ግንቦት 7 የወያኔ ፍርድ ቤት በሁለቱ የሲውዲን ጋዜጠኞች ላይ ያስተላለፈውን የጥፋተኝነት ውሳኔ በማውገዝ በአስቸኳይ እንዲፈቱ የአለም አቀፍ ህብረተሰብ ጫና እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ
ግንቦት7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች ላይ የተሰጠውን ውሳኔ ያወገዘውና አለም አቀፍ ህብረተሰብ የሚችለውን ሁሉ ጫና አድርጎ ያለምንም ቅድሜ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ የጠየቀው ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 15 ቀን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ባወጣው መግለጫ ነው።
“ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፐርሰን ጆግኖቻችን ናቸው” በሚል ርዕስ ግንቦት 7 ባወጣው በዚህ መግለጫ፤ በህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የይስሙላ ፍርድቤት በነዚህ ሁለቱ የሲዊድን ጋዜጠኞች ላይ ያስተላለፈው የጥፋተኝነት ውሳኔ፤ በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ የሚመራው የህወሃት ፓርቲና አገዛዙ፤ ጋዜጠኞች እውነትን በመዘገብ ህዝብ መረጃን በአግባቡ እንዲያገኝ ብሎም በመንግሥትና በህዝብ መካከል ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያደርጉ መሆናቸውን እውቅና ያልሰጠ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ካለ በኋላ ጋዜጠኝነት ለመለስ ዜናዊና ግብረአበሮቹ፤ እነርሱ የሚሉትን እንደ ገደል ማምቶ ማስተጋባት ብቻ ነው ብሎአል።
መለስ ዜናዊ በትረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረበት 1983 ጀምሮ ነጻ ሚዲያ ላይ የተሰማሩ ጋዜጠኞችና የህተመት ውጤቶቻቸው የሥር ዓቱ ዋና የጥቃት ዕላማ ሆነዋል ያለው የግንቦት 7 መግለጫ፤ በዚህም የተነሳ በመቶዎች የሚቆጠሩት ለእስር ተዳርገዋል፤ በእስር ቤት እያሉም አሰቃቂ ሰቆቃና ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፤ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል፤ ይህ መግለጫ በተሰጠበት በዚህ በአሁኑ ሰዓት እንኳ በርካቶች በእስር ላይ ሁኔው ስቃይና መከራ እየተቀበሉ ነው፤ በዚህ የጭቆና ሂደት ውስጥ ለይስሙላ የተቋቋመው የፍትህ አካል ጋዜጠኞችን በመወንጀልና በእስር በመቅጣት እንደ አይነተኛ መሳሪያ እያገለገለ ይገኛል ብሎአል።
በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሰው ሰራሽ ሰቆቃ በአይናቸው ተመልከተው እውነቱን ለመዘገብ ስንቀሳቀሱ ተይዘው የታሰሩት ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፐርሰን ለእውነት ሲሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ ካሉ ጥቂት አለም አቀፍ ጋዜጠኞች መካከል ናቸው ያለው የግንቦት 7 መግለጫ፤ በሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ የተፈጸመው ፍርደገምድልነት የመለስ ዜናዊ አገዛዝ እውነትን ለመደበቅ ሲል በጋዘጠኞች ላይ የሚወስደው የእብሪት እርምጃ ድንበር የማያገድበው መሆኑ ያስመሰከረና ዜጎቻችን ላለፉት 20 አመታት በወያኔ ፍርድቤቶች ሲደርስባቸው የኖረውን ኢፍትሃዊነት አለም አቀፍ ህብረተሰብ እንዲያውቅ አይን ገላጭ ሆኖአል ብሎአል።
በመጨረሻም ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፐርሰን ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ያሳዩት ብቃትና ድፍረት በአገራቸው በስዊድን ህዝብ ፊት ብቻ ሳይሆን በኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድም ክብርና ሞገስ የተቸሩ ጀግና አድርጎአቸዋል በማለት አለም አቀፉ ማህበረሰብ እነዚህን ለሙያቸው ፍቅር ሲሉ በወያኔ ሰቆቃ ሥር የወደቁትን ጋዜጠኞች በአስቸኳይ ለማስፈታት የተቻላውን ሁሉ ጫና እንዲያሳርፉ ጥሪውን በማቅረብ፤ ጋዜጠኞች ከወያኔ እስር እስክፈቱ ድረስ ለሰላምና ለሰው ልጆች ነጻነት ከቆሙት ሃይሎች ጋር ቆሞ እስከመጨረሻው እንደሚፋለምላቸው ግንቦት7 በመግለጫው አረጋግጦአል።
በተያያዘ ዜና በሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ የስዊዲንን ህዝብና መንግሥት እጅግ ያስቆጣ መሆኑን የስዊድን ሚዲያዎች እየገለጹ ነው። የስዊድን ጠቅላይ ሚንስትር በአገራቸውና በአውሮጳ ህብረት ውስጥ ባላቸው የአባልነት መቀመጫ ስልጣን ተጠቅመው በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ላይ ተገቢውን ጫና ባለማሳረፋቸው ዜጎቻቸው በወያኔ እስር ቤት እንዲሰቃዩ ጊዜ ሰጥተዋል የሚል የሰላ ሂስ እየቀረበባቸው መሆኑ እየተዘገበ ነው።