ ነዉ። ምዕራባዉያኑ መንግስታት መሳሪያ ሸጡም አልሸጡ ከ1928 ዓም እስከ 1933 ዓም ድረስ በነበሩት 5 የአርበኝነት አመታት ጀግኖች አባቶቻችን ለነፃነታቸዉ ሲታገሉ እንግሊዝ፤ ፈረንሳይና አሜሪካ ከጣሊያን ወራራ ያድኑናል ብለዉ ከትግላቸዉ የተዘናጉበት አንድም ወቅት አልነበረም። ይልቁንም የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ነፃነት አደራ የወደቀዉ እነሱ ጀርባ ላይ መሆኑን አዉቀዉ የፋሺስት ጣሊያንን የመሳሪያ ጋጋታ ከምንም ሳይቆጥሩ ጣሊያንንና አብሮት የተሰለፈዉን የባንዳ ኃይል አይቀጡ ቅጣት ቀጥተዋል።

የሚገርመዉ ቀዳማዊ ኃ/ሥለሤ ጄኔቫ ሄደዉ አገሬን አትርሷት ብለዉ ልዕለ ኃያላኑን ሲማፀኑ መልሳቸዉ ሽሙጥና ፌዝ የነበረዉ እንግሊዞች የኋላ ኋላ ኢትዮጵያን የረዱት ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት አስበዉ ወይም ሰብአዊነት ተሰምቷቸዉ ሳይሆን ከሂትለር ጎን የተሰለፈችዉንና የአንድ ወቀት አጋራቸዉን ጣሊያንን ለመበቀል ሲሉ ነዉ። ዛሬ 2ኛዉ የአለም ጦርነት በተባበሩት ኃይሎች ድል አድራጊነት ከተፈፀመ ከ64 አመታት በኋላ እንግሊዝ፤ጣሊያን፤ፈረንሳይና ጀርመን ከሌሎች 23 አገሮች ጋር የአዉሮፓን ህብረት ፈጥረዉ ወደ ዉህደት እየተጓዙ ነዉ።ሆኖም ከዚያ እንደ ሳምባ ምች ክፉኛ ካጠናፈራቸዉ የክህደት በሽታ ዛሬም ያገገሙ አይመስልም። የጣሊያን ፋሺስቶች አገራችንን ሲቀራመቱ ከወራሪዉ ኃይል ጎን የቆሙት እነዚህ አገሮች ዛሬም አገራችንን በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ ጥሬ ሃብቷን ከሚቦጠቡጥ የአገር ዉስጥ ቅኝ ገዢ ጎን ቆመዋል። በተለይ እንግሊዝና የአዉሮፓዉ ህብረት በታሪክ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁትን የኢትዮጵያ ህዝብ ተረግጠህም ቢሆን በልተህ አስካደርክ ድረስ መብትህና ነፃነትህ ቀስ ብሎ ይከበርልሃል ማለታቸዉ እነዚህ ኃይሎች የእነሱ ጥቅም አስከተከበረ ድረስ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነፃነት ደንታ እንደሌላቸዉ በግልፅ ያሳያል።

ስለምዕራቡ አለም የፖለቲካ ወላዋይነት ብዙም ግንዛቤ ያልነበራቸዉ አባቶቻቸን በየጫካዉ ገብተዉ ጠላትን ሲታገሉ ምዕራባዉያን ነፃ ያወጡናል የሚል ህልሙም ቅዠቱም አልነበራቸዉም። ዛሬ በመረጃ ዘመን የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ምዕራባዉያንም ሆኑ ሌሎች አገሮች ከኢትዮጵያ ምን እንደሚፈልጉና ኢትዮጵያን ለምን እንደሚፈልጓት ጠንቅቆ ያዉቃል፤ ምዕራባዉያን ከእነሱ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ፍለጎት ጋር እስካልገጠመ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ የፍትህ፤የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ቢመለስ ባይመለስ ጉዳያቸዉ አይደለም። እንዳዉም እንደነሱ አባባል ነፃነት፤ ሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲ እንደ ሰዉ ልጆች መሠረታዊ እሴቶች የሚታዩት አዉሮፓና አሜሪካ ከዚያም ካለፈ በእድገት ወደ ፊት በገፉት ጃፓንና አዉስትራሊያ ዉስጥ ነዉ እንጂ አፍሪካዉያን ሆዳቸዉ አስከሞላ ድረስ አነዚህ መሠረታዊ እሴቶች በሁለተኛና በሦስተኛ ደረጃ የሚታዩ ተራ ነገሮች ናቸዉ። በእርግጥ በምዕራቡ አለም መረገጣችንና መረሳታችን አንገብግቧቸዉ የሚጮሁልን አያሌ ተራማጅ ሀይሎች አሉ፤ ሆኖም የእነዚህ ሀይሎች መልካም አስተሳሰብ የሚያበረታታን እንጂ ትግላችንን የሚተካ መሆን የለበትም።

ዛሬ ለምለሙን የአገራችንን መሬት አርሰዉ የራሳቸዉን ህዘብ የሚቀልቡት ህንድ፤ቻይናና ሳዑዲ ናቸዉ። እነዚህ አገሮች አይናቸዉ ያረፈበትን መሬት ሁሉ በርካሽ ዋጋ የሚቸበችብላቸዉ ሰዉ እስካገኙ ድረስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለአገር ደህንነትና ለብሔራዊ ጥቅም የሚቆረቆር መሪ እንዲኖር አይፈልጉም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምዕራባዉያን ዶላር ባስታቀፉት ቁጥር ለነሱ ጥቅም የወንድሞቻችንን ህይወት የሚገብር መለስ ዜናዊን የመሰለ ግድ የለሽ መሪ ተነስቶ አገር ወዳድ የሆነ መሪ እንዲተካ ቅንጥት ታክል ፍላጎት የላቸዉም። እነዚህ ሁለት ሀቆች ቁልጭ አድርገዉ የሚያሳዩን የዘረኛዉን የመለስ ዜናዊን አምባገነን አገዛዝ አስወግዶ ኢትዮጵያን ከአደጋ የማደን ትግል የሚጀመረዉም የሚጠናቀቀዉም በኛ በኢትዮጵያዉያን ብቻ መሆኑን ነዉ።

በቅርቡ ጎረቤታችን የሆነዉ የኬንያ ህዝብ ህገ መንግስቱ የኬንያን ህዝብ ፍላጎትና የዲሞክራሲ እድገት ደረጃ በጠበቀ መልኩ እንዲሻሻል ግፊት አድርጎ አዎንታዊ መልስ ማግኘቱ የሚታወስ ነዉ። ከዚህ ጥቂት ቀደም ሲል ደግሞ የኬንያ ህዝብ በህብረት ቆሞ አምባገነኖች የቀሙትን ድምፀ ዉሳኔ በሀይል ማስከበሩ የሚዘነጋ አይደለም። ከዚሁ ከአፍሪካ ሳንወጣ የማዳጋስካር ህዝብ የእርሻ መሬቱ ለኮሪያ ነጋዴዎች ሲቸበቸብ አሻፈረኝ ብሎ በመነሳት ሺያጩ እንዲቆም አድርጓል። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የእርሻ መሬቱ ዶላር ይዞ ለመጣ የባዕድ ነጋዴ ሁሉ ሲሸጥ እጁን የፍጥኝ ታስሮ ተመልካች ሆኗል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እሱ የመረጠዉ መሪ ሲታሰር እንጂ ሥልጣን ሲረከብ አይቶ አያዉቅም። የኬንያና የማዳጋስካር ህዝብ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንዲወጣ የታገለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ ለራሱ ነፃነትና ሰብዓዊ መብቶች መከበር ክንዱን አበርትቶ የማይታገልበት ምንም ምክንይት ያለ አይመስለንም።

የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነቱን ከማንም ለምኖ አያዉቅም፤ ነፃነት የፈጣሪ ስጦታ ነዉና ማንም ይሰጠኛል ብሎ ጠብቆም አያዉቅም። ይህ አስተዋይ ህዝብ ነፃነት በግልሰብ ደረጃ የሚደሰትበት እንደማህበረሰብ ደግሞ በጋራ የሚንከባከበዉ ህዝባዊ ንብረት እንደሆነ አበክሮ ይገነዘባል። ዛሬ ድንበራችን ለባዕዳን ገፀ በረከት ሆኖ የቀረበዉ፤የእርሻ መሬታችን ካለፍላጎታችን ለባዕዳን የሚቸበቸበዉ፤አባቶቻችን በክብር ያንቀላፉበት ቦታ በግሬደር የሚታረሰዉና ገዳማቶቻችን መሳሪያ ባነገቱ ሰዎች የሚታመሱበት ዋናዉ ምክንያት እንደ ሰዉ የማይቆጥረን የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ነፃነታችንን በመሳሪያ አፈሙዝ ስለቀማን ብቻ ነዉ። እንግዲህ በእናት አገራችን ዉስጥ እንደ ሰዉ ተቆጥረን በነፃነት ለመኖር ያለን አማራጭ አንድ ብቻ ነዉ፤ እሱም ህዝባዊ ትግል ነዉ።

አገራችን ዉስጥ ያለዉ አገዛዝ ባዕዳን ተዋጋልን ብለዉ ሲጠይቁት ዬት ልዝመትላችሁ ብሎ የሚጠይቅ፤ መሬት ስጠን ሲሉት ደግሞ ምን ያክል ትፈልጋላቸሁ የሚል ተጠያቂነትና ሐላፊነት የጎደለዉ አገዛዝ ነዉ። ይህንን አገዛዝ ከቀድሞዎቹ አምባገነን አገዛዞች ልዩ የሚያደርገዉ ዬኔ ነዉ ብሎ በጎጥ ያደራጀዉ ለህዝብና ለአገር የማይታዘዝ ልዩ ጦር ያለዉ መሆኑ ነዉ። ይህ በጎጥ የተደራጀ ጦር ደግሞ አጥፋ ሲባል ለማጥፋት እየዘመረ የሚሄድ ግደል ሲባል ደግሞ ለምን ልግደል ሳይሆን ስንት ልግደል የሚል እጅግ በጣም ጨካኝ የሆነ ጦር ነዉ። ይህ ጦርና ለዚህ ጦር ትዕዛዝ የሚሰጠዉ ዘረኛዉ መለስ ዜናዊ እስካሉ ድረስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነፃነት፤ዲሞክራሲና እኩልነት የሚባሉ የሰዉ ዘር እሴቶች ሊኖሩ አይችሉም። አገራችን ኢትዮጵያን ይህንን ከመሰለ አሳፋሪ ዘረኛ ስርአት አላቅቆ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን የመገንባት ግዴታ የኛ የኢትዮጵያዉያን በተለይም የዚህ ወጣት ትዉልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነዉ።

ዉሸት መታወቂያ ካርዱ የሆነዉ መለስ ዜናዊ “የኢትዮጵያን ህዝብ ከዲሞክራሲ ጋር አስተዋወቅነዉ” ብሎ ለአለም ህዝብ የተናገረዉ ከጫካ ወጥቶ አዲስ አበባን በረገጠ ማግስት ነበር፤ የሚገርመዉ ዛሬ ከሃያ አመታት በኋላ እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ የመለስ ዜናዊ የቅርብ ደጋፊዎችም ቢሆኑ ዲሞክራሲ ከደደቢት በረሃ እንደ ከላሺንኮቭ በመኪና ተጭኖ እንደማይመጣ በዉል ያወቁት ይመስላል። መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የአንድ ፓርቲ አገር መሆኗን ሊነግረን ለምን 20 አመት እንዳስፈለገዉ ባናዉቅም ዛሬ ከሃያ አመታትና ከአራት አገራዊ ምርጫዎች በኋላ ኢትዮጵያ የአንድ ፓርቲ አገር የመሆኗ ነገር ግን ያለቀለት ጉዳይ ሆኗል። የሚገርመዉ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ በገዢዉ ፓርቲና በፓርላማዉ መካከል ካለዉ ልዩነት በዉኃና በበረዶ መካከል ያለዉ ልዩነት ይበልጣል። ለዚህ ነዉ ዛሬ መለስ ዜናዊና በዉጭዉ አለም ቀጥሮ ያሰማራቸዉ ተላላኪዎቹ ኢትዮዮጵያ የሚያስፈልጋት የኤኮኖሚ እድገት ነዉ እንጂ ነፃነትና ዲሞክራሲማ የተራበ ሰዉ አይቀልቡም እያሉ ለዘረኛዉ አገዛዝ ረጂም እድሜ የሚመኙት።ኢትዮጵያ ዉስጥ እድገት የሚባል ነገር ቢኖር ኖሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዉ ለመግዛት ዕቁብ መግባት አይኖርበትም ነበር፤ እነ መለስ ዜናዊ እድገት እያሉ የሚጮሁብን ጩኸት እዉነት ቢሆን ኖሮ አዲስ አበባ ዉስጥ ተማሪዎች ረሃብ እያጥወለወላቸዉ የሚማሩበት ክፍል ዉስጥ አይወድቁም ነበር። በ10 እና በ 11 በመቶ አደገ የተባለዉ ኤኮኖሚ እዉነትም በዚህ ስሌት አድጎ ቢሆን ኖሮ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ዉስጥ ምግብ በእጅ ጉርሻ እየተለካ አይሸጥም ነበር።

መለስ ዜናዊና የበረሃ ጓደኞቹ የባለስልጣን ቱጃር ያደረጋቸዉን መጠነ ሰፊ ዶላር በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ካልሆነ በሌላ በማንም ስም እንደማያገኙት ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ፤ ስለዚህ የሚጠሩበት ስም በትክክል እንደሚያመለክተዉ እነሱ የሚወክሉት አንድን አካባቢ ብቻ በመሆኑ ተቀዳሚ አላማቸዉ ኢትዮጵያን እንደ ፈረንጅ ላም እያለቡ የኛ ነዉ የሚሉትን አካባቢ ማልማት ነዉ። እነሱ እደገትና ልማት የሚሉትም ይህንኑ የተወለዱበትን አካባቢ እድገትና ልማት ነዉ።

መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ አዲስ አበባ ሲገቡ ሦስትና አራት አመት ዕድሜ የነበራቸዉ ልጆች ዛሬ ኮሌጅ ጨርሰዉ ወይ አለፍላጎታቸዉ የወያኔ አባል ሆነዋል አለዚያም የኛ አይደላችሁም ተብለዉ በወጣትነታቸዉ እንደ አሮጌ ዕቃ ተጥለዋል። እዚህ ላይ እጅግ የሚያሳዝነን ነገር ቢኖር አማራጭ አጥቶ የወየነዉም ሆነ ጎመን በጤና ብሎ ስራ አጥነቱን የመረጠዉ ኢትዮጵያዊ ወጣት ተስፋ የቆረጠና ፊት ለፊቱ የሚጠብቀዉን የብሩህ ዘመን መምጣት የሚጠራጠር ወጣት ነዉ። እዚህ ላይ ይህ ግፈኛ ስርአትም ሆነ የስርአቱ ደጋፊዎች ሊያዉቁት የሚገባ አንድ ሐቅ አለ። ተስፋ መቁረጥ ሰዎችን ወደበለጠ ተስፋ መቁረጥ የሚገፋፋ አደገኛ በሽታ ነዉ፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉም ነገሩ ተሟጥጦ አልቆ አንድ የቀረዉ ነገር ቢኖር ልጆቼ ከዛሬ ነገ ይደርሱልኛል የሚል ተስፋ ብቻ ነዉ። ይህንን ህዝባዊ ተስፋ በጠመንጃ አፈሙዝ ለማጨለም መሞከርና በእድገት ስም ህዝብን በአዝጋሚ ረሃብ መፍጀት ተነጣጥለዉ የሚታዩ ነገሮች አይደሉም። አንድን ህዝብ ወደ ጦርነትና ወደ እልቂት የሚወስደዉ የሰዎች በረሃብ መሞት ሳይሆን የተስፋ መሞት መሆኑን ታሪክ በብዙ መረጃዎች ያስገነዝበናል።

በዛሬዋ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስራ ለማግኘት፤ ለመሾም፤ለመሸለም፤የንግድ ስራ ፈቃድ ለማግኘትና ዉጭ አገር ሄዶ ለመማር የወያኔ ድርጅቶች አባል መሆን የግድ ነዉ። በእርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ እድሜ ልኩን ከብዝበዛና ከጭቆና ተላቅቆ አያዉቀም፡ ሆኖም እንደ መለስ ዜናዊ አገዛዝ የኢትዮጵያን ህዝብ ክብር የረገጠ፤ህልዉናዉን ያንቋሸሸና ማንነቱን የደፈረ አገዛዝ አገራችን አይታ አታዉቅም። ባህር ተሻግረዉ የመጡ ቅኝ ገዢዎችን አይቀጡ አቀጣጥ የቀጣዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ እጅግ በጣም አናሳ ለሆኑ የአገር ዉስጥ ቅኝ ገዢዎች ሰጥ ለጥ ብሎ የሚገዛበት ምንም ምክንያት የለም።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ አገራችንን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ምን ያክል እንደናቀ በግልፅ ከሚያሳዩን ብዙ ነገሮች አንዱ ሻምበል አበበ ቢቂላን የመሳሰሉ የአገር ክብርና ተምሳሌት የሆኑ ጀግኖች በክብር ያረፉበትን የቅዱስ ዮሴፍ መካነ መቃብር አፈራርሶ የስግብግቦቹ የወያኔ ሹማምንት የገንዘብ መሰብሰቢያ ቦታ ማድረጉ ነዉ። ይህ በቃኝን የማያወቅ ስግብግብነትና ማን አለብኝነት የሚያሳየን መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ገንዘብ እስካስገኘላቸዉ ደረስ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የማይፈጽሙት ምንም አይነት ወንጀል አለመኖሩን ነዉ። ይህ ደሞ በግልጽ የሚታይ አዉነት ነዉና ብዙ ማስረጃ የሚያስፈልገዉ አይመስለንም – በድንበራችን ጉዳይ ከጠላቶቻችን ጋር ተዋዉለዋል፤የአገራችንን ገበሬ መሬት ለባዕዳን ሽጠዋል፤ነፍስ ያለወቁ ህፃናት ልጆቻችንን በጉዲፈቻ ስም እንደ ዕቃ ሽጠዋል። እንደዚህ አይነቱ ቅጥ ያጣ ንቀት “ማን ይነካኛል” ወይም “ምን አባታቸዉ” ይሆናሉ ከሚል እብሪትና ጀብደኝነት የመነጨ ነዉ፤ ስለሆነም ከዚህ አይነቱ ዉርደትና ንቀት አንዱኑ የማይቀረዉ ሞት ይሻላልና የኢትዮጵያ ህዝብ እየሞተም ቢሆን ከዚህ አሳፋሪ የመከራ ኑሮ እራሱን ነፃ ማዉጣት አለበት።

በነፃነቱና በአንድነቱ ኮርቶ የሚኖር ህዝብ ታሪካዊ ማንነት የሚለካዉ የኩራቱ ምልክት የሆኑትን ነፃነትና የአገር አንድነት ለልጅ ልጆቹ ማስተላለፍ በመቻሉ ነዉ።በዛሬዋ ህገ ወጥነትና ዘረኝነት በነገሰባት ኢትዮጵያ የሚኖረዉ ኢትዮጵያአዊ ግን የሚጠበቅበት ይህ ቅዱስ አባታዊ አደራ ሳይሆን እራሱን ከአገር ዉስጥ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ማዉጣትና አገሩን ከተደቀነባት አደጋ ማዳን ነዉ።ደጋግመን እንደ ተናገርነዉ ነፃነት ማንም ቆርሶና ለክቶ ሊሰጠዉ የማይችል የህዝብ ንብረት ነዉ፤ ሆኖም ዛሬ በነፃነታቸዉ ኮርተዉ የሚኖሩ ህዝቦች ነፃነታቸዉን የተጎናፀፉት በመራራ ትግልና በመስዋዕትነት ነዉ እንጂ እጅ በመንሳት ወይም በልመና አይደለም። ዛሬ በወያኔ አፈሙዝ ታጥሮ በገዛ አገሩ በግዞት የሚኖረዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን ከዚህ ወያኔ ከጫነበት መከራ፤ስቃይ፤ ዉርደትና ንቀት እራሱን ነፃ ለማዉጣት ያለዉ ብቸኛ አማራጭ ህዝባዊ ትግል ብቻ ነዉ። በዚህ ለመብታችንና ለነፃነታችን በምናርገዉ የሞት የሽረት ትግል ዉስጥ ዘረኞች አንዳንዶቻችንን ሊያስሩ ሌሎቻችንን ደግሞ ሊገድሉ ይችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን የማያዉቋትን እዉነትን፤ የሚረግጧትን ፍትህንና ከሁሉም በላይ ደግሞ በነፃነት የመኖር ፅኑ ፍለጎታችንን በፍፁም ሊገድሉ አይችሉምና ያለ ጥርጥር እናሸንፋለን።