አቡጊዳ – የአቃቤ ሕግ መረጃ እነእስክንድር ሰላማዊ እንጂ ሽብርተኞች እንዳልሆኑ በገሃድ አረጋገጠ !

አቃቢ ሕግ ሰባተኛ ተከሳሽ በሆነዉ ፣ አቶ እስክንድር ነጋ፣ ግንቦት 20 2002 ዓ.ም የተጠለፈ፣ ከአዲስ ድምጽ ራዲዮ አዘጋጅ አቶ አበበ በለዉ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስን እንዲሁም በከረንት አፌር ፓልቶክ ክፍል በብዙ ወንድማገኘዉ (ሞያዬ ምስክር) አወያይነት የተደረገን ዉይይት፣ ትላንት ዴሴምበር 29 ቀን በተቀመጠዉ የፍርድ ችሎት፣ እንደ መረጃ ማቅረቡን፣ የአማርኛዉ ክፍል ጀርመን ድምጽ ራድዮ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ዘገበ።

ከምርጫ 2002 በኋላ ሕዝቡን ለአመጽ ስሜቱን ማነቃቃትና ለሕዝባዊ ተቃዉሞ ማነሳሳት የሚያስፈልገዉ አሁን በምርጫ ማግስት መሆኑን አቶ አበበ በለዉ ሲናገሩ እንደተሰሙ የገለጸዉ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ፣ አቶ እስክንድር ግን በበኩሉ እንደማይስማማና በሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሕግን ተከትሎ የሚደረጉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ብቻ እንደሚደግፍ ሲናገርና ሲመልስ እንደተደመጠ ዘግቧል

አቃቤ ሕግ አቶ እክስንድር ከከረንት አፌር ፓልቶክ ክፍል ጋር ያደረጉትን ዉይይት ያስደመጡ ሲሆን በዚህ በተደመጠዉ ኦዲዮ አቶ እክስንድር በድጋሚ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግልን እንደሚደግፉ በገሃድ ሲናገሩ መደመጣቸውን ፣ የአቶ እስክንድር ኦዲዮዎች ከተደመቱ በኋላ ደግሞ ፣ 1ኛ ተከሳሽ አንዱዋለም አራጌ ጨምሮ በሌሎች ላይ የሚቀርበዉ የድምጽ ማስረጃ ለአቶ እስክንድር ከቀረበዉ ማስረጃ ጋር ተመሳሳይነት ስላለዉ አቃቤ ሕግ «ይበቃኛል» እንዳለ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ዘግቧል፡

አቃቤ ሕግ እነ አንዱዋለም አራጌን «ከግንቦት ሰባትና ከሻእቢያ ጋር በማበር በሽብር ተግባር ተሰማሩ» ለሚለዉ ክሱ እንደ መረጃ ያቀረባቸው አብዛኛ ኦዲዮዎች የማይሰሙ፣ የተሰሙትም ደግሞ ተከሳሾቹ ለሰላማዊና ሕጋዊ ጥቅል የቆሙ እንደሆነ በይፋ ማረጋገጣቸው፣ አቃቤ ሕግ ፣ ምናልባት መረጃዉን አስቀድሞ ሳያጠናና የራሱ የሆነዉ የሕግ ድምዳሜ ሳይወስድ፣ ክሱን አቅርብ ተብሎ በትእዛዝ እንደከሰሰ ሊያሳይ እንደሚችል ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሞያ ይገልጻሉ።

«ብዙ ጊዜ አቅቤ ሕግ ከፖሊስ ተከሳሽ ሲቀርብለት፣ ያሉትን መረጃዎች ያመዛዝን እና ክሱን ለመቀጠል ወይንም ለማቆም ይወስናል። በቂ መረጃ ከሌለ ወይንም መረጆቹ በፍርድ ቤት ሊቆሙ የማይችሉ ከሆነ አቃቤ ሕጎች ከወዲሁ ወድ ፍርድ ቤት አይሄዱም» ያሉን እኝህ የሕግ ባለሞያ ፣ «እነ እስክንድርን ሽብተኞች ናቸዉ በሚል ክስ ለሰላም የቁሙ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ መረጃ እንዳለ አቃቤ ሕግ ካወቀ፣ ተከሳሾቹ መፍታት ወደ ፍርድ ቤትም አለመሄድ ነበረበት» ሲሉ በአቃቤ ሕጉ የተደረገዉ ዉሳኔ ፖለቲካዊ እንጂ ሕጋዊ እንዳለሆነ ያሳየሉ። እኝህ የሕግ ጠበብት፣ የክስ ሂደቱ በአቃቤ ሕግ እጅ ላይሆን እንደሚችልና አቃቤ ሕጉ በሞያዊዉ ሚዛኑ የክስ ሂደቱ መቀጠል እንደሌለበት ቢያምንም፣ ከበላይ በመታዘዙ ያደረገዉ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ አስተያየቶቻቸዉን አክለዋል።

የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ያቀረበዉን ዘገበ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ