የፍኖት ጋዜጣ – የአንድነት ፓርቲና የሊቀመንበሩ ተግባር አስደሳች ጅምር ነው – ወ/ሮ አበበች ከበደ በሰማያዊ ፓርቲ ምስረታ ዙሪያ የሰጡት አስተያያተ
ባለፈው ሳምንት ሰማያዊ የተባለ አዲስ ፓርቲ የምሥረታ ጉባኤውን ሲያካሂድ በአብዛኛው አባላት ከአንድነት ፓርቲ ጋር በታክቲክም ሆነ በስትራቴጂ አብረው ሊሠሩ ያልቻሉ፤ ሆኖም ግን ለሃገርም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ አስተዋፅኦ እናደርጋለን ያሉ ኃይሎች ፓርቲ መሠረቱ፡፡ በፓርቲ ምስረታቸውም ዕለት የአንድነት ፓርቲ በእንግድነት እንዲገኝላቸው ጥሪ አደረጉ፡፡ አንድነት ፓርቲ ጥሪያቸውን በማክበር አጀንዳ ይዞ ውይይት ካደረገ በኋላ የፓርቲው ሊቀመንበር የተከበሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንዲገኙ የወሰነ መሆኑን ባለፈው እትም ቁጥር 23 ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡
በመሆኑም ሊቀመንበሩ በቦታው ተገኝተው ያደረጉት ንግግር ከልብ አስደስቶኛል፡፡ መቻቻልና እርቅ ማለት በተግባር ሲተረጉምም ይህነው፡፡ እንደ አንዳንድ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው የዴሞክራሲ አዝማቾች እኛ ብቻ ነን ብለው በመኮፈስ የስም ማጥፋት ዘመቻ አላካሄዱም ዴሞክራሲውን ሲገድሉና ሲገለባበጡ ለቆዩት ህሊና ካላቸው የአንድነት ፓርቲና የሊቀመንበሩ ተግባር ትምህርት ሊሆናቸው ይገባል፡፡ እነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ነን የሚሉት አምባገነኖች ብሔራዊ እርቅ እያሉ ኢህአዴግ ጫማ ሥር ከመደፋት የአባሎቻቸውን ፍቅር ማግኘት ቅድሚያ ቢሰጡ የሚጐዙበት መንገድ መልካም ይሆናል፡፡ የሚጓዙበት የኩርፊያ ፖለቲካ ምን ያህል እንደ ጐዳቸው አካባቢያቸውን ጥላ ቢስ እንዳደረገው ከዓመታት በፊት የነበራቸውን የአበላት ተሳትፎና የእነሱን ክብር ወደኋላ በእዝነ ልቦና ቢያስቡት ምን ያህል እንደሚያሸማቅቃቸውና እንደሚቆጩ ግልጽ ነው፡፡
ችግሩ የቅራኔ አፈታት አለማወቅና በውስጣቸው የሌለ የዴሞክራሲ እሳቤ ጋር በሚያሳዩት አስመሳይ ሩጫ ሕዝቡ ሳያውቅ አይዟችሁ ስለተባሉ
በዚያ ሽፋን የመንግስት ወንበር ለመቆናጠጥ የነበራቸው ህልም ዛሬ እራቁቱን የቀረ ስለሆነ ቁርጣቸውን ያወቁ ይመስለኛል፡፡ የመንግሥትን ወንበር አበጥረው የሚያውቁት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እርቅና ፍቅር መግባባት የሚጀምረው ከታች ከብዙሃኑ ጋር እንጂ ከአቶ መለስ ወይም ከአቶ
በረከት መንግስት እጅ መጨባበጥ ሊመጣ እንደማይችል አሳምረው ያውቃሉ፡፡ እነዚህ ለብዙሃኑ ትግል ውጤት ሳይሆን “ለሥልጣን ጠለፋ” የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም መግለጫና ብሶት ብቻ በመደርደር የትግል ጊዜያችንን እየበሉ መንገዳችንን ከሚጐዱት ሊማሩ ይገባል፡፡ የዴሞክራሲ መብት ለአንድም ለሁሉም ሕገ መንግሥታዊ መብትም እንደዚህ ግለሰባዊና ማህበረሰባዊ መሆኑን ተገንዝበው ማንም የተፈጥሮ ነፃነቱን ጠብቆ መንቀሳቀስ እንደሚችል ሊያውቁ ይገባል፡፡ የእነሱ አስተሳሰብ እንዲከበር እንደሚፈልጉት ሁሉ የሌሎችንም
ማክበር እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ ከምንም በላይ ትክክለኛው መንገድ “እኔ ብቻ ነኝ” ከሚል ጽንፈኝነት አስተሳሰብ ተላቀው የአንድነት ፓርቲና መሪዎች ተግባራዊ ድርጊት አርአያ ሊሆናችሁ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የአንድነት ፓርቲ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ግን ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነትንም ጭምር የሚያሳይ እንቅስቃሴ በመሆኑ ምስጋና ሊወረወርላቸው ይገባል እላለሁ፡፡
የፍኖት ነጻነት ጋዜጣ በተሳምንቱ በአንድነት ለዲሞርካሲና ለፍትህ ፓርቲ የምትታተም ጋዜጣ ናት። ጋዜጣው በብዛት እንዲታተም ፣ በስፋት በየክልሎቹ እንዲሰራጭ እርዳታዎትን የአንድነት ፓርቲ ይጠይቃል።
የፍኖት ጋዜጣ እትም 24ን በሙሉ ለማንበብ ክለዚህ ይጫኑ !