ፍኖት ጋዜጣ – በነ በቀለ ገርባ ላይ ክስ መስማት ተጀመረ፤የእምነት ክህደት ቃላቸውንም ሰጡ
የፌደራሉ አቃቤ ሕግ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር በሆኑት በአቶ በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ ቁጥር 113633 በ9 ሰዎች ላይ 3 ክሶችን መስርቶ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ሰኞ ታህሳስ 30 ቀን 2004 ዓ.ም ክሳቸው ተሰምቷል፡፡
ይህ የክስ ጭብጥ ተጠርጣሪዎቹ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አሸባሪ ተብሎ ከተሰየመው ኦነግ ጋር ተባብረዋል፣ ሰዎችን አደራጅተዋል፣በድርጅቱ ኬንያ ሄደው ሥልጠና ወስደዋል የሚል ይገኝበታል፡፡ በዚህ ክስ መዝገብም በ “ሽብርተኝነት” ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው 9 ሰዎች ሲሆኑ እነኚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርና የኦፌዲን ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣የኦህኮ ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ ኦልባና ሌሊሳና አቶ ደረጀ ከተማ፣አቶ ወልቤካ ለሜ፣አቶ አደም ቡሳ፣ወጣት ሐዋ ዋቆ፣አቶ መሐመድ መሉ፣አቶ አዲሱ ምክሬ እና አቶ ገለገሎ ጉፉ ናቸው፡፡
ተጠርጣሪዎች አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳ በግላቸው ጠበቃ ያቆሙ ሲሆን አቶ ወልቤካ ለሜ እና አቶ መሐመድ ሙሉ ጠበቃ እንደማይፈልጉና በራሳቸው እንደሚከራከሩ በመግለፃቸው በዕለቱ ራሳቸው ተከራክረዋል፡፡ ሌሎቹ መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው በጠየቁት መሠረት ተከላካይ ጠበቃ የቆመላቸው ሲሆን ከነኚህ ዝርዝር ውስጥ አቶ አደም ቡሳ እና ሐዋ ዋቆ ስማቸው በስህተት ስላልተላለፈ ተከላካይ ጠበቃዋ የሁለቱ ስም ዝርዝር እንዳልደረሳቸው፣የክሱ ጭብጥ ተመሳሳይ ስለሆነ ጠበቃዋ ሊከራከሩ እንደሚቆሙላቸው ገልፀው ፍ/ቤቱም ጠበቃዋ ከተከሳሾቹ ጋር እንዲማከሩ የ30 ደቂቃ ጊዜ በመስጠት ለጊዜው ችሎቱ ተቋርጦ ነበር፡፡
በዚህም መሠረት ከ30 ደቂቃ በኋላ የክስ መስማት ሂደቱ የቀጠለ ሲሆን ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች በክሱ መዝገብ ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል መፈፀም አለመፈፀማቸውንና ጥፋተኛ መሆን አለመሆናቸውን የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ተከሳሾቹም “ፈፅማችኋል ተብሎ በክስ መዝገቡ ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል አልፈፀምንም፤ጥፋተኛም አይደለንም” የሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
በራሳቸው የሚከራከሩት አቶ ወልቤካ ለሜ እና አቶ መሐመድ መሉ ክሱ ላይ ተፈፀመ የተባለው ወንጀል ቀንና ወር አልተጠቀሰም፣ወደ ፊት በሚቀርቡብን ማስረጃዎች ለመከራከር እንዲያመቸን ቀንና ወሩ መገለፅ ነበረበት በሚል መቃወሚያ ሐሳብ አንስተዋል፡፡ በተለይ አቶ ወልቤካ የኦነግ አባል ነህ ተብያለሁ፤በድርጅቱ አባል ነህ ከተባልኩ የተሰጠኝ የሥራ ድርሻ ምን እንደሆነና ምን አንዳደረግሁ አልተጠቀሰም በማለት ክሱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡
አቶ መሐመድ ደግሞ ክሱ ግልፅነት ይጐድለዋል በማለት የተቃወሙ ሲሆን አቃቤ ሕግ በበኩሉ ከወንጀሉ ባህርይ ውስብስብነት የተነሳ ቀንና ወር ባይጠቀስም ዓመተ ምህረቱ ተጠቅሷል፤ ቀንና ወር ባለመጠቀሱ የቀረበው መቃወሚያ አግባብነት የሌለው እንደሆነና ሌሎች ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች ካሉ ማስረጃ በዝርዝር በሚሰማበት ወቅት እንደሚያቀርብና ፍ/ቤቱም የተከሳሾቹን ተቃውሞ ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ በዚህም መሠረት ፍ/ቤቱም ክርክሩን ከሰማ በኋላ የተከሳሾችን የተቃውሞ ሐሳብ ውድቅ ማድረጉን ገልጿል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ ያቀረባቸው 25 የሰው ምስክሮች፣4 የሰነድ፣1 የድምፅ መቅረጫ እና ከአንዱ ተጠርጣሪ ቤት የተገኘ በኤግዚቢትነት የተያዘ አንድ መትረየስ ማስረጃ እንዳለው ገለፆ በጠዋቱ ችሎት የ2 ምስክሮች ቃል ተደምጧል፡፡ ከዚያም ቀሪ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ከሰዓት በኋላ የቀጠረ ሲሆን ምስክሮቹ የሰጡትን ቃል በተመለከተ ለአንባቢው እንዲያመች የሁሉንም ምስክሮች ቃል በሚቀጥሉት ህትመቶች አንድ ላይ እንደምናቀርብ ከወደሁ እንገለፃለን፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ ቀሪ የሰው ምስክሮችን ቃል ለመስማትም ፍ/ቤቱ ዛሬ ጥር 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት በቀጠሮው መሠረት ይሰማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የፍኖት ነጻነት ጋዜጣ በተሳምንቱ በአንድነት ለዲሞርካሲና ለፍትህ ፓርቲ የምትታተም ጋዜጣ ናት። ጋዜጣው በብዛት እንዲታተም ፣ በስፋት በየክልሎቹ እንዲሰራጭ እርዳታዎትን የአንድነት ፓርቲ ይጠይቃል።
የፍኖት ጋዜጣ እትም 24ን በሙሉ ለማንበብ ክለዚህ ይጫኑ !