ረሃብና የኢትዮጵያ ተስፋ በፍሬሰው ፈለቀ
ረሃብ በሀገራችን እንደማንኛውም የዓለም ሕዝብ የሚታወቅ ሲሆን በኢትዮጵያ ለየት የሚያደርገው ባለፉት አርባ ዓመታት ከረሃብ የተለችበት ጊዜ አለመኖሩና መለመዱ ነው። በየአገሩ ያለው ረሓብ እንደማኅበረሰቡ ባህልና የኑሮ ደረጃ የሚገለጽ ሲሆን በኢትዮጵያ ረሓብ አለ የሚባለው በርካታ ሰዎች ሲሞትና ዓለም አቀፍ ዜና ማሰራጫዎች መዘገብ ሲጀምሩ ነው።
ለመሆኑ “ረህብ” ምንድነው? እንዴትስ ይገለጣል? ረሓብና ሰው? ረሓብና እንሣት፤ አእዋፍ፤ እጸዋት፤ በምድሩ ላይ ያለው አፈሩ ድንጋዩ ቀየው… ወ.ዘ.ተ ምልኩን መጠኑን ይቀይራል። ረሓብን በቴሌቪዥን መስኮት የከሳ ገጽታ የተቀዳደደና የቆሸሸ ልብስ ወይም ራቁት አካልን መመልከት ረሓብን ይግልጸዋል?
የዓለም ምግብ ድርጅት ባለሙያዎች ረሓብን ከመብትና ከሞራል (ሥነ-ምግባር) ጋር አጣምረው ይመለከቱታል። የሕፃናት መብት ወይም የሕፃናት ሞራላዊ ደህንነት መብትን በረሓብ ቀጣና ውስጥ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ በአንክሮ ይገልጹታል። የራበው ሰው የሞራል ውድቀት ይጠናወተዋል፤ የአስተሳሰብ ነጻነት፤ ዕውቀቱ ጉልበቱ የማንነቱ ጥያቄ በውስጡ ያሉ የእሱነቱ ሕዋሳት ሁሉ ይከዱታል። የእርሱ አይደሉም አይታዘዙለትም። ሌላው ቀርቶ ለመለመንም አቅም ያስፈልጋል። ልመናንም ለመልመድ ጊዜ ይጥይቃል። ረሓብ ደግሞ ጊዜ አይሰጥም። በሀገራችን በብዛት የሚሞተው የልመና ልምድ የሌለውና የዋሃንና ከአምሥት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት ይበዛሉ።
የኢትዮጵያን ረሃብ መነሻዎች በርካታ እንደመሆናቸው ሁሉ ረሃብንም ለመቆጣጠር ውስብስብ የሆኑ ችግሮች የተጋረጡበት ነው። ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ የተፈጥሮ ክስተት (የአየር ጸባይ ለውጥ) የመንግሥት ፖሊሲ፤ መሬትና ውኃ አጠቃቀም፤ የሀብት ክፍፍል ፍትኀዊነት፤ እርዳታና ተያይዥ ጉዳዮች፤ ቅድመ ዝግጅት አለመኖር የመሳሰሉትን መመልከቱ ረሃብ በኢትዮጵያ ያለበትን ሁኔታና ወደፊትስ የሕዝባችን ተስፋ ምን ሊሆን እንደሚችል ግምት ለመስጠት ይረዱናል።
ረሃብ የመጨረሻ ግቡ ምንድን ነው? ችግር፤ ችጋር፤ ጠኔ፤ ጣር …ወ.ዘ.ተ. የትኛው ቃላት በደምብ እንደሚገልጸው አላውቅም። ረሃብ ጠኔ ደረጃ ከደረሰ በምግብና በመድኀኒት መከላከል የሚቻልበት ሁኔታ ቀርቶ በሕይወት መትረፍ የሚቻለው እንደሎቶሪ በዕድልና በእግዚአብሔር ስጦታ ብቻ ነው። ጠኔ ደረጃ የደረሰ ረሃብተኛ ቢድንም እንኳን በወደፊት ሕይወቱ ላይ በቋሚነት ሊመጣ የሚችል የጤናና የአእምሮ ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
በአገራችን በተለያየ ጊዜ ተክስቷል። በ1957፤ 1966፤ 1977 1983-2004…? ዛሬም ኢትዮጵያ በረሓብ እየተሰቃየች ትገኛለች። ከረሓብ ታሪካችን እንዳየነው የ1956-57 የነበርው ሁኔታ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የነበረው ግንኙነት አገሪቷ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የነበራት ዕይታ ደህና ስለነበር የከፋ ነበር ማለት አይቻልም። የ1966 ዓም ረሓብ ይፋ በመውጣቱና የምዕራቡ ዓለም የንጉሠ ወይም የሥርዐቱ አስፈላጊነት እያከተመ በመሄዱ ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ በመነዛቱ ለመደበቅ አልተቻለም ነበር። የ1977ዓም ረሓብም የወታደራዊ አምባገነን መንግሥት ሊቆጣጠረው ባለመቻሉ የደረው ዕልቂት ቀላል አልነበም።
ከ1983 ዓም ወዲህ ያለው ሁኔታ ግን በብዙ መልኩ የተለየ በመሆኑ አገሪቱ ከረሓብ የተለየችበት ጊዜ አለ ብሎ መናገር የሚቻልበት ሁኔታ የለም።
ለዚህም ዋና ዋና ምክናያቶች በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ርሓብን /ምግብን/ ዋንኛው የፖለቲካ መሣሪያ ማድረጉ ነው። ይህም ሣያንሰው የዚህ መንግሥት አነሳሱና አመጣጡ ዘርን፤ ጎሣን፤ ክልክልን …ወ.ዘ.ተ ልዩነቶችን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ቅድሚያ ለእኔ ዘር ለጎሣዬ የሚል አሰራርን በማስከተሉ ከራሱ ጎሣ ውጭ ያሉት ሊበደሉ ግድ ይላል።
የትግሬ ነፃ አውጭ ግምባር (ሕወሓት/ወይኔ) ወደ ሥልጣን ሲወጣ ከ300000 (ሦስት መቶ ሺህ) አባላት በላይ ቁጥር በላይ ያለው የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት ደሞዙን በማቆም ከነቤተሰቡ በአንድ ጊዜ ወደ ረሓብተኝነት ተዛወረ። የፖሊስ የደህንነት አባላትም እንዲሁ። በዚህ ብቻ አልቆመም በአንድ ወቅት እስከ 52000 ሠራተኛ ያንቀሳቅስ የነበረው የሕንፃ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት፤ የባንክ የዓሰብ ወደብ …ወዘተ ከሥራና ከደሞዝ ሲታገዱ ሕወሓት/ወያኔ እነዚህ ሰዎች/ሠራተኞች እንደጠላት ምርኮኛ ወታደር እንጂ እንደ ዜጋ አልቆጠራቸውም። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ከዓሰብ ወደብ ከልዩ ልዩ ሥራና መኖሪያ የተፈናቀሉ፤ ከልጅነት እስከ እውቀት ያፈሩትን ንብረት ተዘርፈው በአዲስ አበባ ትልቁ አደባባይ ለሦስት የክረምት ወራት ያለምንም መጠለያ የቀን ፀሐይ የሌሊት ቁርና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው አሳልፈውታል። ክዚያም ቀጥሎ የሕንጻ ኮንስትራክሽን ከ4000 በላይ ሠራተኞች ለአንድ ሳምንት የዘለቀ የረሃብ አድማ አድርገው ነበር።
ከዓሰብ ወደብ ተፈናቃዮችና ከሕንጻ ኮንስትራክሽን ሠራተኞች ትግል ምን እንማራለ? “ሰው በሰውነቱ እንደሰው ክቡር ነው” ግን የትኛው ሰው?
“ሰው ባገሩ ሰው በወንዙ ቢበላ ሣር ቢበላ መቅመቆ፤
ይከበር የለም ወይ ማንነቱ ታውቆ።”
ሰውነት፤ አገር፤ ክብር፤ ማንነት ዛሬ የት ናቸው?
አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ፤ አህጉር አቀፍና የብዙ አገራት ዲፕሎማት የሚገኙባት ከተማ እንደመሆኗ ሦስት ወር ክረምት ያለአንዳች መጠለያ ሲሰቃዩ ለሰው ልጅ መብት ቆመናል የሚሉ ድርጅቶችም ሆኑ ጩኸታችንን የምናሰማባቸው አገሮችና ተ.መ.ድ አንድ ነገር ማድረግ ሲችሉ አላደረጉም። ለማድረግም አልፈለጉምም። የሰው ልጅ ስቃይ ሲባል የየትኛው ሰው? ለዓሰብ ወደብ ተፈናቃዮች የተሰጠ መልስ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰጠ መልስ ነው። ዛሬም በኢትዮጵያ ሕዝቡን፤ እንሣቱን እጽዋቱን እያረገፈ ያለው ረሓብ ከዓለም ሕዝብ መደበቁ ሳያንስ የሚሰጠው እርዳታ ለፖለቲካና ወታደራዊ ጠቀሜታ በሚውል መልኩ መሰጠቱ የማን አለብኝ ተግባርና ረሓቡን በቀጣይነት ሕዝቡን በተገዥነት አገሪቱን በጥገትኝነት የሚያኖር በጥናት የተደገፈ ሥልታዊ ዕርዳታ ነው።
የዛሬዎቹ 21ኛው ክ/ዘመን አይሁዶች /እሥራኤል/ ከዛሬ 70 – 80 ዓመታት በፊት በአውሮፓና በሌላው ዓለም ምን ዐይነት የሰውነት ደረጃ ነበሩ? ከናዚ ጭፍጨፋ በፊት በሚደርስባቸው መከራ ዓለም በምን ዐይን ያያቸው ነበር? እነኛ ከኖሩበት ቀዬ በግድ እየተፈናቀሉ ወደ ሞት ቅጥር ሲጓዙ ምንም ማለት አልነበሩም። የእሥራኤል መንግሥት ተቋቁሞ ጠንክሮ ሲወጣ እራሱን ሲያስከብር እነኛ በግፍ የተፈጁ አይሁዶች ሰማዕታት ሆኑ። የእሥራኤል መንግሥት እራሱን ባያስከብር እነኛ በግፍ የተጨፈጨፉ አይሁዶች ሰማዕታት ባልተባሉ ነበር። ከዚያን አልፎ በመላው ዓለም ለዘመናት ተበታትነው የነበሩ የአይሁድ ዝርያዎች ከየሥርቻው እየተፈለጉ ወደተከበረችው ውድ ምድር እሥራኤል ተሰባሰቡ። በትረ ክብራቸውንም አጥብቀው ያዙ።
ዛሬ እኛ ሕዝባችን ምድራችን ስብዕናችን ማንነታችን ክብራችን የት ነው ያለው? ያዛሬውን ችግራችንን ስንመረምር እንዴት እንቀበለው? በእሳት የታቃጥሉ የኢትዮጵያ ስደተኞች የሉምን? ወያኔን ሸሽተው በሕንድ ውቅያኖስ በሚጣሉ፤ የባሕር አውሬ እራት የሆኑ፤ በሽፍቶች እያተዘረፉ የሚገደሉ፤ ከተደፈሩ በኋላ የሚገደሉ፤ የትም የሚጣሉ፤ በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ጥቃት የሚደርስባቸው፤ በኀይማኖታቸው የሚሰቃዩ የሉምን? እነዚህ ኢትዮጵያውያን ፍጥረቶች (ሰዎች) መንግሥት አላቸው? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያዊ ስደተኛን እንደሌላ አገር ስደተኞች በእኩል ዐይን ያያቸዋል? ማንን ፈርቶ? ማን ሊወቅሰው? የኢትዮጵያውያን እንባ የማይፈስበት ምድር አለ? ያልተዋረደበት ምድር ተፈልጎ አይገኝም። ታዲያ በዚህ ሁኔታ እያለን እንዴት እንረዳዳ? የተረፈው ምንም ለሌለው፤ በትርፍነት ከሚደፋው ባዶ አንጀቱን ለሚደፋው እንዴት እናዳርሰው እናካፍለው? ብሎ መጨነቅ የኢትዮጵያዊ ዜግነት ጉዳይ ብቻ ሣይሆን ሰው የመሆን ሕሊናዊ ፈተና ነው። የሰውነት ደረጃችንንም ይነግረናል፤ ሰው በመምሰልና ሰው በመሆን መካከል ያለውን ማንነታችንን እንረዳበታለን።
በሀገራችን ያለው ረሓብተኛ ቁጥር ከሚነገረው አጥፍ በላይ ነው። የረሓብተኛው ምክናያት እንዲሁ። ስቃያቸው ሊታየን አይችልም። ከግምት ውጭ ነን። ብሶታቸው ሊሰማን አይችልም። ይህንን ለማየትና ለመስማት የሚያስችል የመገናኛ ብዙኃን የሉንም። የአገራችን ሕዝብ ዛሬ የዓለም ሕዝብ ሞልቶ ከተረፈው የመረጃ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አይደለም። ይህ ደግሞ በረሓቡ ላይ ተጨማሪ አደጋ ነው። የመገነኛ ብዙኃን በአገር ውስጥ ሕወሃት በሚያስተዳድረው መንግሥት ቁጥጥር ስር በመሆኑ የዚህን ዘረኛ አገዛዝ ፕሮፖጋንዳ ከመሆን አልፎ ለሕዝቡ በእውነት ላይ የተመሠረተ ተጨባጭ መረጃ ሊቀርብ አይችልም። ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያቃርኑ ጉዳዮችን እያባባሰ በዘር፤ በኅይማኖት፤ በቋንቋ…ወዘተ ልዩነቶችን እያሰፋ ማሕበራዊ ዝምድናን እያሳሳ ከብሔራዊ አንድነት ይልቅ ጎሠኝነትንና በማንገስ እርስ በርስ በማናቆር የራሱን ደሕንነት ማስጠበቂያ ናቸው።
በአሜሪካና በጀርመን መንግሥት አማካይነት ከቦንና ከዋሽንግተን የሚተላለፉ የአማርኛና ሌሎች የአገር ውስጥ ቋንቋዎች የሚተላለፉ ሬዲዎ ጣቢያዎች በከፍተኛ ባለሙያዎችና ልምድ ባካበቱ ሥመ ጥር ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች የተደራጁና ብዙ አድማጮችን ያተርፉ ሬዲዎ ጣቢያዎች ናቸው።
እነዚህ ሬዲዎ ጣቢያዎች ተደማጭነት ሊያገኙ የቻሉበት ዋናው ምክናያት በራሳችን ቋንቋ የሚተላለፍ ነፃ ራዲዎ ጣቢያዎች አለመኖራቸው ነው። ታዲያ እነዚህ ራድዎ ጣቢያዎች ነፃ ናቸው ባይባልም አድማጭ እንዳይሸሽ የየመንሥታቸውን መልካም ገፅታ፤ መስፋፋት፤ የፖለቲካ መስመርና የሥነ ልቡና ጫና በማሳደር እነሱ የጠሉት እንዲጠላ ለጥቅማቸው ያደረው እንዲወደድ ትንሽ ትንሽ እውነት እየቀየጡ በሥልጣን ላ ያለውን የሕወሓት/ወያኔን ዘረኛ አገዛዝ የጀርባ አጥንት በመሆን ሲያገለግሉ ሕወሓት እነዚህን መንግሥታት አንገቱን ሲያዞርባቸው እያስተካከሉ የመንግሥታቸውን ፍላጎት ከማሟላት ውጭ ለሕዝብ እውነተኛ መረጃ ማቅረብ አይቻላቸውም።
ሌሎች ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ዜና ማሰራጫዎች የኢትዮጵያን ጉዳይ ከብዙ ያልተጣሩ ነገሮች መካከል አንድ እውነት በመቀየጥ ባልተስተካከለ ሚዛን ስለሚያስተላልፉ የዓለም ሕዝብ የኢትዮጵያውያንን ረሓብና ሥቃይ ለማየት የሚችልበት አንድም ጭላንጭል የለም። ተዳፍኖአል። ይህ አፈና ዛሬ በረሓብ የሚረግፈውን ሕዝብ ሁኔታ እንዳይገለጽ ብቻ ሳይሆን አዲሱ ትውልድ እንዴት ከዚህ የረሓብ አዙሪት እንዳይወጣ መንገዶችን ደፍነው ረሓብ የኢትዮጵያውያን ዕጣ ፋንታ ሆነው ጸንተው እንዲኖሩ አድርገውታል።
ሕወሓት/ወያኔ እንደመንግሥታዊ ኃላፊነቱ ለዚህ ረሓብ መፍትሔ እንዳይፈልግ የሚከተለው የዘረኝነት ርዕዮት ለጥሩ ውጤት የሚያበቃው አይደለም። የትግሬ ነፃ አውጭ ግምባርን አስኳል አድርጎ በዘር የተደራጀ መዋቅራዊ አገዛዝ ቅድሚያ ለእኔ ዘር በሚል ስግብግብ ፍልስፍና አንድን ክልልና ዘር ያስቀደመ ሌላውን የአገሪቱን ሕዝብ በደረጃ ያስቀመጠ አገዛዝ እንዴት አድርጎ ከደረጃ አንድ /ክልል አንድ/ የተቀማጠለ ጥቅማ ጥቅም ቀንሶ ስምየለሽ /ደረጃ የለሽ/ ለሆነው ሰፊው ሕዝብ ይስጥ፤ ያካፍል?
በዚህ መንግሥት አስተሳሰብ የክልል አንድ ብሔረሰብ አባላት በመላው አገሪቱ ውስጥ የሚገኝ ሀብት፤ ሥልጣንና የቁጥጥር ሥራዎች ባለቤትና ደልዳይ ሆኖ የተረፈውን እንደደረጃው አከፋፍሎ ስም የለሽ የሆነው (ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች) ዘንድ እስኪደርስ ያልቃል። ጊዜው አልፎ ጀምበር ይጠልቅበታል።
ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የቆየው የሕወሓት ዘረኛ ሥርዐት የዜግነት ደረጃና የመብት ልዩነት ሕግ ሆኖ እየተሠራበት ያለ በመሆኑ ከእነሱ የተረፈውን እንኳን ለማግኘት ለገዥዎቹ ልዩ ውለታ ማስመዝገብ አለበት። ቢያንስ እንኳን ተገዥነቱን የሚያረጋግጥበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። በዚህ ደግሞ ረጅም ጊዜ ለ20 ዓመታት የቆየው የሕወሓት ትግሬዎች አገዛዝ ያረጋገጠው ነው። ይህንንም ተከትሎ የሚነጉደው እበላ ባይ ከቁጥር አንድ ዘረኞቹ እስከ መጨረሻው ዕርዳታ እህል ስፋሪው ድረስ በሙስና እንዲቆላለፍ ሥርዐቱ የፈጠረው ግዴታ ነው።
አንዳንዶች ርሓብን ከተፈጥሮ ክስተት ጋር ብቻ በማቆራኘት ያለውን የፖለቲካ ሥርዐት ከተጠያቂነት ነፃ በማድረግ ወደ እግዚአብሔርና ዕርዳታ ሰጭዎች ለልመና እንድንተጋ በማሳሰብ አቅጣጫ ለማስቀየር የሚሞክሩ አሉ። እነዚህ ሰዎች ሊገልጹት የማይፈልጉት ነገ ዝናብ በበቂ ሁኔታ ቢገኝ ሰው በረሃብ ይሞታል፤ የዝናብ መጠን ቢቀንስ ሰው በረሃብ ይሞታል፤ በዚህ መንግሥት ሰው ያልተራበበት ዓመት አለን? የ1997. ዓም ኑሮ ውድነትን ምን አመጥው? ሕዝብ በረሓብ እየረገፈ ሼክ ሞሐመድ አላሙዲን ወደ ግብፅ የሚልከው ሥጋ እየጭመረ እንጅ ሲቀንስ አይታይም። በአዜብ መስፍንና በሸሪኮቿ ከገበሬው በማዳብሪያ ዕዳ እየተዘረፈ የሚልኩት ጥራጥሬና ቅባት እህል ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም። ከዚህ ረሓብ ጋር የተያያዘው ሙስና ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ባለፉት 40 ዓመታት ካሪካችን በተለይ አሁን አገዛዙን የጨበጠው የቀድሞ የትግሬ ነፃ አዉጭ ግምባር ረሓብተኛን እያስጎበኘ ሩህሩሁ የዓለም ኅብረተሰብ የለገሰውን ምግብ እየቸበቸበ ጥሬ ገንዘቡን ፀረ ታንክ፤ ፀረ ሰው፤ ፀረ ድልድይ ፈንጂ መግዣ እንዳዋለው የዚህ ዘረኛ አገዛዝ ታሪኩ ብቻ ሳይሆን እንደመታውቂያ የሚገለጽበት ተግባሩ ነው። ይህንን በሚመለከት ከዕርዳታ እህል ሠፋሪው አልፎ ዕርዳታ ሰጭና አቅራቢው ያለውን የሙስና ሰንሰለት ለጊዜው እንለፈውና የዚህ ዘረኛ አገዛዝ ለሕዝቡ ያለውን የተቆርቋሪነት ባሕሪ እንመልከት።
የሕወሓት/ወያኔ አገዛዝ የመነሻ ታሪኩ በክልላዊ ስሜትና ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እራሳቸውን የተለን/የተበደልን ሆነን ሣለ ኢትዮጵያ ጨቁና ስለያዘችን ከዚህ አገዛዝ ተላቅቄ ነፃነቴን አውጃለሁ ብሎ የትግሬ ነፃ አውጭ ግንባርን መሪ ድርጅቱ አድርጎ ለረጅም ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር የተዋጋ ኃይል ነው። በነዚያም የፍልሚያ ዘመኑ የራሱ ባንዲራ /ሰንደቅ ዓላማ/ ክልል፤ ቋንቋ …ወ.ዘ.ተ. ለትግሬ መንግሥትነት የሚያበቁ ቀመር ሠርቶ ሲታገል የኖረ ከተመሣሣይ ተገንጣይ ድርጅት /ሕዝባዊ ግምባር አርነት ኤርትራ/ ሻዕቢያ በመሆን የኢትዮጵያን ወደ ሥልጣን ሲቃረቡ ሌላውን ተገንጣይ ኦነግን በመጨመር አሥመራንና አዲስ አበባን ተቆጣጠሩ።
በዚህ የትግል ሂደት ወያኔ ሻዕቢያና ኦነግ የኢትዮጵያን ቋሚና ጊዜያዊ ታሪካዊ ጠላቶችን እየፈለጉ ከጎረቤት ሶማሌ እስከ ፀረ-ኮሚኒስት ኃያላን ድረስ ዕርዳት እያፈነፈኑ የጠለትን ፍላጉት የራሳቸው አድርገው የኢትዮጵያ ጥላቶች እጀታ በመሆን ኢትዮጵያን ሲያፈርሱ፤ ሲያደሙ መኖራቸው የተወቀ ነው። ሲወጉት የነበሩትን አገር፤ የሚጠሏትን ኢትዮጵያ፤ የማይውዱትን ሕዝብ…ወ.ዘ.ተ ገዢ ሆኑ። ያቺ ጨቆነችን፤ ገዛችን፤ አሰቃየችን የሚሏትን ኢትዮጵያ በእጃቸው ወደቀች። የኢትዮጵያን መንግሥት ወክሎ ይዋጋቸው የነበረው ወታደራዊ ደርግ ታላቋ ሶቪየት ኅብረት ስትፈራርስ በግሉ ጸንቶ መቆም ባለመቻሉ እንኳን ለፍልሚያ እራሱን ለመጠበቅም ትንፋሽ በማጣቱ ሠራዊቱም መሪ አጥቶ መበተኑ የወያኔን ድል እጥፍ ድርብ ሆነ። በደስታ ሰከሩ ምን እነሱ ብቻ መላው የኢትዮጵያ ጠላት ወያኔንና ሻዕቢያን በመርዳታቸው ያደረጉትና ያስደረጉትን ለየሕዝባቸውና መንግሥቶቻቸው ዲፕሎማሲዊ ግዳይ ጣሉ።
ወያኔና ሻዕቢያ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጠንከር ያለ አቋም ባላቸው ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ተቋማት ላይ ጦርነቱን አፋፋመ። አማርኛ ተናጋሪውና የአዲስ አበባ ሕዝብ ከፕሮፖጋንዳ እስከ አንቆ ገደል እስከመወርወር፤ እንደ ቀይ ሽብር በሌባና በነፍጠኛ ስም ፈጸሙ። የኢሠፓ፤የአኢወማ፤ የአኢሴማ፤ መኢሰማ፤ መኢገማ የሕንጻ ኮንስትራችሽን … ወ.ዘ.ተ ንብረት እንደጠላት ንብረት ተቆጥሮ በዘረፋ መልክ ወደ ትግሬ ተጋዘ፤ የሀገሪቱ ታሪካዊ ቅርስ ለውጪ ገበያ ቀርቦ ባወጣው ዋጋ ያለከልካይ ተቸበቸበ፤ ተመዝረበረ። የመከላከያ ሠራዊት ንብረቱማ ባለበት ወደመ የባሕር ኃይሉም መርከቦቹም ለጫረታ ቀረቡ አጠቃላይ አገሪቱ ጭምር።
በዚህ የኢትዮጵያ ውድመት ሂደት ሕወሓትና ሻቢያ የተጫወቱት ሚና በዚህ ለመግለጽ አስቸጋሪ ስለሚሆን የአምባቢያን ትኩረት ሊሆን የሚገባው ወያኔ በረሓብ ለሚሰቃየው ሕዝብ በየትኛው ወገናዊነት ተቆርቋሪ ሊሆን ይችላል። ከላይ በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ተፈጥሮ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰውን ችግር በአንድ በኩል አስቀምጠን ወያኔ የሚመራበት ፖሊሲ፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ያለውን ጥላቻ ግምት ውስጥ አስገብተን ስንመዝነው የትኛው ችግር በቅድሚያ ይቀረፍ? ከለጋሾች የሚገኘው ዕርዳታ በጨካኝ አረመኔ ወያኔዎች እጅ ገብቶ እንዴት ለረሓብትኞች ሊከፋፈል ይችላል? እነዚህ ጥያቄዎች ከወያኔ ባህሪ አኳያ ሲታዩ የወያኔ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው ተቆርቋሪነት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም።
በትግሬ ጠቅላይ ግዛት በፍልሚያ ላይ እያለ በረሓብተኞች ላይ ይፈጽም የነበረውን ተግባር እንዴት በኢትዮጵያ ረሓብተኞች ላይ እንዴት ፀባዩን ይቀይራል? ተብሎስ ይታሰባል? በ20 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ ከሕዝብ ያገኘው ወዳጅነት አለወይ? ለዚህ ጥያቄ መልስ የግንቦት 1997 ምርጫ በአጭሩ መልሶታል።
ከግንቦት 97 በኋላ በርካታ የጥላቻ ተግባር ተከናውኗል። ቁጥሩ በወል ያልታወቀ ሕዝብ ተገድሏል፤ ከመኖሪያው፡ ከሥራው፤ ከትምህርት …ወዘተ ተፈናቅሏል። የታሰረው የተሰደደው ሕዝብና የችግሩ አስኳል የሆነው ወያኔ ቀድሞ ከነበረበት ሕዝባዊ ጥላቻ ምን ያህል እንደጨመረ እንዲሁም ኑሮው ምን ያህል እንዳሻቀበ ለግምትም አስቸጋሪ ነው።
መንግሥትና የሚመራበት አገዛዝ መርሑ ከሕዝብ ጋር ሊያዋህደው ቀርቶ የሚያቀራርበው አንዳች ሕዝባዊ መስህብ የለውም። ከሕዝብ እምነትና ፍላጎት የራቀ ነው። ከእንግዲህ በመንግሥትንት ሥልጣን ሊቆይ የሚችለው በኃይል እንዲሁም በልምድ ያካበተውን ረሓብን አንዱ የመግዣ መሣሪያ በማድረግ ነው። ወያኔ ክሥልጣን ቢወርድ ከሕዝብ ሊቀላቀል አይችልም። ያፈሰሰው ደም፤ ያፈረሰው ቤተሰብ አገር፤ ያሰረው፤ ያፈናቀለው ያሰደደው ሕዝብ ለፍርድ ያቆመዋል። ለዚህም ወያኔ በየደረሰበት የዓለም ክፍል ያሉ ኢትዮጵያውያን ወያኔን እየተከታተሉ በሰላማዊ ሰልፍ መውጫ መግቢያ ያሳጡት።
በኢትዮጵያ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በወያኔ በሼክ አላሙዲን ቁጥጥር ሥር የዋለና በመለስ ዜናዊ ሚስት አዜብ መስፍን (ጎላ) እና የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያከማቹት ንብረት እንዲሁም ከዚህ የተረፈው ለህንድና ለቻይና ማሌዥያ … ወ.ዘ.ተ. እየተቸበቸበ ነው። እዚህ ላይ የቻይናና ህንድ የመሳሰሉት አገራት ለምን ተነሳ የሚል ጥያቄ ሊያስከትል ይችላል። ነገሩ እንዲህ ነው። ወያኔና የኢትዮጵያ ሕዝብ እሳትና ቤንዚን ናቸው ብለናል። እሳትና ቤንዚን በሰላም ሊኖሩ የሚችሉት ሁለቱም እንዳይገናኙ እጅግ ጠንካራ ግድግዳ ሲኖር ነው። ወያኔ ምዕራባውያንን በግሎባላይዜሽን፤ በፀረ ሽብር አገሩን አዋርዶ በመግዛቱ ሲደግፉት ሕንድና ቻይናን በጥቅም የአገሪቱን አንድ አምሥተኛ መሬት በመሸጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ጠላት (ጠንካራ ግድግዳ) በመፍጠር በሚገጥመው ሕዝባዊ ጦርነት የፍልሚያ ቀጣናውን በማስፋት ከቻይና፤ ከሕንድ፤ ከገልፍ ዓረብ ባለሃብቶች አጋዥ ኃይል አግኝቷል።
በዚህ የመሬት ሽያጭ አዲስ ተፈናቃይ፤ አዲስ ረሃብተኛ ተፈጥሯል። የመሬት ሽያጭ መቼ ይቆማል? መፈናቀል መቼ ይቆማል? መልስ የለም። ረሓብ መቼ ይቆማል? ተመሳሳይ መልስ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ረገጣ ለተ.መ.ድ ቢቀርብ ቻይና በኢትዮጵያ የሉዐላዊነት ጥያቄ ላይ ወያኔን ደግፋ እንደምታከሽፈው ጥርጥር የለውም። አሜሪካና አጋሮቿም ቢሆኑ ጠንካራ ኢትዮጵያን ማየት አይፈልጉም። በዚህም ላይ የሕንድና የቻይና ገበሬ አርሶ ኢትዮጵያን ረሓብተኛ ሲመግብ ማለት “ከአይጥ ቤት ብቅል” መሻት ነው። ለሌላው ኢትዮጵያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚባለውም ከፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ የዘለለ ትርጉም አይሰጥም። በተለያየ ጊዜ የተከሰተው የአየር ፀባይ ለውጥ፤ ድርቅ፤ ጎርፍ፤ ብርድ፤ የአንበጣ መንጋ… ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉት የተፈጥሮ ችግሮች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ያሉ ናቸው። የውኃን ችግር በተመለከተ ያደጉት አገሮች ብቻ ሳይሆን ገና በማደግ ላይ ያሉትም ቢሆኑ የዝናብን የከርሰ ምድርን ውኃ እንዲሁም ፍሳሽን በጥቅም ላይ በማዋል የውኃ ፍጆታን ቀደም ብሎ በመተንበይ የዓየር ፀባይን ለውጥና ፍላጎትን አስተካክለው ሲያከፋፍሉ የእርሻና የኢንዱስትሪ ሂደቱ ሳይናጋ የሚጓዝበት ሁኔታ እንዳለ እያየን ነው። እነዚህ አገሮች ዓመታዊ የዝናብ መጠንና የውኃ የትነት ከኢትዮጵያ ያልተሻሉ በርሓማ አገሮችን ማለታችን ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በውኃ ሀብት ዓመታዊ የዝናብ መጠን እንዲሁም በረሓማ ቦታዎችን ስፋትና የውኃ ትነት ጋር ሲነፃጸር ከበርካታ አገሮች የተሻለ ሁኔታ መኖሩ ማንም የሚፈርደው ነው። በእርግጥ በዚህ ረገድ ሊኖር የሚችለው ችግር የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች በሙሉና ጎረቤት ያልሆነችው ግብፅ የዐባይ ተጠቃሚ በመሆናቸው የኢትዮጵያን ዕድገት መፃረራቸው አይቀሬ በመሆኑ ከውኃ ችግራችን አንዱ ነው። ያም ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ በውኃ ጥም እያለቀ እኛ በውኃ ዋና እንራጭበት ቢሉ የማይሆን ነው። ውኃው በግድም በውድም ሁሉም መጠቀም አለበት።
ውኃ ለማንኛውም ሕይወት አስፈለጊ እንደመሆኑ ሁሉ ለእርሻው ኢንዱስትሪው ሁሉ ያለ ውኃ የማይንቀሳቀስ በመሆኑ ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው። ያለ በቂ ዉኃ ዕድገትም ልማት የማይቻል ጉዳይ ነው። ቢቻልም እጅግ አድካሚና ኪሣራውም ከባድ ነው። የሕዝብ ቁጥር አደገ ስንል የውኃ ፍላጎትም እንደሚያድግ አጠያያቂ አይደለም። በውኃ መሬትን ከማልማታችን በፊት የመሬት ይዞታ ዋስትና ማረጋገጥ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም። በኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ ደግሞ መንግሥት በተለውጥ ቁጥር የይዞታ ባለቤትነት የመሬት ሥሪቱም ተለዋዋጭ ነው። ዓፄ ቴውድሮስ “ሲሦ ለአንጋች፤ ሲሦ ለቀዳሽ፤ ሲሦ ለአወዳሽ” የሚለውን ሥርዐት ለውጠው ለራሳቸው አገዛዝ በሚመች መንገድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናቱን ቁጥር በመቀነስ እንዳሻሻሉት ታሪክ ይነግረናል። በዳግማዊ ዓፄ ሚኒሊክም በዘመነ መንግሥታቸው የመሬት ሥሪት ለውጥ በሰፊው እንደነበር ይታወቃል። በተለይም ባላባቶቹ ሥር እንደነ ጂማ አባጂፋር የቆሮ ሥሪት፤ የነ ንጉሥ ካኦ ጦና አስተዳደር የአውራጃና የወረዳ ባላባቶች ከማዕከላዊ መንግሥት ጫና የአዳዲስ ከተሞች ምሥረታና ሠፈራ ቀደምትነት የነበረውን የመሬት ሥሪት ለውጥ ታይቶበታል።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም በተለይ ዘመናዊ እርሻና ኢንዱስትሪው ገና በመቆጥቆጥ ላይ ስለነበር ከዚሁ ጋር የተነሣው የመሬት ፍላጎት ሰዎችን እያፈናቀሉ ዘመናዊ እርሻን ማስፋፋት በመጀመሩ መሬት ይዞታው አዲስ ሥሪት የፈጠረና ሕዝቡንም ያስቆጣ ጉዳይ መፈጠሩ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው። (የቦሎቄ እርሻን ያስታውሷል)
በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የየካቲት 25/67 ምሬት ይዞታ አዋጅ ከሁሉም በተለየ መልኩ ከሁሉም የነበረ ሥር ነቀል አዋጅ መሬትን ከግል ይዞታ ወደ መንግሥት ይዞታ የለወጠ፤ ለጭሰኛው ፋታ የሰጠ ቢሆንም የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ አላሳደገውም። አገሪቱንም ከረሓብ አላወጣትም። የጭሰኛውን ሕይወት በመጠኑ ለውጧል፤ ዋስትናም የሰጠ ነበር። የእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት በገሬው ምርት ላይ የነበረው የግዥ ተፅዕኖ የተዛባ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ሥሌቱም ቀድሞ ጭሰኛው ለባለእርስቱ ያካፍል የነበረው ምርት እና ለእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጠውን በማወዳደር ነው። የመንደር ምሥረታ፤ የእርከን ሥራ፤ መሠረተ ትምህርት፤ ደን ልማትና አፈር ጥበቃ ከዚሁ መሬት ይዞታ ጋር ቁርኝት ነበራቸው። በክፉም በደግም የሚታዩ ናቸውና!!
ወታደራዊ ደርግን የተካው ሕወሓት/ወያኔ እና ሻዕቢያ ሥልጣን ከያዙከያዙበት ጊዜ ጀምሮ የምሬት ይዞታው ለረሓቡ ያበረከተው አስተዋፅዖ ምን እንደሚመስል እንመልከት። የረሓቡ መጠን በሀግራችን የቆዳ ሥፋትና የሕዝብ መጠን የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንደሆነ፤ የረሓብተኛው ብዛት ከቀድሞ ጋር ሲነፃፀር በኤርትራ ከመረብ ምላሽና ከቀድሞዋ ትግሬ ክፍለ ሀገር በስተቀር እየጨመረ እንጂ የቀነሰበት ጊዜ አይታይም። ኤርትራና ትግሬን ያላካተትኩት አደጉ፤ ተመነደጉ ነው እንጅ ምንም ዐይነት መርጃ የተደበቀ በመሆኑ ነው።
የመሬት ይዞታ ለውጥም ከቀድሞዎቹ ለውጦች በአሰቃቂ ሁኔታ የተለወጠበት ሁኔታ ይታያል። በተለይም በዐባይ ተፋሰስ ላይ የሰፈረው አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ የመሬት ይዞታ ለውጥ ተደርጎ አዲስ የመሬት ሥሪት (ሽንሸና) እንደተደረገ የሚዘነጋ አይደለም። የትግሬ ክ/ሃገር ያለው መሬት ይዞታ ከሌላው በተለየ መልኩ እንደሚተዳደር፤ በደርጉ የተወረሰ የከተማ ቦታ ለቅድሞዎቹ ባለቤቶች እንደተመለሰ፤ በልማትም ሆነ በመስፋፋት በኩል የሚደረገው ሩጫ ገሐድ የወጣ እውነት ነው። በሕወሓት የመሬት ይዞታ አሠረር በግልጽ የሚታወቅ ሳይሆን በሥውር ለአንድ ዘርና ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት የበላይነትን እንዲያመች የተደረገ ነው። በፖለቲካ ድርጅት ሕወሓት/ኢሓዴግ፤ በዘር ትግሬ፤ በግለሰብ፤ ሼክ ሞሓመድ አላሙዲን የበላይነቱን ይይዛሉ። እዚህ ላይ አንባቢያን በጥንቃቄ ሊጤኑት የሚገባ ጉዳይ በማንኛውም የአገሪቱ ግዛት ከፍተኛ የልማት ተቋም እንደግለሰብ ከሆነ በትግሬ ብሔረሰብ አባላት ቁጥጥር ሥር ነው። እምቢ አይባሉም አለቆች ናቸው። የትግራይ ልማት ማሕበር ንብረት ዛሬ ለእያንዳንዱ የብሔረሰቡ አባላት ቢከፋፈል እንኳን ጠቀም ያለ ድርሻ ያገኛሉ። ይህም በግልጽ ከሚታወቀው ማለት ነው።
የሼክ መሐመድ አላሙዲን ጉዳይ ያየን እንደሆን ቀደም ሲል በቀኃሥ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ መሬት ይዘዋል ተብለው ይወቀሱ ከነበሩት ክቡር ራስ መስፍን ስለሽ፤ ራስ አሥራተ ካሳ ጂማ አባ ጂፋር …ከነበራቸው ይዞታ የበለጠ ነው። የማይገመት የማይታለም። የሼኩ ንብረት የወያኔ ሚሥጥራዊ ሽፋንና ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች የሚሣተፉበት ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ሂደት እንደሆነ በይፋ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል አይደለም። የሥጋ ዋጋ ይህንን ያህል ሲወደድ ከሼኩ ንግድ አንዱ የኢትዮጵያን ሥጋ ወደ ግብፅ መላክ እንደሆነ ይታወቃል። ሼኩ ለኢትዮጵያ ረሓብ፤ ለመብት ረገጣው፤ ትልቅ ድርሻ አላቸው። አትሌቶችን ይረዳሉ፤ ሙዚቀኞችን ያሳክማሉ እየተባለ በመገነኛ ብዙኃን ዝናቸው ቢሰራጭም የማስታወቂያ /Advertisement/ ሥራ እየተሰራ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። በጥቂት ፍርፋሪ ዝና ለማትረፍ ይሚደረገው ሙከራ ከሚዘርፉት ጋር ሲተያይ ምንም ማለት አይደለም። ያም ቢሆም እውነት የሚረዱት ገንዘብ ለተባለው ሰው በሥራ ላይ ይውላልን? ከፕሮፓጋንዳ በስተቀር ማረጋገጫ የለንም። ቀጥሎአል። ሼኩ ለአገር የሚያስብ ቢሆን ወደ ውጭ የሚልከውን ምግብ ቢያቆምና ለአገር ውስጥ ፍጆታ ቢውል ባመሰገንነው ነበር። የሚያፈናቀለው፤ የሚሰደደው እንዲሁ።
ሼኩ ከመሬት ይዞታ፤ ከረሓብ፤ ክሙስና፤ ካካባቢ ብክለት ጋር ያላቸው ቁርኝት እንደተጠበቀ ሆኖ በፖለቲካው መስክም እጃቸውን በማስረዘም እስከ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድረስ ዘልቀው የእኛን የጭቆና በሰፊው ይወራል። በዐረብ ሊግ እንኳ እልፍኝ አስከልካይንቱ ቢቀርባቸው አጋፋሪነት አይከለከሉም። ከሳዑድ ዐረቢያ ንጉሣዊያን ቤተሰብ ያላቸው ባለሟልነት፤ ከዳች ነገሥታት ያገኙት ሽልማት፤ ሂላሪ ክሊንተንን ለማስመረጥ ያፈሰሱት ገንዘብ (እውነት ከሆነ) የሼኩ እጅ እርዝማኔ የጭቆና ቅንበራችን ከብደትንና የመከራ ዘመናችን እርዝመት የሚያመላክት ነው።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ እየተበደሩ ሸራተን አዲስ ሆቴልን እንዳሳነጹ ስንሰማ ተገርመን ነበር። ለመሆኑ ምን ያህል ገንዘብ ወደ አገር አስገቡ? ሙዚቀኛ አሳከሙ ይባላል፤ የዳነ አይታይም ምስጋናው ግን ይጎርፋል፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እየረዱ የትም አልደረሰም። በዩናይትድ ስቴት የሚገኘው የሰሜን አሜሪካው የኢትዮጵያውያን የባሕልና የስፖርት ማሕበር የእሳቸው ዕርዳታ ሲገባበት ወደ መፈረካከሱ እያመራ መሆኑ ተዘግቧል። እውን ይህ ገንዘብ የእሳቸው ነው? ልግስናቸው እንደደርግ አዋጅ ሳይታሰብ የሚፈስ፤ ተክለ ማንነታቸው እንደወያኔ በፕሮፓጋንዳ ብቻ የተገነቡ ሆነው ወደ ውስጥ ገባ ሲሉ ለወያኔ ግምጃ ቤትነት የተመረጡ ሆነው እናገኛቸዋለን። ዕርዳታቸውም ሆነ ገንዘባቸው የተባረከ አይደለም። የተባረከ ገንዘብ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ቢቀርበት የአፍሪቃ ዋንጫ መሆን ባልተሳነው ነበር። ለዚህ ነው በርካታ ሰዎች ሼኩ የሚረዱት የገንዘብ ቁጥር ነው ወይንስ ቁጥጥር? ጥያቄ የሚጠይቁት። መቀሌን ሲጎበኙ በእያንዳንዷ እርምጃ አንዳንድ የልማት ተቋም ይለግሳሉ። ይህ ልግስና ሼኩና ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚሠሩት የሸር ድራማ እንጅ የደግነት ውጤት አለመሆኑን የሚጠራጠር ይኖር አይመስለኝም።
ከሼኩ ስጦታ (ልግስና) ሁሉ የሚያስገርመኝ የውስጥና የውጭ ዓለም አቀፍ ከያኔያንን (የኪነት ባለሙያዎችን) በታላቁ ሆቴላቸው ሸራተን አዲስ ሲያስተናግዱ ሲሸልሙ ሲያሽሞነምኑ ለአንድ የኔ ብጤ ረሓብተኛ ቁራሽ ዳቦ ለገሱ ሲባል አልሰማሁም። የሰማ ካለ ቢጠቁመኝ እታረማለሁ። እንዲያውም ምግብ ከረሓብተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ከሕፃናት ጉሮሮ እየነጠቁ ወደ ውጭ ሲልኩና ሲከብሩበት ነው የሚስተዋሉት። ይህ ጭካኔ ደግሞ አረመኔነትን የሚገልጽ ነው።
ዜጎች ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት የሚገባ ነገር ሼኩና ወያኔ ያላቸው ግንኙነትና ሚሥጥራዊ ተልዕኮ ምንድን ነው? አንድ ወቅት ከግብፅ መንግሥት ጋር ተጣልተው ሲያማርሩ ነበር በኃላ ሰምና ወርቅ ሆኑ። በሙስሊም አሸባሪነት ጎራም ተጠርጥረው ብዙ ክትትል ሲደረገባቸው ከርሞ ውጤቱ ምን ላይ እንደደረሰ ተከታታዮቹ እንካን ሳያውቁት ፋይሉ ተዘጋ።
ለሀገራችን ረሓብ እንዲባባስ ከወያኔ ቀጥሎ ትልቅ ድርሻ ያበረከቱት ሼክ የንግድ ሥራቸውም ቢሆን በሸርና ደባ ላይ የተመሠረተ፤ በማጭበርበር የታጀበ እንድ አገራችን አባባል “ከጅብ ቆዳ የተሠራ ከበሮ ሲመቱት እንብላው… እንብላው ይላል” በሚለው ቅኝት የተቃኘ ንግድ እንደሆነ በርካታ ማስረጃ አለ። በእኔ አመለካከት ሼኩ የወያኔ ግምጃ ቤት፤ የኢትዮ-ዐረብ አገናኝ መኮንን በተጨማሪም አገር አሻሻጭ ደላላ ይመስሉኛል። የሚባለው እውነት ከሆነ አሩሲ ክፍለ ሀገርን ለእራሳቸውና ለሳዑድ ዐረቢያ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ደልለው አሻሽጠዋል፤ ከሁለቱም ወገን ጥቅም እንዳላቸውም በሰፊው የሚነገር የሰነበተ ወሬ ነው። ለምለሚቱ አሩሲ ያፈራችውን እሸት ለሳዑድ ዐረቢያ ንጉሥ ገጸ በረከት ሼኩ አቅርበው በሳዑዲ ዜና ማሠራጫ ከጨረቃ እንደመጣ ንጥረ-ነገር ጉድ ሲባል ሰንብቷል። እኔ ያሳሰበኝ መሬቱን እየተነጠቀ እንዲፈናቀል የተፈረደበት የአሩሲ ገበሬ ከነቤተሰቡ በረሓብ መርገፉ ነው።
ኢትዮጵያ ዕርዳታ ከምታገኝባቸው ምክናያቶች አንዱ በኤች አይ ቪ ኤድስ የሚለገሰው ነው። የዚህ ዕርዳታ የበላይ ኃላፊ ሆነው እራሳቸውን የመደቡት የውልቃቷ እመቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ናቸው። ወይዘሮዋ የሕወሓት ተውጊ የነበሩና፤ የሰብዓዊ መብት ታጋይ፤ የውያኔ ፓርላማ አባል፤ የአፍሪቃ ኤች አይ ቪ ኤድስ አባል የኢትዮጵያው ተጠሪ፤ ብሔራዊ የአእምሮ ደሕንነት አመራር፤ የትግራይ ልማት ማሕበር አመራር፤ የሜጋ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት፤ የኤፈርት፤ የውልቃይት… ወዘተ ናቸው። እንደ ኃላፊነታቸው ሁሉ ሀብታቸውም እንደምደር አሸዋ የበዛ ነው። የሚያሳዝነው ይኽ ሁሉ ሥልጣንና ሀብት እያላቸው የኤች.አይ.ቪው እንኳን ለሕመምተኛው አልተውለትም። ወደ ለጋሽ አገሮች ባንክ በስማቸው የተከፈተው ሚሥጥራዊ ባንክ በሼኩ በኩል ያሾልኩታል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ታማሪዎች በረሓብ (ጠኔ) መማሪያ ክፍል እየወደቁባቸው የተቸገሩ መምህራን ገንዘብ ከኪሳቸው እያዋጡ ለመመገብ ጥረት ቢያደርጉም ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ የድረሱልኝ ጥሪ ሲያሰሙ፤ ሻሸመኔ ሕፃናት በርሓብ እያረገፉ ሐኪሞች የድረሱልኝ ጥሪ ሲያሰሙ ሕወሓት/ወያኔ/ መቀሌ በሀገሪቱ ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው እጅግ ዘመናዊ ስታዮም ያንጻል። ይህ ነው የተባለ ደህና የእግር ኳስ ክለብ እንኳን የለም። የአዳማንና የሐረርጌን አንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦችን ያስታውሷል!! ይህ ብቻ አይደለም የመቀሌው ዘመናዊ ዓለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፍያም የፈሰሰበት ገንዘብ ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ ሲነፃጸር ለጥገናና ለእክብካቤ የሚወጣው ወጭ እንደሚያመዝን አንዱ የአደባባይ ሚሥጥር ነው። በዚሁ ከተማ የተዘረጉት ዘመናዊ አስፋልት መንደዶች ብዛትና ጥራት ከተሽከርካሪዎች ጋር ሲመጣጠን ከአሥር ዓመት በኃላ ለሚመጣው ትውልድና ለ2020 ለሚገዙ አውቶመቢሎች የተሠራ ነው። የመቀሌ ዘመናዊ ታላላቅ ሕንፃዎችም የነዋሪ እጥረት ስለገጠማቸውና ኪሣራ በማስከተሉ ለጊዜው የሕንፃ ግንባታው አትራፊ ወደሆነችው አዲስ አበባ ከተማ እየተዛወረ ነው። የመቀሌ ሆስፒታሎችም ቢሆኑ አዳዲሶቹ ሲጠናቀቁ የበሽተኛ ዕጥረት ያማጋጠሙ ሥጋት አይቀሬ ነው። ታዲያ ይህ ሁሉ ያልተመጣጠነ ግምባታ ከረሓብተኛው ከሕፃናት ጉሮሮ እየተነጠቀ መሆኑ የሚጠራጠር የለም። እነዚህ ግምባታዎች ውጭ ባንክ ከማስቀመጥ የተሻለ አማራጭ አድርገን ብንወስደው አንዳንዶቹም ተቋማት ከአሥር ዓመት በኋላ የምንጠቀምባቸው ቢሆኑም ሌላው ቢቀር የዐይን ማረፊያም ይሆናሉ።
የሀገራችን ችግር ዘርፈ ብዙ ነው። የረሓቡ ጉዳይ ከማንም ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ታድያ ምን ይደረግ? በግል፤ በጋራ፤ በማኅበር በዕድር፤ ባገር ውስጥ በውጪ ያለው እንዴት ይረዳዳ? ሐሣብ ያፍልቅ? ዕቅድ ይንደፍ? እነኝህ ጥያቄዎች በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ ሆኖ የተገኘ ሁሉ እራሱን የሚያዞርበት ፈታኝ ጥያቄ ነው። አንዳንድ ወገኖች ለውይይት እንኳን እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አታንሱብኝ፡ በሰላም ልሰብትበት እስከማለት ደርሰዋል። በእኔ በኩል መፍትሔም መልስም አይሆንም። ዛሬ ዲያስፖራው አገሩን ለመርዳት ቢያስብ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች፤ በቀይ መስቀል፤ በወርልድ ቪዥን፤ አለያም በሚሥጥር ወያኔ እጅ እንዳይገባ ተዋውሎ ነው። የድሬዳዋው ደቻቱ ያንን ያህል ሰው ሲጨርስና ሲያፈናቅል ወገናችንን ለመርዳት አንዱና ዋነኛው ጋሬጣ ወያኔ እንደነበር አስታውሳለሁ። በዚህም የተነሣ ዛሬ የሕዝባችን በረሓብ መሞት መሰቃየት የሚሰማን ሁሉ በጋራ የሚያስማሙንን ጥቂት የመፍትሔ ሐሳብ ልበልና ጽሑፌን ላብቃ።
በመጀመሪያ ረሃብ ዘር ኅይማኖት ቋንቋ ክልል የፖለቲካ … ወ.ዘ.ተ. የማይለይ በመሆኑ የዕርዳታ ዕደላው መሥፈርት ሳይኖርብት ሊከናወን የሚገባው በመሆኑ ዕርዳታ ሰጭው (ለጋሹ) ልዩነት ባያደርግም ተቀብሎ የሚያከፋፍለው ወያኔ በዘረኝነት የተካነ በመሆኑ ከዕርዳታ ነክ ጉዳዮች እንዲወጣ ማድረግ ካልሆነም ዕርዳታን በአግባቡ ለመጠቀም ወያኔን ማስወገድ።
ረሓብን ለማስወገድ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀን የውኃ አጠቃቀማችንን በማሻሻል የእርሻ ምርትን ማሳደግ ከአንድ ጊዜ በላይ ማምረት ሲቻል በመሆኑ ትኩረት ሲሰጥበትና የኢትዮጵያ ውኃ ቁፋሮ ሥራ በትግራይ ልማት ማሕበር ፈቃድ ሰጭነትና ቁጥጥር ሥር መማከሉ ቀርቶ ከግለሰብ ጀምሮ ነፃ ውኃ የመውጣት የመገደብ የማከፋፈል መብት ማክበርና ወደ ትግሬ የተወሰደው የአዋሳ ውኃ ማሰልጠኛ ተቁም ወደቦታው ተመልሶ ሌሎችም ማሠልጠኛዎችንም ማቋቋም። ወያኔ ይህንን ሊቀበል አይችልም። ካልሆነ ወያኔን ማስወገድ።
ከረሓብ ለመላቀቅ አስተማማኝ የመሬት ይዞታ ባለቤትነትን ማረጋገጥ፤ ለረጂም ጊዜ መንከባከብና ዛፍ በመትከል፤ አፈሩን ለመጠበቅ፤ የዐየር ፀባይ ለውጥን ለመቋቋምና ዘላቂ ልማትን ለማቀድ በመሬቱ ላይ ከፍ ያለ ካፒታል፤ ዕውቀት፤ ጉልበት በማፍሰስ ዘላቂ ልማትን ማምጣት አንዱ ነው። ይህ ወያኔ እያለ የማይታሰብ ነው። መሬት ለባዕድን መሸጡን፤ የፖለቲካ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ለፈለገው የሚሰጥ የሚወሰድ፤ አንዱን ጎሣ ከሌላው፤ ክልልን ከክልል ግጭት መፍጥሪያ እንደቻይና ሕንድ የመሳሰሉትን ለወያኔ ወዳጅ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ማፍሪያ በመሆኑ ውያኔን ማስወገድ አለያም ረሓብን በፀጋ መቀብል ነው።
ርሓብን ለመግታት ከመንግሥት ከወያኔ ዘረኝነትን፤ ሙስናን፤ ጥላቻን ባንዳነትን፤ መሬት ለባዕዳን መቸብቸብን፤ ማፈናቀልን፤ ማሰደድን የመሳሰሉትን እኩይ ባሕሪ ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ቀጠሮ ማቆም አለበት። ይህ ደግሞ ወያኔ ከሣጥናዔል ድቁና የተቀበለበት ክህነቱም ቁርባኑም በመሆኑ ሊለቀው ስለማይችል አማራጩ መወገድ ብቻ ነው። በምትኩም ረሓብን ለመዋጋት የሚያስችል መንግሥት ማቆምና መታገል ግድ ይላል።
ሕዝቡም የረሓብን አዙሪት ለመጣል የጎሣ የቋንቋ የኀይማኖት ልዩነት መጋረጃን ቀዳድዶ በመጣል በአንድነት ንብረቱን፤ አውቀቱን፤ ጉልበቱን በማስተባበር በብሔራዊ መግባባት የሥራ ቅደም ተከተል ዘርግቶ በአፋጣኝ መንቀሳቀስ አለበት። ይህ እንዳሆን ወያኔ የሠራው ክፍፍል እንቅፋት ስለሚሆን ወያኔን ማስወገድ ተቀዳሚ ተግባሩ ሊያደርገው ይገባል።
ዕርዳታ ሰጭዎች (ለጋሽ አገሮች) የሚሰጡት ዕርዳታ ረሓብተኛውን ከመታደግ ይልቅ ዘረኝነትን ጭቆናን የፖለቲካ ድጋፍን ማስፋፊያ መሆኑን አውቀው ወያኔን ከዕርዳታ አከፋፋይነት ማስወጣት እምቢ ካለ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲሰላፉ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ፤ ለዚህ ተግባር ችሎታና ብቃት ያላቸው ዜጎችን ማትጋት።
ረሓብን ለመዋጋት ቅድሚያ ወያኔን ለማስወገድ መነሣት ይህንን ካልተቀበልን ረሓብንና ውርደትን ተሸክሞ በፀጋ መኖር ነው። እንደእኔ ወያኔን አስወግደን ረሓብን ለመዋጋት ጊዜ ሣንሰጥ እንነሳ እያልኩ እሰናበታለሁ።
በሌላ ጽሁፍ እስክንገናኝ ቸር ይግጥመን!!
ተዋናይ፣ ከቫንኩቨር ካናዳ!!!