የኤርትራ ተቃዋሚዎች የስደት ፓርላማ ለማቋቋም ተስማሙ
(የማነ ናግሽ፥ ሪፖርተር)
የኤርትራ ተቃዋሚዎች ጥምረት (ኪዳን) ሰሞኑን በአዲስ አበባ ባካሄደው ጉባዔ፣ የስደት ብሔራዊ ሸንጎ (ፓርላማ) ለማቋቋም መወሰናቸውን አስታወቀ፡፡ ይህንን የሚያመቻች ብሔራዊ ኮሚሽንም ተሰይሟል፡፡
አሥር ተቃዋሚ ኃይሎችን ያካተተውና የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ኪዳን በመባል የሚታወቀው ጥምረት፣ ከኤርትራ ሲቪል ማኅበረሰቦች ጋር በጋራ በመሆን ከሐምሌ 24 እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2002 ዓ.ም. ያካሄደው ብሔራዊ ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡
ይህ ‹‹ብሔራዊ ጉባዔ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ›› በሚል መሪ ቃል ከአንድ ሳምንት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ቄራ ካምፓስ) የተካሄደው ኮንፈረንስ፣ ከ330 በላይ ኤርትራውያን የተሳተፉበት ሲሆን፣ ከኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ኪዳን ውጭ ያሉ ተቃዋሚ ኃይሎች፣ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የኤርትራ ሲቪል ማኅበራት ተወካዮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የወጣቶችና የስደተኞች ተወካዮች እንደተሳተፉበት የብሔራዊ አመቻች ኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት መግለጫ ያመለክታል፡፡
የብሔራዊ ኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ትናንት በሒልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ብሔራዊ ጉባዔው በአንድ ዓመት ውስጥ የስደት ፓርላማ ለማቋቋም ወስኗል፡፡ ይህንን የሚያመቻች 53 አባላት ያሉት ብሔራዊ ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡
የቋንቋና የብሔር ጥያቄም ዴሞክራሲያዊ ነው በማለት የተቀበለው ጉባዔው፣ የሚመሠረተው ብሔራዊ ሸንጎ በፕሬዚዳት ኢሳይያስ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት ከወደቀ በኋላ፣ የሚቋቋመው የሽግግር መንግሥት የጠራ ፖሊሲና አቋም ያለው ለማድረግ ጠቃሚ መሆኑን የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት አባል አቶ መሐሪ አብርሃ ተናግረዋል፡፡
ጉባዔው ለመጀመርያ ጊዜ የሲቪል ማኅበረሰቦች እኩል ተሳታፊ ያደረገ ነው ያሉት ሌላው የኮሚሽኑ አባል፣ የኮሚሽኑ አባላት 60 በመቶው ከሲቪክ ማኅበራት የተወከሉ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
በኤርትራ መንግሥት እየተፈጸመ ያለው ሁለንተናዊ ጭቆና በአጭሩ መቋጨት እንዳለበት የተስማማው ብሔራዊ ጉባዔው፣ በብሔር፣ በቋንቋና በሃይማኖት በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ላይም ስምምነት መደረሱን መግለጫው ያመለክታል፡፡