ኢትዮጵያዊው ዶክተር ጁባ ውስጥ ተገደሉ

(ሪፖርተር) — በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የአፍሪካ ሕክምናና ምርምር ፋውንዴሽን (አመሬፍ) ዳይሬክተር የነበሩት ኢትዮጵያዊው ዶክተር ዓለማየሁ ሰይፉ ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥር 5 ቀን 2004 ዓ.ም. ተገደሉ፡፡ በጁባ ከተማ ዳርቻ በሆነችው የማላካል አካባቢ በሚገኘው ቤታቸው በር ላይ በታጣቂዎች ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ላይ የተገደሉት የ46 ዓመቱ ዶክተር ዓለማየሁ፣ መኪናቸውንና ሌሎች ንብረቶቻቸውን መዘረፋቸው ታውቋል፡፡

Dr Alemayehu Seifu

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ግድያውን ለማጣራት ምርመራ እያካሄደ ሲሆን፣ የዶክተሩን መኪናም እሑድ ከሰዓት በኋላ ላይ ያምቢዮ ጁባ መንገድ ላይ ተገኝቷል፡፡ ፖሊስም መኪናውን ሲያሽከረክረው የነበረውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው ታውቋል፡፡

የዶክተር ዓለማየሁ አስከሬን ባለፈው እሑድ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ባለፈው ሰኞ ሲኤምሲ መንገድ ላይ በምትገኘው የሳህሊተ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓት ተደርጐላቸዋል፡፡ ዶክተር ዓለማየሁ የ15 ዓመት ወንድ ልጅና የ12 ዓመት ሴት ልጅ አባት ነበሩ፡፡

የአመሬፍ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ትዕግሥት ግርማ በዶክተር ዓለማየሁ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ይህ ለመላው የአመሬፍ ቤተሰብ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ አመሬፍም በዚህ አሳዛኝ ወቅት ከዶክተር ዓለማየሁ ቤተሰብና በደቡብ ሱዳን ከሚገኙ የአመሬፍ ሠራተኞች ጐን ይቆማል፤›› ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፣ ‹‹አመሬፍ ጉዳዩን አስመልክቶ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዶክተር ዓለማየሁ በጁባ የሚገኘው አመሬፍ ዳይሬክተር የሆኑት ባለፈው ዓመት ጥር ወር ሲሆን፣ ከዚያ በፊት እ.ኤ.አ. ከመስከረም 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የአመሬፍ ምክትል ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ዶክተር ዓለማየሁ አመሬፍ ከመግባታቸው በፊት በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት፣ በኬር ኢንተርናሽናልና በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ይሠሩ ነበር፡፡

ዶክተር ዓለማየሁ በሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ ሲኖራቸው፣ በሕዝብ ጤና የማስትሬት ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡

አመሬፍም በዶክተሩ ምትክ የፕሮግራም ማኔጀር የነበሩትን ዶክተር ጆሴፍ ሊፑዋን ዳይሬክተር አድርጐ ሾሟቸዋል፡፡