ለ’አጥፍቶ-ልማት ጥፋት’ ዘመነ ማግስት ዕቅድና እርምጃ በዘውገ ፋንታ
መግቢያ፥
ይህ አዲስ ዘመን፣ ያሳለፍነው የ‘አጥፍቶ-ልማት ጥፋት ዘመን’ ፍጻሜ ማግስት ነው ብለን ማመን ይገባል። ሁለንተናችን በምንላት እናት አገራችን ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ወገን፣ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ከገዢውና አገልጋዩ በስተቀር ያልተጎዳ ሰው አለ ማለት ክህደት ይሆናል። ወያኔ ከፈለቀበት ምድርም ቢሆን የከፋ ዕልቂት የፈጸመ መሆኑ ለታሪክ በተረፉት ሰዎች አፍ እየተነገረ ሲሆን፣ በየሸለቆውና ሜዳው ያለው እጽም ደግሞ ተጨማሪ ምስክር ነው። የወገንን ጠቅላላ አስከፊ ሁኔታ በዚች ትንሽ የጽሑፍ መነጸር ለማቅረብ አይቻልም። የጽሑፉም አላማ ይኽ አይደለም። ወያኔ በሀገር ውስጥ ያለውን ትውልድ ካወደመ በኃላ፣ በባህር ማዶ የተሰደደውን ተከታትሎ እያጠፋ ነው። የስደተኛው ወገን አስፈላጊውን ቁርጥ ዕርምጃ እንዲወስድ የሚያስገድድ ከዚህ የበለጠ መከራ የለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ “የአጥፍቶ-ልማት ጥፋት” በሆነ ዘመን ከእንግዲህ ወዲያ በማንጎርጎር የሚኖርበት ምክንያት አይኖርም። ካለበት አዘቅት ለመውጣት ወደ ሰላምና ብልጽግና ዘመን ለመሸጋገር ድልድዩን መፍጠርና መስራት አለበት። ይኽ ካልሆነ ወደታቀደለት ወደ ሶስተኛው ደረጃ አይኑ እያየ ይገባል። ለመግንዘብ ያህል፣ የመጀመሪያው ደረጃ ጥፋት መንግሥቱ ኃይለማርያም ያወደማት ኢትዮጵያ ናት። በሁለተኛው ደረጃ መለስ ዘናዊ ያጠፋው የሀገር ሕልውናና ታሪክ ነው። በሶስተኛውና መጨረሻው ደረጃ፣ ሁሉም ጉዳይ የሚፈጸምበት ጊዜ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ራሳችንን እና እናት ሀገራችን የምንላት እንደታሪክ አድርገን የምናወራበት ወቅት ይሆናል። ይኽን ለማድረግ የተነሱትን አንጠራጠር። ማድረግ የሚገባንን እንድናደርግ ያለንበት ወቅትና ሁኔታ ያስገድደናል። የመለስም ይሁን የሌላውን ውጥን ማክሸፍ ይኖርብናል። ይኽን ስናደርግ በድል ወቅት ማዶ ሆነን መለስ ብለን የተሻገርነውን ገደል ስንገነዘብ ልንኮራ እንችላለን። በክፍል ፩ የቀረበው በዚህ ላይ ያተኮረ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የአስተዳደር ለውጥ እንዲመጣ ያደረገው ጥረት በአምባገነኑ መንግሥት ከሽፏል። ሕዝብ የመረጣቸውን እንደራሴዎቹ በጦር ኃይል ሥልጣን የጨበጠው አረመኔው መንግሥት አሻፈረኝ ብሎ መሪዎቹን ወህኒ ቤት አጎረ፣ መራጩንም ሕዝብ እያደነ ገደለ። የለውጡ እንቅስቃሴ ኃይልና ጉልበት የነበረውን ወጣት በእስርቤት አጭቆ በበሽታ፣ በርሀብና በድብደባ ቁጥሩ ያልታወቀውን ተኪ ትውልድ ጨረሰ። የተረፈው ሲሸሽ የአውሬ ዕራት ሆኗል። ሀገር አቋርጦ የወጣው አብዛኻኛው በባህር ተደፍቆ ሞቷል። የተረፈው በባዕድ ሀገር በአሽዋ ላይ በርሀብና በበሽታ ደክሞ ከወደቀበት በግብፁ፣ የመኑ፣ ሳውዲና ሌላ ሀገር ፖሊስና ቀማኛ በጥይት ተጨፍጭፏል። የኢትዮጵያ ወገን ለእንደዚህ አይነት ውድመት የተዳረገበት ወቅት ካለንበት ዘመን ውጭ እንደማይታወቅ ይነገራል። የወያኔው መንግሥት በኢትዮጵያኖች ላይ የሚያደርሰው ግፍ በኢትዮጵያ ምድር ብቻ የተወሰነ አይደለም። በውጭ የሚኖረው የኢትዮጵያ ወገን ለለውጥ ስላደረገው አስተዋጽዖ ቅጣት፣ ወያኔ ገንዘብ ሊገዛ የሚችለውን ሽብር በኑሮው ላይ ለማድረስ ያወጣው አስፈሪ ምስጥራዊ ዕቅዱ ያመለክታል። የውስጡን ሰላማዊ ሕዝብ አውድሞ፣ አሁን ደግሞ በስደት ዓለም በየአሕጉሩ በሚኖረው ወገን ላይ አተኩሯል። ይህ ድርጊቱ የብዙ ሀገሮችን ህግ የሚጥስ ቢሆንም በንቀት ወይም በተሰጠው ዕለፍ ምልክት ሰርጎገቦቹን አሰራጭቶ የስደተኛውን ሰው ትዳር፣ ኑሮ፣ ንግድና ስራ ከዚያም አልፎ ተርፎ ትብብሩና አንድነቱ እንዲናጋ ያቋቋመውን ማሕበረሰብና ሕብረተሰብ (Association and Community Organizations)እንዲሁም መጸልያ ቤተእግዚእብሔር በነሱ ቁጥጥር ስር እንዲውል፣ ካልሆነ እንዲወድም የሚያደርጉት ትርምስ በአፍሪካ፣ ኢሮፕና አሜሪካ ከተሞች የሚፈጸመው አጉልቶ ያሳየናል። ክፍል ፪ በዚህ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው።
ክፍል ፩ ዕቅድና እርምጃ
የወያኔው መንግሥት ፍጻሜ
በችኮላ ተቀናጅቶ የተቋቋመው የተቀዋሚው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጂት ባልተጠበቀ ሁኔታ በአንድ ምርጫ ሙከራ ድል ማድረጋቸው የመሪዎቹ ስልት ቢሆንም፣ በይበልጥ አጉልቶ ያሰየው የሕዝቡን ቆራጥ ውሳኔ ነበር። ገዥው መንግሥት ያልጠበቀው ሹም-ሽረት ስለሆነበት፣ ሥልጣን በያዘበት መልክ ሙሉ የጦር ኃይሉን በመላው ሀገሪቱ ላይ አሰራጭቶ በሕዝብ ላይ አምጾ የጭቆና አገዛዙን ቀጠለ። የአምባገነኑ መንግሥት መሪ ቀደም ሲል እንዳስታወቁት ከሥልጣን የሚወርዱት ጦራቸው በጦር ኃይል ድል ሲደረግ ብቻ ነው ስለአሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ያለበትን ችግር በሚገባ በመረዳት መሪው ከሰጡት ጥፋትና ዕልቂት ምርጫ ውጭ መፍትሔውን እያሰላሰለ ቆይቷል። አሁን ግን መውሰድ የሚገባውን ድርጊት ለማድረግ አጋጣሚውን ዕድል የሚያልፈው አይደለም። ያላአንድ ሰው ሕይወት ጥፋት ድልን ለመቀዳጀት የሚያስችለውን መንገድ ያውቃል።
የቅንጅት ትንሳዔ
ቅንጅት እንደፈረሰና እንደወደመ ተደርጎ ተወስዷል። ይኽ አርቆ ያለማሰብ የሚፈጥረው ስህተት ነው። ቅንጅት ሥልጣኑን ተቀማና ታሰረ እንጂ አልወደመም። ቅንጂት ወድሟል ከሚባለው ስህተት አስተሳሰብ መውጣት አለብን። ክብርት ም/ሊቀ መንበር ብርቱካን ሚደቅሳ ‘ቅንጅት መንፈስ ነው’ እንዳለችው ያንን ለመቀበል የሚሳነው አዕምሮቢሱ የወያኔው አካልና የሱ ፖለቲካ ደላላ ጥቅሙ ከጭቆና አገዛዙ ጋር የተሳሰረው ብቻ ነው። ‘ተዋግተህ ሥልጣን ያዝ’ ብለው ላፌዙበት መሪ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሥልጣን ማውረጃ መድፉና ጥይቱ “ቅንጅት” ነው። የሕዝብ ምርጫ የተደረገው በእየአንዳንዱ ፓርቲ ሕልውና እንጂ በግለሰቡ መሪ ላይ ብቻ የተመረኮዘ አይደለም። ይህ ከሆነ፣ ሕዝብ ምርጫውን የሰጠው ለፓርቲው አካል እንጂ ለወካዩ መሪ አይደለም ማለት ነው። ቅንጅት ምርጫው ቢሰረቅበትና ቢቀማም፣ ውሳኔውን ዘለዓለማዊ የሚያደርገው ወይም የሚሽረው የሕዝቡ ነጻ ውሳኔ ብቻ ነው። ሕዝብ ሥልጣኑን የሰጠው አካል ሲረከብ ለማየት ሃያ ዓመት፣ ከተገደደም አርባ ወይም መቶ ዓመት መቆየት ይችላል። ለዚህ ድርጊቱ የሚያግደው የጊዜ ገደብ የለም። የቅንጅት አካል የሆነውና በዚያ መንፈስ በምርጫ የተሳተፈው በሕዝብ ምርጫ የተሰጠውን ሥልጣን ለመረከብ በመጠበቅ ላይ እንዳለ መታወቅ አለበት። ይኽ ሊፈጸም የማይችለው ሕዝብና ሀገር ወይም ኢትዮጵያ ሳትኖር ብቻ ነው።
ይህ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ጊዜም ለማይቀረው የመንግሥት ለውጥ ባላሰበው ወቅት ቢመጣ ተረካቢ እንደራሴና አገሪቱን ጠባቂ አካል የለንም ብሎ እንዳይሰጋ፣ ሥልጣን ተረካቢ የ“ቅንጅት” አካል ያለ መሆኑን ማወቅና ማሳወቅ ይገባል። ትንሳዔ ለ’ቅንጅት’ ብሎ ማስተጋባትም አስፈላጊ ነው። የቅንጅት አካል የነበሩትና በመንፈሱም የሚጠቃለሉ ሁሉ የበፊቶቹ ፓርቲ መሪዎች ወይም እያንዳንዱ ፓርቲ በፈጠራቸው አዳዲስ መሪዎች አማካይነት የቅንጅትን ትንሳዔ ዝግጅት ለማቀናበር ኃላፊነትና ግዳጅ አለባቸው። ወያኔ በፈጠረው ውዥንብርና ትርምስ እንዲሁም አንዳንድ የፓርቲ መሪዎች ራሳቸው ከፈጠሩት የፖለቲካ ውስብስብ ውስጥ እንዲወጡና ለቅንጅቱ አካል አመሰራረት ብቁ መሆናንቸውንና ትብብራቸውን ቢገልጹ ሰማይ ጠቀስ ርምጃ ይሆናል። የዚህን ሀገራዊ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚያስተባበር ወይም በቅድሚያ የሚወጥን አንድ ዓለምእቀፍ አማካሪ አካል መፍጠር ተቀዳሚው ዕርምጃ ይሆናል። የዓለምእቀፍ አማካሪ አካል አፈጣጠር እጅግ ለየት ባለ መልክና ስርዓት የተዋቀረ መሆን ይገባዋል። የወያኔ እጅ እንዳይገባና ንክኪት እንዳይኖር የዓለምአቀፉ አማካሪው አካል ከፍተኛ ጥንቃቄ ለማድረግ ስራው በሥልጣን ደረጃዎች የተቆላለፈና የተሳሰረ እንዲሆን መቆጣጠሪያ ብልሀቶችን እንዲጠቀም ሁኔታው ያስገድዳል። በተጨማሪም አካሉ የኢትዮጵያን ቅርጽና ቅርሶች ሁሉ የሚያንጸባርቅ መሆን ይገባዋል። ይህ አካል በጥቂቶች ወይም በተውጣጡ የድርጅቶችና የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች አማካይነት ሊወጠን ይችላል። ምናልባት ከአሁን በፊት ለሕብረት ብዙ አስተዋጽዖ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክርቤት (Ethiopian National Congress ‘ENC’ )በአዲስ መልክና ሕልውና ተጠናክሮ የዓለምእቀፉን አማካሪ አካል በበላዩ ላይ ወይም በጎኑ እንዲመሰረት የሚረዳ ኃይል ነው የሚል ግምት አለ። ሊቀመንበሩ በዚህ ጉዳይ ላይ እራሳቸውን ማዝለቅ ይኖርባቸዋል። በአጠቃላዩ፣ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶችና ግለሰቦች በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ ተጋብዥ ሁነው መገኘት የለባቸውም። የዚህ አካል ወጣኝና መስራች ሆነው መነሳት ይጠበቅባቸዋል።
የቅንጅት ዳግማዊ አቀነባበር
በ2005 ዓ/ም በፊት ትንሽ ቀደም ብሎ የተዋሀደው የቅንጅት አካል እንደነበረው ሆኖ መነሳት ይኖርበታል። ይህ እንዳይሆን የሚያግደው የወያኔ እጅ እንጂ ሌላ ኃይል አይኖርም፣ ቢኖርም በዚህ መንፈስ ጎርፍ የሚነሳውን የሕዝብ ኃይል ሊያግድ ፈጽሞ አይችልም። የቅንጅት ትንሳዔም የፖለቲካ ውዝግብና ጥያቄ የሚያስነሳ አይደለም፣ ለመሆንም አይችል። ሁሉን ጉዳይ መስመር ለመስያዝና መሰናክሉን አስቀድሞ ለማስወገድ ዓለምእቀፍ አማካሪ አካል አስቀድሞ መፍጠር ለሚነሳው ችግር ሁሉ መፍትሔውን ያበጃል። በተጨማሪም አምላክ አስቀድሞ ለዚህ ዘለቄታ ያዘጋጀውን መረዳት ይኖርብናል። ገንዘብ በሚገዛው አሸባሪ ኃይል ጥቅም ኢትዮጵያን ሲያሰቃዩ የኖሩት ዲክታተሮች ሁሉ አንድ በአንድ እየረገፉ ሲዎድሙ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአይኑ አይቷል። የቅንጅት ምክትል ሊቀመንበር ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ከውጩ የኢትዮጵያ ወገኖቿ መካከል መገኘቷ የአምላክን ስራ ተረድተን አጋጣሚውን ወቅትና ዕድል መጠቀም ብልህነት በይበልጥም ጀግንነት ነው። በርግጥ ቅንጅት ፈርሷል ብለው በማመን በየፊናቸው የተሰማሩትንና አዲስ የፖለቲካ ሕልውና የፈጠሩትን ተመለሱና ቅንጅትን ፍጠሩ ማለቱ ምናልባት ለያዙት ሂደት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በዚህ ችግር ከገጠማቸው የነሱ አቋም ለቅንጂት መቀነባበር እንቅፋት እንዳይሆን የዓለምእቀፉ አማካሪ አካል መፍትሔ ይፈጥራል። በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ጨቋኙ መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ የማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲ አላማ ከሆነ፣ ከሕዝብና ከተለያዩ የፖለቲካ ዘርፎች ተቀላቅሎ መስራት የሚገባው መሆኑን በመረዳት እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት በዚህ ብሔራዊ ጉዳይ እንደሚካተት የሚታመን ነው። ሳይሆን ከቀረ፣ የዓለምእቀፉ አማካሪ አካል የሚወስደው ዕርምጃ የማይጣስ ሆኖ መታየት አለበት። የዓለምአቀፉ አማካሪ አካል የሚቀዳጀው መብትና ሥልጣን በሁሉም የተከበረና የበላይነት ያለው ይሆናል። ይኽ አካል በተሰጠው መመሪያና ሥልጣን መሰረት የቅንጅት አካል በምክትል ሊቀመንበሯ በክብርት ብርቱካን መሪነት የሚቋቋምበት ተጠንቶ እንዲቀርብ ወይም የላቀ መመሪያ ፈጥሮ ቅንጅት እንዲቋቋም ያደርጋል። የኢትዮጵያኖች የዓለምአቀፉ አማካሪ አካል የተለያዩ ቅርንጫፎችና ሁሉን ወገን ያካተተ አባል ያለው እጅግ ሰፊ የጠቅላላ ጉባዬ አካልም ይኖረዋል። በውስጡ የሚፈጠሩ ቅርንጫፎች ሁሉ ምግባራቸውና ሥልጣናቸው በመተዳደሪያው ደንብ ውስጥ ይዘረዘራል። በዚች ገጽ የተጠቀሰው ለአንባቢ ሲባል እንጂ የሚደረገውንና መደረግ ያለበትን አውቆና ተንትኖ ለማቅረብ አይደለም። ለዚህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ምሰሶ ሆነው ቤቱን ለሚገነቡት አበዎች ሰፊውን ድርጊትና ዕቅድ ለነሱ መተው ተገቢ ነው።
ከዚህ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀርበው በስደት ለሚገኘው የኢትዮጵያ ወገን ሁሉ ጠንቅ በሆነው አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ነው። የወያኔው መንግሥት በውጭ ሀገር የሚኖሩት የተቀዋሚው ፓርቲ የቅንጅት ደጋፊ በመሆናቸው፣ በቂም በቀል ለመቅጣት ያቋቋሙትና ያዳበሩት የጋራ መረዳጃ ማሕበረሰቦችና ሕብረተሰቦች እንዲፈርሱ አለበለዚያ በነሱ ቁጥጥር ስር እንዲገቡ በገንዘብና በልዩ ልዩ ጥቅም የተገዙ አጥፊዎችን በየሀገሩ አሰራጭቶ አስቀምጧል። ስለዚህ፣ የኢትዮጵያ ወገን እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ መሆኑ የሚሳት አይደለም። ለጥፋት ያሰማራቸው ሰዎች የፖለቲካ ማዕከሎችን ካወደሙ በኋላ አሁን ደግሞ ቤተክርስቲያኖችን ለማፍረስ ሰፊው ዕቅዳቸው በስራ እየዋለ ነው። ድብቅ ሴራውን እንኳንስ ያልተመራመረው እጅግ የተመራመረውም ሰው ተደናብሮበታል። የመንፈሳዊውንና የዓለማዊውን ስርዓት ለይቶ ለማወቅ ተስኖታል። ከንቱ የሆነው ሰው ደግሞ መንፈሳዊ በሆነው ስርዓት ውስጥ ገብቶ “መብትህ ነው፣ መብቴ ነው” እያለ፣ በቀውስ አስተሳሰብ ሌላውን እያሳሳተ ይገኛል። ምናልባት ከዚህ ውጭ ጥሩ ለማድረግ ብለው ባለማወቅና ባለመብሰል ተንኮለኛውን የሚከተሉ አይጠፉም። ጥፋቱ ሰፊ እየሆነና ውዝግብ እየፈጠረ በየከተማው የሳምንቱ ወሬ ዘገባ ሆኗል። ይህ ውዝግብ ከልኩ ያለፈ ሁኔታ እየፈጠረ ስለሄደ ችግሩን መላው የስደተኛው ወገን እንዲያስብበትና ዕርምጃ እንዲወስድ የሚቀጥለው ገጽ በዚህ ችግር ላይ ያተኩራል።
ክፍል ፪ መንፈሳዊ ጽናት
በመንፈሳዊው ድርጅቶች ላይ የሚካሄድ ሽብር
በዳላስ፣ ፖርትላንድ፣ ሎስእንጀለስ፣ ዲስትሪክት ኦፍ ኮለምብያ (ዲ.ሲ)፣ ሻርሎት በሌሎችም ከተሞች በሚገኙት የኢትዮጵያውያን ተዋህዶ ቤተክርስትያኖች ላይ የደረሰው ተመሳሳይ ሁከት በኢትዮጵያ የሰፈነውን ተመሳሳይ አከፋፋይ ስርዓት ያንጸባርቃል። በስያትል የኢትዮጵያ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያንን የወያኔ አጎብጓቢዎች በእጃቸው ለማድረግ ከዚያም ለጌቶቻቸው አሳልፈው ለመስጠት ለብዙ ጊዜ ሲታገሉ ቆይተዋል። ወደ ስያትሉ ችግር ከመግባታችን በፊት፣ በአፍሪካ በካምፓላ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደረሰውን ችግር ብንመረምር ትምህርት እናገኛለን።
የካምፓላው ምሳሌ
በካምፓላ መካነሰላም መድሀኔዓለም ቤተክርስቲያን የተፈጠረው ችግር ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ከዚህ የሰፈረው አስተያየት ልጅ ተክለሚካኤል አበበ በሰጠው ሪፖርት ላይ የተመሰረተ ስለሚሆን ዕውነት ወይም ስህተት በሚባሉ አሻሚ ሀሳቦች ላይ ይህ ጸሐፊ ሸሸት ለማለት ይሞከራል። ልጅ ተክለሚካኤል የወጣቶች መሪ ከመሆኑም በላይ፣ ዳቆን ሆኖ ቤተክርስትያን ያገለገለ በመሆኑ፣ ያደገበትን ዕንቁ ቅርሶች በሚያጋጥመው ቦታ ሁሉ በሚገባ ሲያንጸባርቅ ይታያል። ለዚህም ከፍተኛ አድንቆትን ማትረፉን ይህ ጸሐፊ በአቅሙ ይመሰክራል። በዚህ ጽሑፍ አንድ ወይም ሁለት ያስተሳሰብ ልዩነት ቢፈልቅም፣ ሌሎቹ ቁምነገሮች ልዩነቱን ያደበዝዙታል። ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ልጅ ተክለሚካኤል በጥንቃቄ የሰነዘረባቸውን የመንፈሳዊና ዓለማዊ አሰራርና ስርዓት ለመመርመር ከጽሑፉ ቀነጣጥቤ አቅርቤአለሁ።
“ይሄ ቤተክርስቲያን ሲገነባና የቦታው የባለቤትነት መብት ማስረጃዎች ለአቡነ ኤልያስ ሲሰጡ፡..” “ብዙ ሰዎች፡ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን በዚህ ጉዳይ ላይ አፍስሰዋል።” “ህዝብ ድምጽ የሰጠበትን ጉዳይ፡ ያለምንም አጥጋቢ ምክንያት መሻራቸው አግባብ አይደለም።” “ሕዝብ በህጋዊው ሲኖዶስ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ፡ እንዲያምጽም ይገፋፋል።” “በመሰረቱ፡..የውጪው ሲኖዶስ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ያላቸው ስልጣን የሚመነጨው ከህዝቡ ነው።” “ህዝቡ አዝኖና ተበሳጭቶ ወደሌላ አቅጣጫ እንዳይሄድ፡ ማድረግ ነው እንጂ፡ህዝብን የሚያሳዝን ውሳኔ መወሰን አግባብ አይደለም።” “በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም ያሉት አባቶች የማስተውልባቸው ችግር፡ አንደኛ ህዝቡን አያደምጡም ወይንም በሕዝቡ አይተማመኑም።”
ቤተክርስትያን የሚቋቋመው ለምዕመናን መገልገያ ነው መባሉ ትክክል ነው። ለካህናቱና ለመነኩሲው ከሆነ ገዳም ይሆናል። ቤተክርስትያን የብዙ ትውልድ ቅርስና ሀብት ነው። የሚቋቋመውም በምዕመናን አስተዋጽዖ ነው። የበቴክርስቲያኑ ጠባቂ፣ ተጠባባቂና ኃላፊው እንዲሁም ባለንብረቱ ካህናቱ ናቸው። ይህን ሥልጣን የሚጋራ ወይም የሚሻማ ሰው ሊኖር አይችልም። የቤተክርስትያኑ ስራ ሁሉ የመንፈሳዊ ስራ ስለሆነ ማንም ምዕመናን ከካህናቱ በላይ የሆነ ስልጣን እንዲኖረው የቢተክርስትያን ካኖን (ህግ) አይፈቅድም። ምዕመናኑ ታዞና ተጠይቆ ያገለግላል። ራሱ ለእግዚእብሔር ለማድረግ የፈለገውን ግብርና ስለት ለቤተክርስቲያን ያበረክታል። በአጸፌታው ስልጣንና ክብር የሚጠይቅና የሚሰጠው አይሆንም። ምዕመናኑ ለቤተክርስቲያኑ የሚለግሰው ለነፍሱ ስለሆነ አጸፌታ መጠበቅ ፈጽሞ አይገባውም። ካህናቱ ስራ እንዳይበዛበትና ከልምዳቸው ውጭ በሆነው ስራ በከንቱ እንዳይቧዝኑ ከምዕመናኑ ከሚችሉት እርዳታ ይጠይቃሉ። ለእንደዚህ ያለ ቋሚ ስራ ቦርድ (ስራአስኪያጅ) አማካሪ አካል መፍጠር ልምድ ሆኗል። ማናቸውም ሰው የገጠመውን ችግርና ኑዛዜ የሚነግረው ለቄሱ እንጂ ለምዕመናን አይሆንም። ካህኑ በማናቸውም የቤተክርስትያን ምግባር ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጥ ወይም የተደረገውን ለመለወጥ የመንፈሳዊ ስልጣን አለው። ምዕመናኑ ያን ውሳኔ ሊለውጠው ወይም ሊጥለው አይችልም። ምክንያቱም ምስጢርና ኑዛዜ ሰሚው ካህኑ ብቻ ስለሆነ ውሳኔውም በዚያ ዕውቀት ላይ የተመረኮዘ ስለሚሆን ምክሩ የቦርዱ ውሳኔው የካህኑ ይሆናል። ይህ ወዲህ ወዲይ የሚእስብል ጉዳይ አይደለም። የመንፈሳዊና የዓለማዊው አስተዳደር መሰረታዊ ልዩነታቸው ይህ ነው። ስራአስኪያጅ ቦርድ አማካሪ ነው። የስራውን ዕቅድና ፍጻሜ ውሳኔ ካህኑ ተቀብለው እንዲያጸድቁት ምክሩን ያቀርባል። ቦርድ ሥልጣን የለውም። ምክንያቱ ከላይ ተጠቅሷል። ግን ይኽን የማያውቁ ሰዎች ሕዝብ የመረጠውን ቦርድ ካህናቱ ሻሩት የሚባል አሳዛኝ፣ አላዋቂና አሳፋሪ ነገር ይሰማል። እነዚህ ግለሰቦች በዓለማዊው ክፍል የሚደረገውንም አንዱንም የሚያውቁ አይመስሉም። ኮንግረስ የወሰነውን ጉዳይ የበላዩ ሴኔቱ ወይም ፕረዚዳንቱ ያፈርሱታል። ዝቅተኛው ፍ/ቤት የወሰነውን ከፍተኛው ፍ/ቤት ያፈርሰዋል። የካህናቱ የበላይነት ሥልጣን እንደዚሁ ነው። ሕዝብ የወሰነውን ፍ/ቤቱ ሰፊ ጥቅሙንና ጉዳቱን አመዛዝኖ ያፈርሰዋል፣ ካህናቱም እንዲሁ።
በካምፓላ የሚገኘው የመካነኢየሱስ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሕዝብ አዲስ ቦርድ መረጠ። የቤተክርስትያኑ መሪ በአላቸው መንፈሳዊ መነጸር ተመርተው የቀድሞውን የቦርድ አካል በነበረበት እንዲመለስ አደረጉ። የተከፋው ብርድ እምነቱን በካህኑ ላይ አጽንቶ አሜን ብሎ መቀበል ይገባው ነበር። ቤተክርስቲያኗን ከማናቸውም ችግር የሚጠብቋት ካህናቱ ብቻ ናቸው። አለበለዚያ የወያኔም ሰው ካልተቀላቀልኩ ብሎ በዚሁ መልክ ሊጮህ ይችላል። ቤተክርስቲያን የሰፊው የሲኖዶሱ አስተዳደር አካል አንዱ ናት። በማናቸውም አሰራር አንድ ካህን በቤተክርስቲያን ውስጥ የተዛባ ነገር ከፈጸሙ የሚቆጣጠር የበላይ የሲኖዶሱ አካል አለ። እንከን ሲገኝ በካህናቱ ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ወደኋላ አይልም። በካምፓላ ያለው የከፋው የቦርድ አካል አቤቱታውን ለበላይ አቀረበ። የበላዩ ባለሥልጣን የበታቹን ውሳኔ አጸደቀ። አሜን! በቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ላይ አቤቱታ አስፈላጊ አልነበር። ዕልክ ይታያል። በድጋሜ የበላይ ባለሥልጣን የሰጠውን ውሳኔ ተቀብሎ እሺ አሜን ቢል ኖሮ ትልቅ አርእያ ባሳየ ነበር። ግን ዕልክ፣ ተልዕኮ ወይም የመንፈስ ችግር እንዳለው ሰው አቤቱታው ለመላው ዓለም ሕዝብ እንዲሰማ አደረገ። በዚህ ድርጊት የተጎዳውና በመጥፎ ስራ የተጋለጠው የመንፈሳዊው ስራ ያልገባቸውና ሥልጣን ለመያዝ በከንቱ የደከሙት የቦርዱ አባሎች ናቸው። ብዙ ሰዎች ቤተክርስቲያንን እንደ ማሕበረሰብ(ኮሙኒቲ)ድርጅት አድርገው ማሰብ ጀምረዋል። ምዕመናን በፍቃዳቸው ቤተክርስትያን ያገለግላሉ። ከዚህ በጎ ስራ ጋር የተያያዘ ሥልጣን የለም፤ ሽሚያም አያስፈልግም። ካህናቱ ባላቸው ታዋቂ ወይም ምስጢራዊ ጉዳይ ምክንያት የሚያፈርሱበት ሥልጣን አላቸው። ወገኖቻችን በብልሀነት እየላቁ መሄድ ይገባቸዋል። ከዚህ ውጭ ሲደረግ ለወያኔዎች ቀዳዳ እንደመክፈት ሴራ ሆኖ ጎልቶ ይታያል። በነሱ ልብ ዕውነት ቢኖርም፣ ድርጊት በሌላ ቦት ወያኔን እንደሚጠቅም ማወቅ ይገባል።
በስያትል በኢትዮጵያ ቅዱስ ገብርኤል ተዋህዶ ቤተክርስትያን የተፈጠረው ችግር ከሌሎቹ በጣም የተለየ አይደለም። የቤተክርስቲያኑ ጠባቂ ካህናት በየጊዜው አስቸጋሪና ራስን ወዳድ በሆኑና የወያኔ ንክክነት የሚታይባቸው ሰዎች ቤተክርስቲያኑን ለማከፋፈል ሲጥሩ ኖረዋል። ካህናቱ በመቻልና በምክር በማስተማር እያስታገሱ ቆይተዋል። ሆኖም ቤተክርስቲያኗ አንዳንድ አስቸጋሪ ሰዎች ከሚፈጥሩት ብጥብጥ አልዳነችም። በዚህ ምክንያት የቆየ ችግር ያላቸው ሰዎች እያገረሸባቸው ሌሎችም ዕንከኖች እየተደራረቡ ችግሩ ሊስፋፋ በቅቷል።
አንዳንድ ሰው የወያኔ ደጋፊ ወይም ተቃራኒ መሆኑን እራሱም አቋሙን አያውቅም። ጥቅም ወዳለበት ሲገለባበጥ ትናንት ምን እንደሰራ ዛሬ ምን እንደሚያደርግ አያውቅም። ‘ወያኔ ነው’ ሲባል ወያኔ የምትኮተኩተው እየመሰለው የሚቧዝን አይጠፋም። የዚህ ወጥ የሆነ አንድ ሲያለቅሱ በጣም የሚያስለቅስ፣ ሲስቁ እየዘፈነ በጣም የሚያስቅ ለየት ያለ ጠባይ ያለው ሰው በየከተማው መቸም አይታጣም። ይኼው ሰው ተታላይ የሆኑ ጥቂት ወጣቶችን ሰብስቦ “የቅዱስ ገብርኤል ተዋህዶ ቤተክርስትያን የተለገሰውን ፕያኖ አውጥቶ ካልጣለ ወጥተን እንሄዳለን” በሚል ዘመቻ አነሳስቶ የተከተሉት እንደወጡ ቀርተዋል። ሌላ ቤተክርስቲያን አቋቁመው ከዚያም ሁከት ተፈጥሮ እንደገና ለብዙ ተከፋፍለው አንዳቸው አዲስ አበባ ባለው ሲኖደስ ስር ተካቶ በሰላም እየኖሩ ናቸው ተብሏል።
የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የዱሮ ስራአስኪያጆች በሌላ ተተክተው ስለተገለሉ የተከፉ መሆናቸውን በተለያየ መልክ ቅሬታ ያሰሙ እንደነበር ኑዋሪው ሁሉ የሚያውቀው ጉዳይ ነው። እንደሚባለው አንድ ሰው በቅርብ ጊዜ ቤተክርስቲያኑን በበላይነት ለማስተዳደር ጠይቆ፣ ካህናቶቹ ቁርጥ መልስ ሰጥተው በዚያም ተበሳጭቶ ነበር ተብሏል። እንደሚወራው የተሰጠው መልስ ‘አንደኛ ዳቆን፣ ካህን ወይም ጳጳስ ያልሆነ ሰው ቤተክርስትያኗን እንዲያስተዳድር ለመሾም የሚያዳግት መሆኑን፤ ሁለተኛ ብቁ የሆኑ አስተዳዳሪዎች ቤተክርስቲያኗ እንድሏት፣ ሶስተኛ ሊላ ከተፈለገ፣ ሲኖዶሱን በመጠየቅ መሪ እንደሚመደብላቸው የሚደረግ መሆኑን’ ስነስርዓቱን እንዲያውቅ በደንብ የገለጸለት መሆኑ ታውቋል። ዳሩ ግን፣ ሰውየው አላከበሩኝም በሚል ግምት ቅሬታው ቀን የያዘለት ይመስላል ሌሎች ችግሮች ተደራርበው በአካባቢው ብቅ ብለዋል። በዚህ ዐይነት ቤተክርስቲያኑን ማተራመሻ ይሆናል ብለው የቆሰቆሱት ሁሉ ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ከሸፎባቸዋል።
ካህናቱን ለማገጨት አጋጣሚ ሆኖ ያገኙት አንድ ድርጊት በቅርብ ጊዜ ተፈጽሟል። ቦርድ ያልሆኑ ምንም ሥልጣን የሌላቸው ሰዎች በመንፈሳዊው ስራ ጣልቃ ገብተው ሰባኪ ካህን ለቤተክርስቲያኑ ለመሾም በታላቅ ድፍረት ተነሳስተው ተደርጎ የማይታወቅ አሳፋሪ ድርጊት ፈጽመዋል። አንድ የቤተክርስትያኑ ታላቅ ሊቀሊቃውንት ወደ ሌላ ከተማ ለከፍተኛ ስራ በመዘዋወራቸው፣ ያንን የግልና የካህናቱን ውሳኔ በተንኮል ለመመረዝ እኒህን ታላቅ ሊቃውንት ስለአባረሯቸው መመልስ አለብን ብለው ትርምስ ጀመሩ። እንደተለመድው መግቻ በሌለው ዜና ማሰራጫ አማካይነት ችግራቸውን በዓለም ዙሪያ ላለው ወገን እንዲሰማ አደረጉ። በዚህ የተከፋው ምዕመናን ቤተክርስቲያናቸው ደምቃ እንድትታይ ቁጥሩ በሶስት እጥፍ በዝቶ ጸጋ ለብሶ አምሮበት ታይቷል። በጥባጮቹ “ኮሚቲ” በሚል ስም ብቻ አስጸያፊና ስርዓት የጎደለው ደብዳቤ ለሕዝብ ከዚያም አልፎ ለሲነዶሱ ልከዋል። በላኩት ደብዳቤ ላይ የኮሚቲው ሊቀመንበር ስምና የሌሎቹም ስም ዝርዝር የሌለበት መካን ደብዳቤ ተሰራጨ። ዳሩ ግን፣ ግጭት ለመፍጠር የወጠኑት ተንኮል ራሳቸውን መልሶ አጋልጧቸዋል። ታላቅ የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሁንም ወደፊትም ሀብትና ተስፋ የሆኑትን ሊቀሊቃውንት ጋብዘው ካሉበት ወደ ስያትል አምጥተው በዶለቱት ሴራ ወጥመድ ለማስገባት ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቶ ታላቁ ምሑር መክረውና ባርከው ቤተክርስቲያኗን በታማኝነት እንዲያገለግሉ አደራ ብለው ተመልሰዋል።
ቅዱስ ገብርኤል ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያደረገውና የፈጸመው በብዙ ሚሊዮን ብር ከሚካሄዱት ትላልቅ የመንግሥት ድርጅት ካሳዩት እጅግ የሚያስንቅ ስራ በወጣቱና ሕብረተስቡ አማካይነት ግሩም ውጤት አሳይተዋል። ካህናቱና ምእመናኑ በከተማውና በስቴቱ መታወቅና መመስገን ይገባቸዋል። ሠርጉ፣ ክርስትናው፣ በክፉም ጊዜ ሀዘንተኛ የሚጽናናበት፣ በበዐል ጊዜም ወላጆችና ልጆች ያገር ልብስ በመልበስ ባህላቸውን የሚያንጸባርቁበት ዕድል እንዲያገኙ ይች ቤተክርስቲያን ምክንያት ሆናለች። ይች ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ተወልደው፣ ተጠምቀው፣ መዝሙር ዘምረው አድገው በየዩኒቨርስቲው ገብተው በታላቅ ደረጃ ተመርቀው የወጡት ኢትዮጵያኖችን ቁጥራቸውና ብዛታቸው አስደናቂ ሆኗል። አሁንም ወጣቱ ትውልድ፣ በባህሉ፣ በዕድገቱና በትምሕርቱ በቤተክርስቲያኑ ክብካቤ እየፋፋ ነው። ሕብረተሰቡ በአንድ ወቅት ብዙ ዕክል ወድቆበት ነበር። በወጣቶች የልክስክስ ጠባይ የተለከፉ ለራሳቸው፣ ለቤተሰብ፣ ለሕብረተሰቡና ለከተማው ሕዝብ ችግር እየፈጠሩ የመንግሥትን የገንዘብና የህግ አቅም እየሟጠጡ ትልቅ ችግር ሆነው ነብር። የነዚያ ቁጥር እጅግ እያነሰ እንዲሄድ ቤተክርስቲያናችን ታላቅ ሚና በመጫወት ትገኛለች። ልጆቻቸው በታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች ገብተው የሚማሩት ወላጆች አብዘኽኞቹ የማይጽፉና የማያነቡ ናቸው። ከሕጻንነታቸው ጀምረው ቸክ የሚጽፉት፣ ደብዳቤ የሚልኩ ሌላም ሂሳብ የሚሰሩ ልጆቹ ናቸው።
ቤተክርስቲያኗ ታገልግል፣ አንወካት። ሕጻናት በተረጋጋ ሕዝብ መካከል ይደጉበት፣ አንረብሽ። ወላጆችም ያሳድጉበት። ይች ቤተክርስቲያን ብዙ መቶ በየሳምንቱ የሚጎርፉባት፣ ዓመት በዐል ሲሆን ደግሞ በሺህ የሚቆጠር ሕዝብ የሚሰበሰቡበት ቦታ ነች። ለአካባቢው ግርማ ሞገስ የሰጠች ነች። ለሕዝብ ብዙ ጥቅም አምጥታለች። ካህናቱ አስደናቂ ስራ ሰርተዋል። የእስልምና ዕምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ሀዘን ደርሶባቸው እንግዳ እንዲቀበሉ መጽናኛ ቦታ አዳራሹን እንዲፈቅዱላቸው ጳጳሱን ጠየቁ። ጳጳሱ አዳራሹ ከፈለጉበት ቀን ጀምሮ ለነሱ እንዲመደብ ባስቸኳይ አዘው ማናቸውም ዕርዳታ እንዲደርግላቸው አደረጉ። ስትፈልጉ ተገልገሉበት ብለዋቸዋል። በዚህ ድርጊት የተመሰጡ ወገኖች በፋሲካ ጊዜ በሬዎች ገዝተው ለቤተክርስቲያኑ አበረከተዋል።
መደምደሚያ
ኢትዮጵያ ሁለት ችግሮች ገጥመዋታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ካለበት አዘቅት የሚወጣው ባለፈው እንደታየው በመቀናጀትና በህብረት ነው። ቅንጅት የተሰጠውን ሥልጣን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑ አለበት። ስለዚህ ዓለምእቀፉን አማካሪ ቶሎ መርጦ እሱ ደግሞ በበኩሉ ቅንጅትን እንዲያቋቁም ማድረግ ሌላ ቀላል አማራጭ ያለ አይመስልም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክር ቤት እንዲሁም ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ለዚህ ዕቅድ መሳካት ቁልፉና በሩ ናቸው። አንዱን ጠቅሶ ሌላውን ማስቀረት ትክክል ስለማይሆን ለዚህ የሚያገለግሉትን ከመጥቀስ መቆጠብ ተመርጦ የብዙ ሰውና ድርጅቶች ስም አልተነሳም። ዳሩ ግን፣ ሶስቱ የከፍተኛው ፍ/ቤት ዳኞች ሌሎችም ተስደው የወጡት እንደሚጨመሩበት አያጠራጥርም።
ወያኔ የውጩን ስደተኛ ወገን ለማጥፋት ሰፊ ዕቅድ አለው። በኤትዮጵያውያን ማሕበረሰብና ቤተክርስቲያኖች እንዲሁም መስጊዶች የሚያሰራጨው የማተራመሻ ዘዴ ዘለቄታ ያለው ጠንክ እንደሚያመጣ አያጠራጥርም። የብዙዎቹ ማሕበረሰቦች ችግር የወያኔ እጅ እንዳለበት ያመለክታል። ስያትል የሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ተዋዶ ቤተክርስቲያን የሲኖደሱ ዋና ጽ/ቤት ሆኖ የሚያገለግል በጠቅላላም ለኢትዮጵያኖች ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥ ስለሆነ፣ ወያኔ በእጁ ቁጥጥር ለማግባት ካልሆነም ለማፍረስ ያለው ፍላጎት የማያጠራጥር አይደለም። የሚታየው አሳዛኝ ጉዳይ፣ ከኋላ ሆነው መልካሙን ሰው ከሚወደውና ከሚወዳቸው ሕዝብ ጋር በማያውቀው ተንኮል ማጋጨታቸው ነው። ከዚህ ድርጊት የሚያመልጥ ድርጂት የለም። ሁሉም በተራው ይህ ጣጣ ይገጥመዋል። ስለዚህ ወገኖች ተባብረው የተነሳውን ሽብር ማስታገስና እንዳይደገም ማድረግ ይገባቸዋል።
==============
ስለ ጸሐፊው (ዘውገ ፋንታ)
ዳቆን ሆኖ አባቱን እየተከተለ በላስታ በየቤተክርስቲያኖችና ገደማቱ በድቁና አገልግሏል። መጀመሪያ በስያትል ቤተክርስቲያን ሲቋቋም ብዙ ሳይቆይ ቦርድ የተባለው አካል እራሱን ፈላጭ ቆራጭ አድርጎ፣ ቄሱን ተቀጣሪ ነህ፣ አባረንሀል ብለው ቤትክርስትያኑን እንዳይቀዱስበት በሩን ዘጉ። እኒህ አገልጋይ ቄስ ሊቀሊቃውንት አስተራየ ጽጌ ናቸው። እሳቸው ባዘዙት መሰረት በስያትል ከተማ መሐል ካለ አንድ ትልቅ ቤተክርስቲያን ባለቤቶቹ ጸሎት በማያደርጉበት ሰዓት ቂስ አስተራየ ጸሎት እንዲያደርጉ እንዲፈቅዱላቸው በመጠየቅ ስለተፈቀደላቸው ከዚያ ቅዳሴና ጸሎት ማድረግ ተጀመረ። አዲሱም ቤተክረስትያን ቅዱስ ገብሬል ተባለ።