ለምን ተውኸኝ ? ላማ ሰበቅታኒ (?ינתבזא המל) – (በነጋ አባተ)
እውነት ሲሸጥ፤ እውነት ሲሰቀል፤ እውነት ሲደማ የተጮኸ ጩኸት ነበር። ይህ የሰቆቃና የጭንቅ ጩኸትም በአኬልዳማ ተደመደመ። በወቅቱ እውነት እንዲሰቀል ምክኒያት የሆኑ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የሃይማኖትን ልብስ ለብሰው በማስመሰል ከመቆም ውጭ ከዕውነት ጋር የተቃረኑ፤ ኑሮአቸውና ማንነታቸው በውሸት የተሞላ ነበር። ኢየሱስ ወደ እነርሱ መጣና እንዲህ አላቸው “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ……እውነትም በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም ሃሰተኛ የሃሰት አባት ነውና..”እንግዲህ የተውኔቱ ግጭት(conflict) የጀመረው እዚህ ላይ ነው። በዕውነትና በሃሰት መካከል የተከፈተ ጦርነት!። ተውኔቱ ይጻፍ ጀመረ። ጸሃፊዎቹ በጊዜው ወንበሩን በተቆናጠጡትና በሃሰት ጎራ የተሰለፉት የፈሪሳውያን ቡድን አባላት ነበሩ። ሃሰት በዕውነት ላይ ዘመተ።
ተውኔቱን ከአባታቸው ጋር ሆነው ስለጻፉት ሴራው በእጅጉ የተዋጣለት ሆነ። ጲላጦስ ከእነርሱ ጋር እንዲተባበር “እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ” ብሏል ብለው በስልጣኑ እንደ መጣበት አድርገው ሸራረቡት ቀጠሉ ከህዝቡ ለመነጠልም “ከአብርሃም በፊት እኔ አለሁ ብሎ የእምነትህን መሰረት ናደ ብለው ህዝብን ለማነሳሳት ሞከሩ። ተውኔቱ በዚህ ሁኔታ ተጽፎ ካለቀ በኋላ የኢየሱስን መግቢያና መውጫ የሚያውቅ ጠቋሚ ተፈለገ። ለገንዘብ ልቡ የሚቀልጥ፤ የህሊናውን ህግ ጥሶ ከሰውነት ወደ ዓውሬነት የሚዘቅጥ ሰው ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል ሲፈለግ ይሁዳ ተገኘ(የዛሬዎቹን ይሁዳዎችን ተመልከቱልኝማ)ለማንኛውም ህሊና አይሸጥም ነውር ነው። አኬልዳማም የተውኔቱ መዝጊያና የውሸታቸው ጣራ መድረስ መገለጫ ሆኖ ተካተተ እነርሱም ስለ እውነት መመስከር ጀመሩ።” የደም መሬት” አሉ።
ስለ አኬልዳማና ስለ ስሙ ማንነት ብዙ አልልም ወንድሞቼ ሉሉ ከበደ እና ፋሲል የኔ ዓለም በሚገባ ሄደውበታል። ስለ ፊልሙ ቅንብርም ድንቍ የኪነ_ጥበብ ሰው ታማኝ በየነ ዋቢ እያጣቀሰ በማቅረብ የሀሰቱን ቡድን ሲያሸብረው ለእውነት የቆመውን ኢትዬጵያዊ ግን አንጀቱን አርሶታል። ብራቦ ታማኝ!። እናንት የቍርጥ ቀን የኢትዬጵያ ልጆች በርቱ!። ልቀጥል
ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት በነበሩትና ከእውነት ጋር በተጣሉት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ዕውነትን ለማጥፋት ተውኔት ሲጻፍና ዛሬም መለስና ግብረአበሮቻቸው ሲጽፉት ተውኔቱን በዘመኑ ርቀትም ይሁን ከሰዎቹ ባህሪ ጋር ለማነጻጸር ስሞክር ታሪክ ራሱን ሲደግምና ትንቢቱ ሲፈጸም አስገረመኝ።
የእነዚህን ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ስራ ስንመለከት ዕውነትን የሰቀሉት እነርሱ፤ የዓላማቸው ማስፈጸሚያ የተጠቀሙበትን ይሁዳን በሰላሣ ብር ያታለሉት እነርሱ፤ መሬቱን ገዝተው አኬልዳማ (የደም መሬት ) ብለው የሰየሙት እነርሱ ይህን ሁሉ ካደረጉና ከፈጸሙ በኋላ እውነት የሆነውን ኢየሱስን በመቅበራቸው ለጊዜውም ቢሆን ቀለል ያላቸው መስሎ ታያቸው። እውነት ግን ተሰቅሎ ሞቶም አልቀረም በትንሣኤ ተነሣ። ትንቢቱም ተፈጸመ።
ዛሬም እነመለስ እውነተኛውን የኢትዬጵያን ታሪክ የሰቀሉት እነርሱ፤ ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ የሚሆኑ ይሁዳዎችን በገንዘብ እየገዙ የሚያታልሉ እነርሱ፤ቦንብ እያፈነዱ የሚገድሉ እነርሱ፤ ህዝብ ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ እነርሱ፤ አኬልዳማ ብለው መሬት የሚያስተካክሉ እነርሱ፤ ሰዎች ሆይ! ዛሬም ከሁለት ሽህ ዓመት በኋላ ዕውነት በኢትዬጵያ አደባባይ ተሰቅሎ( אלוקים למה אזבתני ) አምላኬ ሆይ ለምን ተውከኝ? እያለ ነው። ይሁን እንጅ የ“ዕውነት” ማንነት የትንሣኤ ኃይል በሚባል ንጥረ_ነገር ጥቅጥቅ ብሎ የተሞላ በመሆኑ ዕውነትን ገደልን ፣ ቀበርን ብሎ መፎከር አይቻልም።ዕውነት ከሰው አቅም ውጭ የሆነ መለኮታዊ ስዕብና አለው። ባልታሰበ ጊዜና ሥፍራ ድንገት ተነሳሁ፣ አለሁ ይላል።ምን ማድረግ ይቻላል? ከዕውነት ጋር የተጣሉ ሁሉ ግን እንደ ደነገጡ፣ እንደ ተሸበሩ ይኖራሉ። የተሸበረ ደግሞ የሚያደርገውን አያውቅም የሰሞኑ የነአቶ መለስ አኬልዳማ ድራማ የሚነግረን ይሄንኑ ነው። እመኑኝ አኬልዳማ የሃያ ዓመቱ ተውኔት መዝጊያ ነው።
የአኬልዳማ ደራሲ አቶ መለስ ለራሳቸው ብዙ ናቸው። እርሳቸው ለራሳቸው ያላቸው ስፍራ እጅግ ግዙፍ ነው። የሚያስገርመውና የሚያሳዝነው ግን ሁኔታው ሁሉ እርሳቸው ካሰቡት በተቃራኒው መሆኑ ነው። መለስ ለራሳችው የሁሉ ነገር መፍትሄ ናችው። ለተራበውና በችግር ለሚማቅቀው ለኢትዬጵያ ህዝብ ጠረጴዛው ላይ ምግብ ማስቀመጥ አልቻሉም እንጅ በዓለም ላይ ባልታዬ የኢኮኖሚክስ ፍልስፍናቸው የሀገሪቱን ዕድገት አባርረው ካልጠፋው ቊጥር ብለው ነው መሰል ደባብለውና አነባብረው ባለ ሁለት አኅዝ በማድረግ የደደቢት የኢኮኖሚክስ ሊቅ መሆናችውን ለማሳየት ሞክረዋል። እርሳቸው የእርሻ ፣የህክምና ፣ዛሬ እንደምናየውም የተውኔት ባለሙያም ናቸው። በአጠቃላይ እንደ ጅሉ አምባገነን መሪ እንደ ኢዲ አሚን ዳዳ እኔ ፕሬዚዳንት፦ ጄኔራል፦ ዶክተር መለስ ዜናዊ ነኝ ብለው በአደባባይ አላወጁም እንጅ የሚገባን ከሆነና የልብ ጆሮአችን ካዳመጠ በሽርሞ ነግረውናል። እኔ ሁሉን ነኝ አሉ!። እርፍ!።
እንደ እድል ሆኖ ግን መለስ የያዙት፤ የጨበጡትና የነኩት ሁሉ ምድረበዳ ነው። ልምላሜ፣ በረከት የሚባል ነገር ከእርሳቸው ጋር በመሃላ የተጣላ ነው የሚመስለው። ጉስቍልና፤ችጋር፤ ርሃብ ያለጥርጥር የሳቸው ናቸው። በዚህ ሁሉ በማፍያው የአቶ መለስ ዘመንም ግን ድንገት ተነስተው ባለጠጎች የሆኑ የሌሊት ሰዎች የሉም አላልኩም ድንገት ሰጥተው ድንገት የሚነጥቋቸው ባለጠጋ የሚመስሉ ብዙ ድሆችን መፍጠር ችለዋል። ይህም ከተውኔቶቻቸው ጭብጦች አንዱ ገጽታ ነውና።
የዚህ ሁሉ የሁሉን አዋቂነት ባህሪና ምኞት መገለጫው፣ መነሻውና ምንጩ ትዕቢት መሆኑን ልብ ልንል ያስፈልጋል። መለስ አሁን አሁንማ ከትዕቢታቸው ብዛት የተነሣ ራሣቸውን ወደ አምላክነት እየቀየሩና የመመለክ ባህሪ እየታየባቸው የመጡበት ጊዜ ነው። ይህን ጉዳይ ሳነሳ ከአራት ዓመት በፊት ያነበብኳት ኒውስዊክ መጽሄት ትዝ አለችኝ። መጽሄቷ በውስጥ ገጾቿ አንድ ቀልቤን የነጠቀው ርዕስ አስፍራለች ርዕሱ እንዲህ ይነበባል “ Pride goes before destruction a hughty spirit before a fall ”(ትዕቢት ውድቀትን፤ ኩሩ መንፈስም ጥፋትን ያመጣል)ይላል የአማረኛ ትርጉሙ። ርዕሱ የተወሰደው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌ ክፍል ሲሆን ከስሩ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ምስል ተገችሯል።የጽሁፉ አጠቃላይ ሀሳብም የሰውየው አካሄድ በትዕቢት የታጀበና ውጤቱም ጥፋት እንደሆነ በሰፊው ያትታል። ታዲያ አቶ መለስ የመንፈስ አባታቸውንና አሳዳጊአቸውን ኢሳያስን መስለው ቢገለጡ ምን ያስገርማል?። ወንድ ልጅ ተወልዶ ይባል የለ? ችግሩ መጨረሻው አለማማሩ ነው ሰው የትዕቢት መንፈስ ሲገባበት መውደቅ ይጀምራል በመከናወን እንዲራመድ የሚረዳውን ከእግዚአብሄር ዘንድ የተሰጠውን ድንቅ ስጦታ ማስተዋል የሚባለውን ንጥረ ነገር ያጣል ትዕቢትና ማስተዋል አብረው መኖር አይቻላቸውም። ለዚህም ነው አምባገነን መሪዎች ሁሉ በአንድ ቋንቋ የሚናገሩት በትዕቢት ሳንባ ስለሚተነፍሱ ነው ፍጻሜው ግን እንደ ባቢሎን ግንብ መፈራረስን ያስከትላል።
ወደ ዋናው ሀሳቤ ስመለስ ወደ ስደት ከመውጣቴ በፊት አንድ የቲአትር ባለሙያ ጓደኛየ የአጫወተኝን ከጽሁፌ ጋር ተያያዥነት ስላለው ላካፍላችሁ ወደድኩ።ከምርጫ 97 አንድ ዓመት ቀደም ብሎ “ስውር ጥላ”የሚል የሙሉ ጊዜ ተውኔት ጽፌ ለአንዱ ቲአትር ቤት ሰጠሁ የቲአትር ቤቱ ገምጋሚዎች ተገናኝተው በተውኔቱ ላይ መነጋገር ይጀምራሉ። ገምጋሚዎቹ ለሁለት ይከፈላሉ። የገምጋሚዎቹ ክርክር በተውኔቱ አቅም ማጣት ላይ አልነበረም። ጥያቄው የተውኔቱ መሪ ገጸ_ባህሪ አቶ መለስ ዜናዊ መሆናቸውና “ለገሰ” የሚለውን የቀድሞ ስማቸውን በቀጥታ መጠቀሜ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ የእርሳቸውንና የማፍያ ቡድናቸውን ሥራ ወለል አድርጎ የሚያሳይ ተውኔት መሆኑ ነው። በመጨረሻም “አንዳንድ ማስተካከያ ተደርጎበት እንደገና ይቅረብ’ በሚል ስክሪፕቱን መለሱልኝ ከዚህ በኋላ ከአንዳንድ ገምጋሚዎች ጋር ተገናኝተን ስንነጋገር ተስተካክሎ ይቅረብ ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? ብዬ ጠየቅኳቸው የሰጡኝ መልስ “ጠየም አድርገው ያፈጠጠ ነው ሽሮአችን እንብላበት” አሉኝ ወዳጆቼን አልተቀየምኳቸውም።ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳለ እንደወረድ ይቅረብ ብለው የሞገቱም ነበሩና። ከእነኝህ ወዳጆቼ መሀከል ከአንደኛው የቴአትር ባለሙያ ወዳጄ ጋር ቡና እንደ ወረደ ይዘን ጨዋታችንን እንደወረደ ቀጠልን በራሳችን ዓለም ውስጥ ሆነን የአራት ኪሎ ቍማርተኞችን በላናቸው ፣ቀረጣጠፍናቸው ሰውየው አንድ ወቅት ለሙያተኞች ያሉትንም አጫወተኝ።መለስ በአንድ ወቅት ይመለከታቸዋል የተባሉ የቲአትር ባለሙያዎችን ሰብስበው የወራወሩት ወሬ እንዲህ የሚል ነበር “እኔ ክላሲካል ድራማ ስትሰሩ ማየት አልፈልግም። ህዳሴ ፣ኢህአዲግ ምናምን እያላችሁ ስሩ “ ብለው ምናምንቴን የሆነ አቧራ ንግግር በሙያተኛው ሁሉ ላይ አራገፉበት። ይኼው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቲአትር ቤቱ ሁሉ ውሃ ውሃ ይሸት ጀመር። አላልኳችሁም?መለስ ኮቴ ደረቅ ናቸው።
ዘመን አይሽሬው የእነ ኤሲክለስ ፣ሶፎክለስ፣ኢሪዩፒደስ፣አርስቲፈንስ እና የሌሎችን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች መለስ በሁሉን አውቃለሁ ምኞታቸውና ትዕቢታቸው በቀይ ካርድ ቢያስፈነጥሩአቸውና የዓይናችሁ ቀለም አላማረኝም ብለው ጠራርገው ከሀገር ቢያስወጡአቸው ማን ይከለክላቸዋል ? እሳቸው የጥበብ ሁሉ አናት ናቸው!። የምን ሶፎክለስ ፣አርስቲፈንስ የመለስ የደደቢቱ የምርምር ውጤት የሆነው ደደብኛ አስተሳሰብ ከሁሉ የላቀ ነው።
እውነቱ ግን ወዲህ ነው። የእነ ሶፎክለስን ዘመን አይሽሬ ስራዎች የሆኑት ንጉሥ ኤዲፐስና አንቲገንን የመሳሰሉትን ተውኔቶች ስናይ ሰዎችን ከዕውነት ጋር የሚያጣብቁ ብሎም የሚያፋጥጡ ከተፈጥሮአዊ ህሊናችን ጋር ወግነን እንድንቆም የሚሞግቱ ሥራዎች መሆናቸውን ነው። መለስ እነዚህን ስራዎች ተመለከቱ ማለት በአንገታቸው ላይ ስይፍን መዘዙ ማለት ነው። ምናቸው ሞኝ!። ለእውነት መኖርን የመረጠው ኤዲፐስ ገና መናገር ሲጀምር በውሸት የተወጣጠረው ቆዳቸው መንተብ ፤ በሴራ የተገመዱ ጅማቶቻቸው መበጣጠስ ይጀምራሉ።ከዚህ ሁሉ ጣጣ መለስ ሁሉን አዋቂነታቸውን ተጠቅመውና ከመንፈሳቸው (his ghost) ጋር እየመከሩ መልካም ለማድረግ ባልታደሉ ጣቶቻቸው እየቦነጫጨሩ እንደ አኬልዳማ ያሉ ተውኔቶችን ቢያቀርቡልንስ ? በእነዚህ ሃያ ዓመታት የሆነው ይሄው ነው።
ሴራዎች ተመዘዙ።በትንንሽ መድረኮች በየቀበሌውና በየመንደሩ ተሰርተው ከተጠናቀቁት ብዛት ካላቸው አጫጭር ተውኔቶች ውጭ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ካገኙላቸው ተውኔቶቻቸው መካከል ኃየሎም ፣ ክንፈ ፣ ጸሐዬ /ሻለቃ/፣ይሁዲው ሙሉ ዓለም እና የቦናፓርቲዝም ቦንብ የተጣለባቸው የነስዬ ቡድን ፤ታምራት ላይኔ በመሪ ተዋናይነት የተካፈሉባቸው ጥቂቶቹ ናቸው።
እናም ክላሲካል ድራማዎች ከዕውነት ጋር ከተጣሉት ከመለስ ፊት ሞገስ የላቸውም ። በእርሣቸው ድርሰት ውስጥም በምናብ የተቀረጹ ገጸ ባህሪያት ተብሎ ነገር የለም።ቀልድ አያውቈም ።ገጸ ባህሪያቱን በውኑ ዓለም እያናገሩቸው፣ እየሳቈላቸው፣እየጨበጧቸውና እያጎረሷቸው በአስፈላጊው ጊዜና ቦታ ይሰውአቸዋል። ምስኪኖቹ ገጸ ባህሪያትም መሬት ላይ ተዘርረው ደም በደም ሲሆኑ መለስ ከነአውሊያቸው ከተቅበዘበዙበት ለትንሽ ጊዜ እፎይ ይላሉ። እስትንፋሱ የተሰረቀውን በድን እየተመለከቱም ይፎክራሉ።
ሰሞኑን በአኬልዳማ በኩል የቀረበልንም ይኼው የሃያ ዓመቱ የተውኔት መዝጊያ ነው።የሰሩትን በደልና ግፍ ሊደብቍት አልተቻላቸውም እንደ ፈሪሳውያን አውጥተው ዘረገፉት አኬልዳማ ብለውም ሰየሙት አይገርምም ትንቢትና ፍጻሜ ሲመሳሰል? ድርጅቶችን በአሸባሪነት መክሰሳቸውም ግራ ቢገባቸው እንጅ መልዕክቱ ለኢትዬጵያ ህዝብ ሃያ ዓመት ሙሉ የሰራንብህ ግፍ ይህን ይመስላል ብለውም በምጸት ተቀኙበት።ለዛሬ በዚህ ይብቃኝ ቸር ይግጠመን!።