ነርሶችን የምትገፋም “የምትሸጥም” አገር
ነፍሰ ጡር በቃሬዛ ተሸክሞ አዋላጅ ፍለጋ ብዙ ማይል ማቋረጥ እና መንከራተት ዛሬም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያልተነካ እና ያልተቀረፈ ችግር ነው። የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን በሰፊው እያሰማራሁ ነው የሚለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገና ያልደረሰባቸው እና መፍትሄ ያላገኘላቸው የኤችአይቪ እና የወባ በሽተኞች ቁጥርም ቀላል አይደለም። ባለፉት ዓመታት ከድርቅ ጋራ በተያያዘ ለረኀብ ከተጋለጡት 13 ሚልዮን በላይ ዜጎች ውስጥ ለችጋር በሽታ የተጋለጡትንም መንግሥት የቁጥር መከራከርያ የመጫወቻ ካርድ አድርጓቸው ነበር። ከጤና ጋራ በተያያዘ በየጊዜው ለሚታየው ችግር አንዱ የመፍትሄ አቅጣጫ በቂ የኾነ የጤና ባለሞያ በየክልሉ እና በየገጠር ወረዳዎች እንዲዳረስ ማድረግ ነው። ሰሞኑን የተሰማው ዜና ግን “ሳይተርፋት ታበድር ሳትቀበል ሞተች” የሚባለውን ተረት እውነት የሚያደርግ ይመስላል፤ መንግሥት ነርሶችን እያሠለጠነ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ ላይ ሊሰማራ ነው።
ይህን መረጃ የወጣው በዚህ ሳምንቱ የሪፖርተር ጋዜጣ የእሁድ ዕትም ላይ ነው። አስገራሚው ዜና የኢሕአዴግን የፖሊሲ አቅጣጫ ውድቀት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። እንደ ጋዜጣው ዘገባ መንግሥት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ነርሶች ለውጭ ገበያ በማቅረብ የገቢ ምንጭ የማድረግ ዕቅድ አለው። በመጀመርያው ዙርም 200 ያህል ነርሶችን ለይቶ ለመላክ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጽፏል። ይህ ዐይነቱ ዕቅድ እንደ አገር ሲታይ መጥፎ ተብሎ የሚታሰብ ወይም በራሱ ሐሳቡ ችግር ያለበት አይደለም። ነገር ግን ችግር ኾኖ የሚወጣው ኢኮኖሚያዊም ኾነ ማኅበራዊ ትርፍ ለማምጣት የሚያስችል ደረጃ ላይ የሌለውን የኢትዮጵያን የሕክምና ዘርፍ ለትርፍ ማጨቱ እውነት ሲኾን ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሕክምና የጥራት ደረጃ አጠያያቂ ኹኔታ ውስጥ ባለበት እና በቂ የኾኑ የሕክምና ባለሞያዎችን በአግባቡ ማሰማራት ካልተቻለባት አገር ነርሶችን አሠልጥኖ መላክ የአመራር ችግር መኖሩን ማሳያ ነው።
ለዚህ ወለፈን አንዱ ማሳያ በሕዳር ወር ይፋ የተደረገው የወርልድ ባንክ መረጃ ነው። “Migration and Remittances Factbook 2011” በሚል ርዕስ ሥር የተቀመጠው መረጃ እንዲህ ይነበባል፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሠለጠኑት 26.4 በመቶ የሚኾኑት እና በዚያው በኢትዮጵያ ውስጥ ከተወለዱት 29.7 በመቶ የሚኾኑት ዶክተሮች በስደት ላይ የሚገኙ ሲኾን እውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን ለሌሎች አገራት የሚገብሩ ናቸው። እነዚህን ዶክተሮች ጨምሮ በነርሲንግ የሠለጠኑ ባለሞያዎች ለስደት የተዳረጉት በአነስተኛ ክፍያ፤ በሞያዊ ነጻነት ዕጦት እና በአስተዳደራዊ ብልሹ አሠራር ምክንያት ነው። በየጊዜው ለሚጨምረው የጤና ባለሞያዎች ፍልሰት ይህ ችግር ያለው አሉታዊ አስተዋጽዖ እንደ ቀላል የሚወሰድ አይደለም። አኀዙንም እያሻቀበው ነው።
የብሉይዎቹም (Classical) ኾኑ ወቅታዊ የኾኑት የኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች የዓለም አቀፍ ንግድ ሥርዐትን በተመለከተ የሚያስማማ ኀልዮት አላቸው። አንድ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሸቀጥ አቅራቢው አገር ካለው አንጻራዊ አብላጫ ታይቶ የሚመዘን ነው፡፡ የሸቀጡ በአገር ውስጥ ተትረፍርፎ መገኘት፣ ከሌሎች አጋራት ጋራ ሲነጻጸር አነስተኛ የኾነ የምርት ወጪ ማስከተል መቻሉ፣ በሌሎች የአገር ውስጥ ሀብቶች የሚተካ መኾኑ እና ሸቀጡን በመላክ የሚገኘው ጠቀሜታ ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ኪሳራዎችን ለመሸፈን የሚያስችል መኾኑ ግምት ውስጥ የሚገቡ መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው፡፡
ከእነዚህ መመዘኛዎች አንጻር ኢትዮጵያ ስትፈተሽ ነርስ “ለመሸጥ” የሚያስችል የተግባርም ኾነ የኀልዮት ብቃቱ የላትም፡፡ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ይፋ ባደረገው የ2010 ዓ.ም መረጃ ኢትዮጵያ ያሏት የጤና ባለሞያዎች ቁጥር አገሪቷ ካለባት ከፍተኛ የጤና ችግር ጋራ ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ዶክተር ለ20 ሺሕ ሰዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ግዴታው ሲኾን ለ10 ሺሕ ዜጎች እንዲሁ በተመሳሳይ ሁለት ነርሶች ብቻ ናቸው የተዘጋጁት፡፡ አንድ የአካባቢ እና የማኅበረሰብ ጤና ባለሞያ 10 ሺሕ ዜጎችን እንዲያገለግል ይጠበቅበታል፡፡ ይህም በጤና ባለሞያዎች እና በማኅበረሰቡ ያለውን የአገልግሎት ጥመርታ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት ሳይቀር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል።
ዛሬ የዓለም አቀፍ ሽያጭ ጉዳይ የተነሳባቸው የነርሶችም ስደት ቁጥር ከሌሎች አገራት ጋራ ሲነጻጸር ከፍተኛውን ምጣኔ ይይዛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሠለጠኑት ነርሶች መካከል 16.8 በመቶ የሚኾኑት በስደት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ያፈጠጠው እና ያገጠጠው እውነታ ይህ ኾኖ ሳለ አገሪቷ በባለሞያዎች በቁጥርም በጥራትም ራሷን ሳትችል የባለሞያ ሽያጭ ውስጥ እንድትገባ መታሰቡ መንግሥት አሁንም በጥናት ላይ የተመሠረተ እና ዘላቂ የኾነ መፍትሄ ማምጣት በሚችል ዕቅድ ላይ ከመመሥረት ይልቅ ከ“ድንገቴ” ዕቅድ ምትኀት ሊወጣ አለመቻሉን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ይኹንና ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ኾኖ የሚቀጥል ከኾነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክትባት የሚሰጥም ባለሞያ ማግኘት ሕልም ይኾናል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጤና ችገር ለመፍታት እና የጤና ባለሞያዎችን ፍልሰት ለመቀነስ ፖሊሲ መቅረጽ ያስፈልጋል የሚል ተማጽኖ ሲቀርብ ነበር። ችግሩን ለመቅረፍ ከቀረበው የፖሊሲ አማራጭ ይልቅ መንግሥት ነርሶችን በመላክ የንግዱ አንደኛው ተዋናይ በመኾን ከሐሳቡ በተቃራኒ ቆሟል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖሊሲዎች እና የአሠራር የእርስ በርስ መጣረስ እየበዛ ነው፡፡ ስለ “አምስት ዓመት የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ” መስበክ የጀመረው ኢሕአዴግ አገሪቷን ጥበብ ከተሞላበት እና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ካገናዘበ መፍትሄ እና ዕቅድ ይልቅ በተዐምራት ወደፊት ሊያሠግራት እንደሚችል የሚያሳየው በተቃርኖዎች ውስጥ ኾኖ ነው፡፡
የሥራ አጥ ቁጥሩ ምጣኔ በዓመት በ20 በመቶ እየተመነደገ ኢሕአዴግ የጉልበት ሠራተኞችን ጭምር ከውጭ ለማስመጣት ያቅዳል፤ ከመቶ ዓመታት በፊት የተዘረጋ የባቡር መሥመር ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ያለ አሳቢ እና ያለ አስተዋይ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች እንኳ ሳይጠገን ተዘግቶ፤ በድንገት ከ6000 ኪሎ ሜትር በላይ የሚኾን የባቡር መሥመር ለመዘርጋት አምስት ዓመት ብቻ በቂ ነው የሚል ሐሳብ ይደመጣል። በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት መካከል እናደርሳታለን የሚለው የኢሕአዴግ ዲስኩር ተነግሮ ሳያበቃ በሸቀጦች የዋጋ ውድነት እና በፖለቲካዊ ነጻነት ዕጦት ኑሮውን መቋቋም የከበደውን ማኅበረሰብ ለልማቱ መዋጮ ማድረግ አለብህ በሚል ስብከት ሊያጠምቁት ካድሬዎች ቁጭ ብድግ ይላሉ። ኢሕአዴግ እያለፈባቸው ያሉት ተቃርኖዎች ብዙ ናቸው።
በዚህ ወቅት የጤና ባለሞያዎቹ የጥራት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽቆልቆል እና ከሕዝቡ ቁጥር ሥግረት ጋራ አለመመጣጠን ትልቁ መነጋገርያ በኾነበት ወቅት የሕክምና ባለሞያዎች ሽያጭ ወደ አደባባይ ብቅ ማለቱ ችግሩን ለማቀጣጠል ተጨማሪ ግብዐት ይኾናል፡፡ መንግሥት የጤና ባለሞያዎችን ቁጥር በማብዛት የማኅበረሰቡን ጤና መጠበቅን ዋነኛ ግብ ማድረግ ሲገባው በተቃራኒው እየተጓዘ መኾኑ ብዙዎችን ማስገረሙ አልቀረም፡፡
መንግሥት መድረክ ላይ እንደሚናገረው የባለሞያዎችን ሽያጭ (በቀጣይም የማኅበረሰብ ሳይንስ ተማሪዎችን ለመላክ ዕቅድ እንዳለው ሪፖርተር ጠቅሷል) አንዱ የውጪ ምንዛሬ ማስገኛ መንገድ ሊያደርገው ይመስላል፡፡ በርግጥ አገሪቷ ውስጥ የመሥራትም ኾነ በሰላም የመኖርን ነጻነት ተነፍገው በስደት የሚገኙ ዜጎች ለአገሪቱ የሚያስገኙት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ የሚካድ አይደለም፡፡ በየጊዜው የሚወድቅ የሚነሳውን የውጭ ምንዛሬ ክምችት በመደጎም አስተዋጽኦዋቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ከ40 ሚልዮን ዶላር አልፎ የማያውቀው በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የሚገኘው ገንዘብ በአሁኑ ወቅት 350 ሚልዮን ዶላር ደርሷል፡፡
ይህ ገንዘብ ለአጭር ጊዜ ችገሮች ማስተንፈሻ መጥቀሙ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት ለሚስተዋለው የሠለጠነ ባለሞያ እጥረት እንዲሁም ይኼን ተከትሎ በረዥም ጊዜ ውስጥ ለሚከሰተው የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ጉስቁልና እና ምስቅልቅል ማካካሻ ሊኾን ግን አይችልም፡፡ የዛሬ የባለሞያዎች ዕጦት ነገ በምንም መልኩ ሊመለስ ወደማይችል ችግር መንዳቱ ግልጽ ነው፡፡ እስከዚያው ግን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕሙማንን ለመስዋዕትነት አቅርቦ “ነርስ የመሸጥ ንግድ” ላይ ሊሰማራ ያሰበ መንግሥት አፍርተናል።