በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ንብረት አውድመዋል የተባሉ 52 ተማሪዎች መቀጣታቸውን ተገለጸ
በማንኛውም የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ወጣት ዜጎች በአገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ወያኔን በሚቃውም መልኩ ምንም አይነት ተሳትፎ እንዳያደርጉ ለማገድ ለሥርዓቱ ታማኝ የሆነ አስተዳደር በየትምህርት ቤቶቹ ከማቋቋም ጀምሮ ለነጻነታቸውና ለመብታቸው የሚቆረቆሩትን አድኖ ከትምህር ገበታቸው በማባረር ተግባር ላይ የተሰማራው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ሰሞኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ቅጣት ማስተላለፉን ዘጋቢያችን ከስፍራው ባስተላለፈው ዜና ገለጸ።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ካሉ ተማሪዎች ቁጥራቸው 50 በሚሆኑት ላይ የተላለፈው ቅጣት በሁለት ደረጃ የተከፈለ ሲሆን ጥፋተኝነታቸው በአንደኛ ደረጃ የተፈርጀው 22 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ከትምህርታቸው እንዲገለሉ ሲደረግ፣ 18ቱ ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በተማሪዎቹ ላይ ይህ ቅጣት የተላለፈው በቅርቡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በምግብ መመረዝ ምክንያት በተነሳው በሽታ የተማረሩ ተማሪዎች የመብት ጥያቄ አቅርበው ስለነበር ይህንን የመብት ጥያቄ ማቅረባቸው እንደወንጀል ተቆጥሮባቸው ነው።
አንድ አመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲባረሩ መደረጋቸው አንሶ ተማሪዎቹ ባስነሱት ተቃውሞ የወደመ ንብረት አለ ተብሎ የንብረቱ ግምት በጥሬ ገንዘብ እንዲከፍሉም ተወስኖአክል። እንደሪፖርተራችን ዘገባ የወደመውን ንብረት መክፈል ካልቻሉ የትምህርት ማስረጃቸው የማይጣቸው ሲሆን፣ ከዚህ በኋላም በማንኛውም ዓይነት ጥፋት ውስጥ ቢሳተፉ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲው ይባረራሉ ተብሎአል።
በጐንደር ዩኒቨርሲቲ ማራኪና ቴዎድሮስ ግቢዎች ውስጥ ከአንድ ወር በፊት ‹‹ሽጌላ›› በተባለ ከተበከለ ምግብ ወይም ውኃ በሚነሳ ባክቴሪያ ሳቢያ በተቀሰቀሰ ወረርሽኝ ከ1 ሺ በላይ ተማሪዎች መታመማቸው ይታወቃል።
ወያኔ ህዝባዊ ተቃውሞን በሃይል ለመጨፍለቅ እየወሰደ ያለው ፋሽስታዊ እርምጃ አላማ ህዝብን በፍረሃት ቆፈን ውስጥ በመክተት የአገዛዝ እድሜውን ለማራዘም እንደሆነ የተሰወረ አይደለም።