የወያኔ ፍርድ ቤት በስዊድን ጋዜጠኞች ላይ ያስተላለፈው ቅጣት አለም አቀፍ ተቃውሞ ቀስቅሶአል
የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍና ሰቆቃ ለመታዘብ ወደ ክልሉ ሲገቡ የተያዙትና በወያኔ ፍርድቤት የአስራ አንድ አመት ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች ጉዳይ ከፍተኛ የሆነ አለም አቀፍ ተቃውሞ በአገዛዙ ላይ ማስነሳቱን የዝግጅት ክፍላችን አረጋገጠ።
የወያኔ ፍርድ ቤት ከትናንት በስቲያ ባስተላለፈው ቅጣት የተቆጡና የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ካሉት አገሮች በተጨማሪ የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ፍርዱን ፍትህ የሌለበት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነት ለመገደብ የተሰጠ የፖለቲካ ውሳኔ ሲሉ አጣጥለውታል።
የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ፍሬድሪክ ራይንፌልት መንግሥታቸው ሁለቱም ያገራቸው ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ማንኛውንም እርምጃ እንደሚወስድ ያስታወቁ ሲሆን የአውሮጳ ህብረት የውጪ ግንኙነት ሃላፍ የሆኑት እንግሊዛዊዋ ክርስትን አሽቴን ጽቤት ባወጣው መግለጫ ሁለቱም ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንደሚፈቱ ያለውን እምነት ገልጾአል። ይህም በዲፕሎማሲ ቋንቋ “በአውሮጳዊያኑ ዜጎቻችን ላይ ያስተላለፋችሁት ፍርድ ውሃ የማይቋጥር ስለሆነ ጫወታችሁን ወደ ጎን ተወት አድርጋችሁ ግንኙነታችን እንዳይበላሽ ከፈለጋችሁ በአስቸኳይ ፍቱዋቸው” የሚል መልዕክት እንዳለው ለዲፕሎማቲክ ግንኙነት ቀረበታ ያላቸው ምንጮች ይናገራሉ።
የወያኔ ፍርድቤት ዳኛ የሆነው ሸምሱ ሲርጋጋ የፍርድ ውሳኔውን እያነበበ ባለበት ወቅት በብስጭት ችሎቱን ረግጠው የወጡት በኢትዮጵያ የሲዊዲን አምባሳደር ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብየ እና ጆአን ፐርሰን ለእስር የሚያበቃ ወንጀል ያልፈጸሙ ሙያተኞች ናቸው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለ በጋዜጠኞቹ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ያስቆጣቸው አትዮጵያውያን ከትናንትና በስቲያ ስቶክሆልም በሚገኘው የወያኔ ኤምባሲ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን የግንቦት 7 ዘጋቢ ከስፍራው በላከልን ሪፖርት ገለጸ።
ኢትዮጵያዊያኑ ጋዜጠኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ በጠየቁበት በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በርከት ያሉ የስዊድን ታዋቂ ሚድያዎች ተገኝተው ዜናውን በሙሉ የዘገቡት ሲሆን ፣ ኢትዮጵያዊያን ባስተላለፉት መልእክትም በጋዜጠኛ ማርቲን ሽብየ እና ጆአን ፐርሰን ላይ የተወሰደው እርምጃ የአገራችን ዜጎች ላለፉት 20 አመታት ሲጋቱት የኖሩት ኢፍትሃዊነት መሆኑን በመረዳት ምእራባዊያን መንግስታት ወያኔን ከስልጣን ለማስወገድ የሚደረገውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል ።
ወያኔ በጫካ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት ይቆጣጠራቸው ወደነበሩት ቦታዎች የውጪ ጋዜጠኞችን በማስገባት ደርግ በነርሱና በአካባቢያቸው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ይፈጽም የነበረውን ጦርነት ሲያስዘግቡ እንደነበረ ይታወቃል። የወያኔን ጸረ ደርግ ትግል ከነርሱ ጋር ሆኖ ይዘግብ ከነበሩት አንዳንዶቹ ስዊድናዊያን ጋዜጠኞች እንደነበሩ ሰሞኑን በሙያ ባልደረቦቻቸው ላይ በተሰጠው ፍርደገምድል ውሳኔ ተቆጥተው ሲናገሩ ተደምጠዋል።