አቡጊዳ – ስለሰላማዊ ትግል በግልጽ የተደረገ ዉይይት እንደ ሽብር ተግባር ማስረጃ ሆኖ ቀረበ !
በሽብር ስራ ተሰማርታችኋል በሚል መስረት የሌለዉ ክስ የታሰሩ፣ የአቶ አንድዋለም አራጌ፣ የአቶ እስክንድርና ነጋ እና ሌሎች ሰላማዊ ታጋዮችን ጉዳይ የሚያዳምጠዉ ችሎት፣ ዲሴምበር 24 ቀን ፣ አቃቢ ሕግ ያቀረባቸዉን ቪዲዮዎችና ኦዲዮዎች አዳምጧል።
ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ ያዳመጠዉ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ዉስጥ በይፋና በግልጽ የተደረገዉን፣ አቶ እስክንድር ነጋ በእንግድነት የተገኙበትን እና በአቶ አንዱዋልም አራጌ የተመራዉን ስብሰባ ነበር። በዚህ ስብሰባ ጋዜጣኛ እስክንድር ነጋ፣ ሰላምዊ በሆነ መንገድ እንዴት ለዉጥ ማምጣት እንደሚቻል፣ ሰፋ ያለ አሃተታ የሰጡ ሲሆን፣ በዚያ ወቅት ያቀረቡትን ፣ ለሕዝብ ሁሉ ይፋ የሆነ ፣ በሰላማዊ ትግል ላይ ያነጣጠረ ጽሁፍ፣ አቃቢ ሕግ እንደ ሽብር ተግባር መቁጠሩ ምን ያህል ሕግ መቀለጃ እየሆነ የሚያሳይ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።
ሌላዉ እንደ መረጃ የቀረበዉ ቪዲቶ አቶ አንዱዋለም አራጌ ያደረጉትን ንግግር ያዘለ አንድ ቪዲዮ ነበር። በዚህ ቪዲቶ አቶ አንድዋለም ገዢው ፓርቲ በሰላም ስልጣኑን ለሕዝብ እንዲያስረክብ የጠየቁበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀት እንዳለበት ያሳሰቡበትና የተቃዋሚ ድርጅቶች ልዩነቶቻቸዉን እጣበዉ በአንድነት እንዲሰባሰቡ ጥሪ ያቀረቡበት ቪዲዮ ነበር።
አቃቢ ሕግ በዚህ ቪዲዮ፣ አቶ አንዱዋለም አራጌ በሰሜን አሜሪካና በመካከለኛዉ ምስራቅ የታየዉን የለዉጥ እንድቅስቅሴ በማንሳት፣ ንግግራቸዉን መጀመራቸዉ ነበር እንደ «ሽብር» ተግባር ለማሳየት የሞከረዉ።
በቱኒዚያና በግብጽ የተደረጉ ሕዝባዊ፣ ሰላማዊ እንቅስቅሴዎች በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸዉ ፣ በሰለጠነዉና ዲሞክራቲክ በሆነዉ አለም የተሞገሱና የተደገፉ እንቅስቃሴዎች እንጂ ፣ እንደ ሽብር ተግባር የተቆጠሩ እንዳልሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን የሕወሃት/ኢሕአዴግ አቃቤ ሕግ፣ ለምን ስለግብጽና ስለቱኒዚያ አነሳችሁ ብሎ ማሰሩ፣ ምን ያህል አገዛዙ የሽብርን ትርጉም ፍጹም እንዳቀለለና እንዳዛባ የሚያሳይ እንደሆነ የሕግ ተንታኞች ይተቻሉ።
አቃቤ ሕግ፣ ማንነታቸው የማያታወቅ አዉሮፓ ያሉ ሰዎች፣ አቶ አንድዋለም የሚሰሩት ሥራ ጥሩ እንደሆነ መግለጻቸውን የሚናገር፣ የተጠለፈ የስልክ ኦዲዮም እንደ ሌላ የሽብር ተግባር መረጃ አቅርቧል።
አቶ አንዱዋለም አራጌ የአንድነት ዋና ጸሃፊ ፣ ከዚያ በኋላ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ሆነዉ በሚሰሩበት ጊዜ፣ በድርጅቱ ዉስጥ ትልቅ አስተዋጾ ያደረጉ አንጋፋ የድርጅቱ መሪ እንደሆኑ ይታወቃል። እርሳቸው የሚመሩት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በየሳማንቱ የሚታተምን፣ የፍኖት ጋዜጣን የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ በየጊዜዉ በስካይፒ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የሕግ ባለሞያዎችን እንዲሁም ጋዜጠኞች እየጋበዘ በአንድነት ጽ/ቤት ዉስጥ አባላትን የማደራጀትና የማንቃት ትልቅ ሥራ እንደሚሰራ ይታወቃል።
አቶ አንዱዋለም አራጌ በአገር ዉስጥ ሆነ ከአገር ዉጭ በጣም የሚከበሩና የሚወደዱ፣ የሰላማዊ ፖለቲካ መሪ ናቸዉ። በዚህም ሃላፊነታቸው ከሁሉም አቃጣጫዎች የተለያዩ ማበረታቻዎች፣ ከአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ በየጊዜዉ እንደሚደርሳቸው መገመት አያስቸግርም። ታዲያ ይህን አይነቱን ማበረታቻ፣ ገዢዉ ፓርቲ፣ እንደ ሽብር ተግባር ማቅረቡ ፣ምን ያህል ገዢው ፓርቲ የተጨበጠ መረጃ እንደሌለው የሚያሳይ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።
ፍርድ ቤቱ ዲሴምበር 29 አቃቢ ሕግ የሚያቀርባቸዉን ተጨማሪ መረጃዎች የሚሰማ ሲሆን አቶ አንድዋለም አራጌና አቶ እስክንደር ነጋ ከኢሳት ቴሌቭዥን ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅም እንደ መረጃ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ገዥዉ ፓርቲ፣ ኢሳትን የግንቦት ሰባት ንቅናቄ አካል አድርጎ በስህተትና ያለመረጃ በመዉሰድ፣ በኢሳት ቴሌቭዥን መቅረብ የግንቦት ስባት አባልና ደጋፊ መሆን ማለት እንደሆነ፣ አኬልዳማ በተሰኘዉ አሳፋሪ ፕሮግራሙ ለማመላከት መሞከሩ ይታወሳል።
ነገር ግን ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት የሌላቸው በርካታ ግለሰቦች በየጊዜዉ በኢሳት እንደሚቀርቡ በስፋት የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርቡ የአሜሪካ ረዳት ምክትል የመከላከያ ሚኒስተርና የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካን ቻርጅ ድፌር የነበሩት፣ ወ/ሮ ቪኪ ሃደልሰን፣ በኢሳት ቴሌቭዥን ቀርበዉ በኢትዮጵያ ጉዳይ ሰፊ ቃለ ምልልስ ሰጥተዋል። ቃለ መጠይቁንም ያደረጉት በሽብር ስራ ከተከሰሱት አንዱ ከሆኑት ከአቶ አበበ ገላው ጋር መሆኑም ይታወቃል።
እነአንዱዋለም አራጌ በኢሳት መቅረባቸዉ ሽብርተኛ እንደሚያስደርጋቸዉ በመጥቀስ ፣ አቃቤ ሕግ፣ የፊታችን ሐሙስ ከተከራከረ፣ እነ ቪኪ ሃደልሰንን «ሽብርተኞች» እንደሆኑ መናገር ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል ያነጋገርናቸው ተንታኞች ይገልጻሉ።