ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ “በለሎች እስረኞች ላይ በሃሰት መስክሪና በነጻ ትለቀቂያለሽ ተብዬ በሃሰን ሺፋና ሌሎች ወንጀል መርማሪዎች ተጠይቄ እምቢ በማለቴ ጨለማ ውስጥ ለ13 ቀናት ታግቼያለሁ” ስትል ለወያኔ ፍርድ ቤት ችሎት ተናገረች
ወጣቷ ሴት ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ይህንን የወያኔ ከፍተኛ ወንጀል መርማሪዎች ተንኮል ያጋለጠቺው ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የወያኔ ፈደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልዴታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ፊት ቀርባ የተመሰረተባትን የሽብርተኝነት ክስ እንድታስተባብል በተጠየቀችበት ወቅት እንደሆነ ዘጋቢያችን ከስፍራው ከላከልን ሪፖርት ለማወቅ ተችሎአል።
ጋዜጠኛ ርዕዮት ለይስሙላ ፍርድቤቱ በሰጠቺው ማስተባበያ ቃል “እኔ በሙያዬ ጋዜጠኛ ነኝ፣ ይህን የሚያውቀው አርቲስት ደበበ እሸቱ የኢትዮጵያን ሪቪዩ ድረ ገጽ ባለቤት ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ ሪፖርተር ሲፈልግ እኔን አገናኘው፣ እኔም ፈቃደኛ ሆንኩኝ፡፡ በዚህም ለ2 ወር ከምናምን የተለያዩ ዜናዎችን ሰርቻለሁ፡፡ መጋቢት መጨረሻ 2003 አካባቢ በቃ የሚል በየአካባቢው እንደተፃፈ ኤልያስ መረጃ እንዳለውና ፎቶ አንስቼ እንድልክለት ጠይቆኝ ልኬለታለሁ፡፡” ብላለች።
ርእዮት አክላም “ሌላው ፍርድ ቤቱ እንዲያውቀው የምፈልገው በርካታ መርማሪዎችና ትልልቅ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች፣ በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ሀሰን ሺፋ-ን ጨምሮ፣ በሌሎች ተከሳሾች ላይ በሀሰት መስክረሽ ነፃ ውጪ ብለውኛል፡፡ ይህን አልቀበልም በማለቴ እርሳቸው እንዲህ ዓይነት አቋም ካለሽ ለምን ጫካ አትገቢም ብለውኛል” በማለት ተናግራለች፡፡
ርእዮት “አንድ አሁን እዚህ ችሎት ፊት የሌለ ዐቃቤ- ሕግ፣ በሀሰት እንድመሰክር አባብሎኝ አልቀበል በማለቴ ከ25 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እሥራት ይጠብቅሻል ብሎ ዝቶብኛል፡፡ እኔም በሰዎች ላይ በሃሰት ለመመስከር ፍቃደኛ ባለመሆኔ በማዕከላዊ እሥር ቤት ለ13 ቀናት በጨለማ ክፍል ብቻዬን አሥረውኛል፤ ከጨለማ ክፍሉ እንድወጣ በተደረኩበት ዕለትም አንዱ መርማሪ እያሳሳቀኝ አንዷ ተደብቃ በቪዲዮ ልትቀርጸኝ ሞክራ ፊቴን ከልዬ ራሴን ተከላክያለሁ በማለት የወያኔ ጀሌዎች ሊያደርሱባት ከፈለጉት የሞራልና የአካል ማሸማቀቅ እንዴት እራሷን እንዳዳነች ተናግራለች::
በመቀጠልም “እኔ ጋዜጠኛ ነኝ በሰላማዊ መንገድ መንግሥትን እቃወማለው፡፡ ይህንን በማድረጌም ሆን ብለው በኔ ላይ የሃሰት መረጃ ለማሰባሰብ ሲባል በምገለገልበት የኢሜሌ አድራሻ ከኔ ያልሆኑ በርካታ የውሸት መልዕክቶች ሆን ተበልው እንዲገቡ ተደርጎብኛል፡፡ በኢሜሌ ላይ የነ ጆሃር ሙሀመድን ጽሑፍ ከተውብኝ ተጠያቂ ሊያደርጉኝ ይፈልጋሉ፡፡ የትርጉም ድርጅቱ ሁሉ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት እንዳለው በሚያስመስል መልኩ እንዲተረጉሙ በተሰጣቸው መልዕክቶች ውስጥ ሽብር ሽብር የሚል ትሩጉም ከራሳቸው ጨምረዋል፡፡ ለምሳሌ፣ በሰሩት ትርጉም ውስጥ ያልነበረ አንድ ቦታ ላይ አመጽ ትክክለኛ አማራጭ ነው ብለው አቅርበዋል፡፡ ይህ ተቃዋሚ ስለሆንኩ ብቻ የተሰራብኝ ደባ ነው፡፡” ብላለች።
ይህ በዚህ እንዳለ ፍርድ ቤቱ በእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል በተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባል አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚሃብሄር፣ የአውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ እና ሂሩት ክፍሌ ላይ የመከላከያ ምሥክሮችን ባለፈው ሃሙስ አደመጦአል፡፡
አርቲስት ደበበ እሸቱ የርእዮት ዓለሙ የመጀመሪያ ተከላካይ ምሥክር ሆኖ ርዮትን ከኢትየጵያን ሪቪዩ ድረ ገጽ ጋር እንዴት እንዳገናኛቸው ለፍርድ ቤቱ ያስረዳ ቢሆንም ጋዜጠኛ ርእዮት ዓለሙ የሙያ ምሥክርነት ሊሰጡ የመጡትን የመድረክ አመራር አባልና የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረንስ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና እና የሕግ ባለሙያ የሆኑትን ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምን “በሕግ ላይ ሙያዊ ምስክር አይሰጥም ሕግ የመተርጎሙ ሥራ የኔ ብቻ ነው” በማለት ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበለ ተያይዞ የደረሰን ዜና አመልክቶአል። ሁለቱ ምሁራን የፍርድ ቤቱን ስንብት በዝምታ ተቀብለው ሲወጡ “የቀኝ ዳኛው ችሎቱን መከታተል ከፈለጋችሁ መቀመጥ ትችላላችሁ” ሲሏቸው ዘወር ብለው በትዝብት አይን አይተዋቸው ወጥተዋል ተብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢብዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሄር በበኩላቸው “እኔ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀመንበር ነኝ፣ ሽብርተኝነትን እናወግዛለን መቼም ቢሆን ሽብርተኝነትን ደግፈን አናውቅም፣ አንደግፍም፤ ከጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ ጋር ያለን ግንኙነት የፖለቲከኛና የጋዜጠኛ ነው፡፡ ከእርሱ የተቀበልኩት ገንዘብም ተልዕኮም የለም፡፡ ነገር ግን ለፓርቲ የሚገባ ገንዘብ ከአንድ ግለሰብ ተቀብያለሁ፣ ይህ ደግሞ በፓርቲው ሰነድ ውስጥ ይገኛል፡፡” በማለት በወያኔ የፈጠራ ክስ እንዳልተደናገጠ በሚገልጽ አነጋገር አስረድቶአል።
“ፓርቲያችን ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ አስገብቶ ማስፈራሪያና ዛቻ ከመንግሥት ሲደርስብን ነበር፤ ፓርቲያችን የተቋቋመው መንግሥትን ለመቃወም ነው፣ በሕጉ መሠረት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በ24 ሰዓት ውስጥ ማሳወቅ አለበት እንጂ ማስፈቀድ አለበት አይልም፣ መለስ በቃህ የሚለው መፈክርም በፓርቲያችን የተፃፈ ነው፡፡ ደህንነቶች ግማሾቻችንን ደብድበውናል፣ እኔ ጸጉሬ እየተነጨ ነው የተደበደብኩት” በማለት ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል፡፡
በኤልያስ ክፍሌ የክስ ፋይል ሦስተኛ ተከሳሽ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ዐቃቤ- ሕግ ባቀረበብኝ የስልክ፣ የኢሜል ልውውጥ ክሶች ላይ ነው የማስተባብለው አለ ካለ በሁዋላ ” እኔ መብቴን በተጠቀምኩና ሙያዬን በመተግበሬ ነው የተከሰስኩት፣ የሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 2/4 ይሄን ይፈቅድልኛል፣ ተሸሽሎ የወጣው የፕሬስ አዋጅ አንቀጽ 7 ይህን ማድረግ እንደምችል ያስቀምጣል ይሄ ይያዝልኝ” ካለ በሁዋላ ፤ “በኢሜል ልውውጡ የተጨመሩ ቃላት ወደ አማርኛ ሲተረጎም የተዛቡ ቃላት ተጨምረውብኛል፣ ይሄም ፍርድ ቤቱን ለማጭበርበር ነው፤ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሻለሁ የሚል አለ፣ ሰኔ 23 ቀን 2003 ዓ.ም ኢሜል እንደተፃፃፍኩ የቀረበ አለ፣ ነገር ግን እኔ ሰኔ 12 ቀን በቁጥጥር ሥር ውዬ ሰኔ 13 ቀን ፍርድ ቤት ቀርቤያለሁ፣ እንግዲህ ከታሰርኩ ሳምንት ሆኖኝ ሁሉ ተፃፅፊያለሁ ማለት ነው፡፡ እኔ ጋዜጠኛ ነኝ ነገር ግን የጦር ጄኔራል አድርገው አቅርበውኛል፡፡ ጦርነት እየተካሄደነው የሚል አለ፡፡ ውጪ አገር ላለ ወንድሜ በእንግሊዝኛ አዛውንት አባቴ ታሞ ኦፕሬሽን ላይ ነው ይታከም ያልኩትን የጦርነት ኦፕሬሽን ነው ብለው ተርጉመውታል፡፡” ሲል የወያኔ አቃቤ ህግና ወንጀል መርማሪዎች በጋራ የሚያቀነባብሩትን የሃሰት ክስ ድራማ አጋልጦአል።