ደቡብ ክልል በወያኔ ግምገማ እየተተራመሰ ነው ተባለ ። አርበኛው የኔሰው ገብሬ የከፈለውን ህይወት መስዋዕትነት ዋጋ ለማሳጣት የስም ማጥፋት ዘመቻ ያካሄደው ባለሥልጣን ከሃላፊነቱ ተባረረ። ሃያ ሰባት የመኢአድ አባላት በደቡብ ክልል በወያኔ ካድሬዎች ታሰሩ
በህወሃት የሚመራው ዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በተለያየ ሹመትና ጥቅማ ጥቅሞች የራሱ ምርኮኛ አድርጎ የሚገለገልባቸውን የሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆች በአዳዲስ ታዛዦች ለመተካት ዘወትር በሚጠቀምበት ግምገማ ሰሞኑን በደቡብ ክልል በርካታ ሰዎች ከነበሩበት የሃላፊነት ቦታ መባረራቸውን የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን ኢሳት በትናንትና የዜና ዘገባው አስታወቀ።
እንደ ኢሳት ዘገባ የደቡብን ክልል እያተራመሰ ያለውና ከ50 በላይ ለሚሆኑ የወያኔ የቀድሞ ሹሞች ከሃላፊነት መነሳት ምክንያት የሆነው ግምገማ ዋነኛ አላማ፤ በቅርቡ በዳውሮ ዞን በዋካ ከተማ ከተነሳው ጸረ መንግስት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ መረጃው በአለም እንዲሰራጭ በማድረግ በኩል እጃቸው አለበት ብሎ የጠረጠሯቸውን ሹመኞቻቸውን በማባረር በአዲስ ሰዎች ለመተካት የታለመ ነው።
በአሁኑ የወያኔ ግምገማ የመባረር እጣ ከደረሳቸው ታማኝ አገልጋዮች መካከል የደቡብ ክልል የፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ የነበረው አለማየሁ አሰፋ የተባለ የወያኔ ተለጣፊ ድርጅት አባል አንዱ እንደሆነ የዘገበው ኢሳት ፤ በወያኔ ኢፍትሃዊነት ተማሮ በራሱ ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ ለህልፈት የበቃው ወጣት መምህር የኔሰው ገብሬ ዜና እንደተሰማ “የኔሰው ገብሬ የአእምሮ በሽተኛ ነበር” በማለት ሰዎች የሃሰት ምስክርነት እንዲሰጡ በማድረግ ለወያኔ አለቆቹ ከፍተኛ ዉለታ ለመዋል የሞከረ እንደሆነ ገልጾ በዚህም ምክንያት በዋካ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻና ተቃውሞ ከማስነሳቱም በላይ በደቡብ ክልል እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ብሶት ለማስታገስ አልቻለም በሚል ተወንጅሎ ከተላላኪነት ስልጣኑ እንዲተባረረ ምንጮቹን ዋቤ በማድረግ ዘግቦአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትናትናው ዕለት ታህሳስ 16 ቀን የዳውሮ ዜን የተለያዩ ወረዳዎች ካቢኔ አባላት በዋካ ከተማ የተፈጠረውን ችግር እየገመገሙ ባሉበት ወቅት ከጌኛ ወረዳ የመጡ አርሶ አደር ራሳቸውን በገመድ ሰቅለው ለመግደል ሲሞክሩ በቦታው የነበሩ ፖሊስና የካቢኔው አባላት ባደረጉት ህይወት የማዳን ርብርቦሽ ሰውየውን ከሞት ለማትረፍ መቻሉን ኢሳት አክሎ ገልጾአል።
አርሶአደሩ ይህን እርምጃ የወሰዱት የወረዳው ካቢኔ አባል የወንድሙን ሥልጣን ጋሻ መከታ በማድረግ መሬቴን በጉልበት ቀምቶ ወስዶብኛል በሚል ቀሬታ እንደሆነና ችግራቸውን በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያመለክቱም መፍትሄ የሚሰጣቸው ሰው በመታጣቱ ተስፋ ቆርጠው እንደሆነ ለማወቅ ተችሎአል።
በአገሪቱ የሰፈነው ኢፍትሃዊነት አስመርሮአቸው ህይወታቸውን ለማጥፋት ሙከራ ያደረጉ ግለሰብ በአሁኑ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሎአል ያለው ኢሳት መምህር የኔሰው ገብሬ ራሱን በእሳት አቃጥሎ ከገደለበት ጊዜ ጀምሮ አንድ የመንግስት ሰራተኛ ራሱን አንቆ ለመግደል መሞከሩን፣ መሬቱዋን የተቀማች ሌላ ሴት አርሶ አደር ደግሞ ገደል ውስጥ ገብታ ራሱዋን ማጥፋቱዋን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጠዋል ብሎአል።
በሌላ በኩል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ልዩ ዞን በዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ 27 የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራርና አባላት በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መኢአድ አስታወቀ፡፡ የደምባ ጎፋ ወረዳ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማዩ ማይጠሎ በበኩላቸው፣ የተጠቀሱት የመኢአድ አባላት የታሰሩት በአካባቢው እየተከናወነ ያለውን የልማት ሥራ ለማደናቀፍ በመንቀሳቀሳቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
መኢአድ ትናንት ለሪፖርተር በላከው ጥቆማ እንዳስታወቀው፣ ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከታሰሩት የመኢአድ አባላት መካከል ስድስቱ የፓርቲው አመራሮች ናቸው፡፡
በጎፋ ልዩ ዞን የዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ የመኢአድ ሰብሳቢ አቶ ኢልካዩ ኤሮ፣ ምክትል ሰብሳቢው መምህር አየለ ታደሰ፣ ዋና ጸሐፊው አቶ ዘሪሁን እኩሌ፣ የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ኢሳያስ ዘርቦ፣ ሃምሳ አለቃ ማናዬ ሞላልኝና አቶ መንግሥቱ ማናዬ ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ በመኢአድ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በስብሰባ ላይ እያሉ በፖሊሶች የታሰሩ መሆናቸውን መኢአድ አስታውቋል፡፡
ሌሎቹ ሃያ አንድ የዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚዎችና አባላት የታሰሩትም ከላይ በተጠቀሰው ቀን ምሽት የወረዳው የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት የመኢአድ አባላት በሚኖሩበት አካባቢ አሰሳ እንዲካሄድ ካዘዙ በኋላ መሆኑንም ገልጿል፡፡
የዳምባ ጎፋ ወረዳ የምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማዩ ማይጠሎ በበኩላቸው፣ የመኢአድ አባላት የታሰሩት የክልሉ መንግሥት በአካባቢው እያከናወነ ያለውን የተፋሰስ ልማት ለማደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፣ በደምባ ጎፋ ወረዳ የተፋሰስ ሥራ ለመሥራት ለቀያሾች ሥልጠና እየተሰጠና ጐን ለጐን ሌሎች የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ፣ ሃያ ሰባቱ የመኢአድ አባላት ‹‹የተፋሰስ ሥራውን አንሠራም›› ብለው በመቃወማቸው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሊውሉ ችለዋል፡፡
በአካባቢው የሚኖሩት የመኢአድ አባላት በሌሎች ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በተፋሰስ ሥራው እንዳይሳተፉ የሚጠይቅ ደብዳቤ አዘጋጅተው ለመበተን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጠቆሙት አቶ ማዩ፣ ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ሃያ ሰባቱ የመኢአድ አባላት ልማቱን ለማደናቀፍ ተመሳሳይ አጀንዳ ይዘው ሲወያዩ በነበረበት ወቅት በፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ቀጣና ኃላፊ አቶ እንድሪያስ ኤሮ በበኩላቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመኢአድ አባላት የታሰሩት ልማት በማደናቀፋቸው ሳይሆን የግለሰቦችን ማሳ አንቆፍርም ብለው በመቃወማቸው ነው፡፡
በአካባቢው የሚገኘውን የግለሰቦች ማሳ ከመቆፈር ይልቅ ነዋሪዎች በጋራ የሚጠቀሙበትን መሬት ለተፋሰስ ሥራ ማዋል የተሻለ እንደሚሆን በመጠቆም ለቀበሌው ኃላፊዎች በጽሑፍ ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለጹት አቶ እንድሪያስ፣ ይህ የመቃወም መብት ልማት እንደማደናቀፍ ተወስዶ የመኢአድ አባላት ለእስር መዳረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹የዜጎች የመናገርና የመጻፍ መብት የተጠበቀ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ማንኛውንም ነገር የመቃወም መብት አላቸው፤›› የሚሉት አቶ እንድሪያስ፣ የደምባ ጎፋ ወረዳ ባለሥልጣናት ግን ሕገ መንግሥቱ ለዜጐች የሰጠውን መብት በመጣስ ሰላማዊ ዜጐችን እያሰሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ዜጎች በመንግሥት ባለሥልጣናት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን መቃወም አይችሉም ወይ?›› የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የወረዳው ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማዩ ማይጠሎ ግን፣ ‹‹ይህ የልማትና የሕይወት ጉዳይ ነው፡፡ እነሱ ካልሠሩ ማን መጥቶ ሊሠራላቸው ነው? አንሠራም ማለት አይችሉም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ወረዳውም በመኢአድ አባላት ላይ ‹‹ልማትን በማደናቀፍ›› በሚል ክስ ለመመሥረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በመጨረሻም በደቡብ ክልል እየተፈጸመ ያለው ተስፋ መቁረጥ የአገራችን ህዝብ በአገዛዙ ላይ ያለውን ምሬትና ጥላቻ ነጸብራቅ እንደሆነ ብዙዎች የፖለተካ ተንታኞች ይስማማሉ