ወያኔ ለህዳሴ ግድብ ገንዘብ ለማሰባሰብ በዱባይ አድርጎት የነበረው ስብሰባ እንዳልተሳካ ተዘገበ
ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 7 ቀን 2004 ዓም 1 በዱባይ ከተማ መራቅባት በተባለ አካባቢ በሚገኘዉ የማርየት ሆቴል ውስጥ በአንድ የወያኔ ሚንስትር ዴኤታ የሚመራ ቡድን ህዳሴ ግድብ ለተባለው ፕሮጄክት ማካሄጃ ገንዘብ ለማሰባሰብ ስብሰባ ጠርቶ የነበረ ሲሆን ወደ 100 ሺህ ኢትዮጵያዉያን ይኖሩባታል ተብሎ በሚታሰበው የአረብ ኢምሬትስ፣ ከ100 ያነሱ ሰዎች መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥን ኢሳት በትናንትናው ዜና እወጃው ዘግቦአል።
የስብሰባው አጀንዳ ወያኔ የዲያስፖራውን ህበረተሰብ በትናንሽ ጥቅማ ጥቅሞች የራሱ ምርኮኛ ለማድረግ የነደፈውን የዲያስፖራ ፖሊሲ በተባለው ረቂቅ ላይ ውይይት ለማድረግና ስለ አባይ ግድብ ተነጋግሮ ቦንድ ለመሸጥ እንደሆነ የኢሳት ዘገባ አመልክቶአል።
ውይይቱን የመሩት የወያኔ ተወካዮች የተላኩበትን መልዕክት ተናግረው እንዳበቁ ለተሰብሳቢው የጥያቄና መልስ ዕድል ሰጥተው እንደነበር የተዘገበ ሲሆን ተሰብሳቢዎች ከተጠሩበት አጀንዳ ውጪ “ለምን መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ ይገባል?፣ በሀገር ዉስጥ ያለው ቁልፍ ችግር የፍትህ መታጣት ነዉ ለምን ስለርሱ ትኩረት አልተሰጠም? መንግስት የህዝቡን ባህልና ሀይማኖት ከቁብ ሳይቆጥር ለምን የግብረሶደማዉያን ስብሰባ በሀገር ውስጥ እንዲደረግ ፈቀደ? ኢትዮጵያዉያን በአረብ አገራት አጅግ ዘግናኝ ግፍ ሲደርስባቸዉ አገዛዙ አንድም ነገር ሳያደርግ ቆይቶ አሁን ገንዘባችሁን አምጡ ሲል አያፍርም ወይ? የሌሎች አገር ዜጎች በሀገራቸዉ የተለየ ክብርና እንክብካቤ ሲደረግላቸው እኛ ግን በሀገራችን ከኤርፖርት ጀምሮ የሚደርስብን እንግልትና መከራ አሳፋሪ ነዉ ለምን? በአሁን ሰአት እናንተ በኢኮኖሚ አደግን አደግን ትሉናላችሁ እድገቱ የት ነዉ ያለው? እናንተ አደግን ትላላችሁ ግን አብዛኛዉ ኢትዮጲያዊ ያለው እኛ በምንልክለት ብር መሆኑን እንዴት ዘነጋችሁት? እኛ ብር መላክ ብናቆም ምንያህል ሰው ጦም እደሚያድር ቤቱ ይቁጠረዉ ቤተሰቦቻችን እኮ እባክሽ/እብክህ ብር ላኪና እኛም እንምጣ ነው የሚሉት፤ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጲያ ዉስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መከፋፈል እና እርስ በእርስ የመጠላላት ሁኔታ ተፈጥሮአል። ማንኛዉም ሀገር እንዲያድግ ከተፈለገ ህዝቡ አንድነት ሊኖረው ይገባል፣ ያለአንድነት እድገትና ሰላም አይኖርም፣ ይህ መንግስት ግን ህዝቡን ከፋፍሎታል ለምን? የሚሉ ጥያቄዎች መቅረባቸውን ኢሳት ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ዘግቦአል።
በተሰብሳቢዎቹ ከአጀንዳ ውጪ የተለያዩ መሠረታዊ ችግሮች ዙሪያ ጥያቄ ማንሳት ያልጣመውና ያስደነገጠው የመድረኩ ሰብሳቢ በመሃል ገብቶ ከዚህ በላይ ጥያቄ አናስተናግድም በማለት ጥያቄውን ለማስቆም ቢሞክርም በሁኔታዉ የተናደደው ተሰብሳቢ በጩሄት ተቃውሞውን እንደገለጸና የወያኔ ተላላኪዎች ባላሰቡት ሁኔታ የተላኩበትን አላማ ከግብ ሳያደርሱ ስብሰባው ያለውጤት መበተኑን ለማወቅ ተችሎአል።
በሰሜን አሜሪካ የመለስ ዜናዊ መላዕክተኛ ግርማ ብሩ ሰሞኑን በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ለማድረግ ሞክሮት የነበረው ተመሳሳይ ስብሰባዎች ታላላቅ ተቃውሞ ገጥሞት ያለውጤት መጠናቀቁን መዘገባችን ይታወሳል።