በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በወያኔ የግፍ አገዛዝ ተማሮ በራሱ ላይ ነዳጅ አርከፍክፎ በሎከሰው እሳት ለህልፈት የበቃውን ወጣት የኔሰው ገብሬን መዘከር እንደቀጠሉ ነው

በአገራችን ውስጥ የሰፈነውን ኢፍትሃዊነትና የግፍ አገዛዝ በመቃወም የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ከተሰበሰቡበት አዳራሽ ደጃፍ ላይ በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ አሰቃቂ አሟሟት ህይወቱን መስዋዕት ያደረገውን መምህር የነሰው ገብሬን የሚዘክር የተለያዩ ስብሰባዎች በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ እየተካሄደ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰኡ ዘገባዎች አመለከቱ።

በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ክፍለግዛቶች መዘከር የተጀመረው የመምህር የኔሰው ገብሬ መስዋዕትነት ባለፈው ቅዳሜ ና እሁድ (ታህሳስ 7 ና 8/2004 ዓ.ም) በሎሳንጀለስና በኒዘርላንድስ መካሄዱን የሚገልጹ ዘገባዎች፡ ያመለክታሉ በሆላንድ ርዕሰ ከተማ በአምስተርዳም በተደረገው ስነሥርዓት ላይ በከተማው የሚኖሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ወኪሎች ንግግር እንዳደረጉም ይገልጻል።

በሆላንድ በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አስተባባሪነት በተካሄደው በዚህ ሥነሥርዓት ላይ በሆላንድ የሲቪክ ማህበራት ተወካይ የሆኑት አቶ ቦጋለ ካሳየ እንደተናገሩት፤ የመምህር የኔሰው ገብሬ መስዋዕትነት ፍትህና እኩልነት ለሚናፍቀው ለኛ ትውልድ ከፍተኛ የሆነ እዳ ጥሎ አልፎአል። ይህንን የተጣለብንን እዳ ለመወጣት ደግሞ “ከራሳችን ጋር በመታረቅ፣ ጭቆናን አምርረን ልንቃወምና ወያኔ በትናንንሽ ጥቅማጥቅሞች እየደለለ ሊከፋፍለን የሚያደርገውን ጥረት በጋራ መክተን አድሎአዊነትን፤ ጭቆናንና ግፍን በመዋጋት በአገራችን ስላምና ብልጽግና ለማምጣት ሁላችንም በጋራ ልንቆም ይገባል ስለዚህም ሁላችንም ለፍትህና ለእኩልነት የሚደረገውን ትግል የማገዝ ሃላፊነታችንን በመወጣት መምህር የኔሰው የተሰዋለትን አላማ ከግብ ማደረስ አለብን” ብለዋል።

በመቀጠልም የተናገሩት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ህብረት አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ “የኔሰው የፈጸመው ገድል ከእነ አጼ ቴዎድሮስና አቡነ ጴጥሮስ የሚተናነስ አለመሆኑን ገልጠው፣ በየኔሰው ሞት የሽብረተኛው አምባገነን አገዛዝ ትክክለኛ ማንነት ተጋልጦአል ካሉ ቦሃላ የኔሰው በህይወቱ በከፈለው መስዋትነት አገራችን ያለቺበትን አስከፊ ሁኔታ ተገንዝበን አሁን ከገባንበት ትርምስ ለመውጣትና የኔሰው ጥሎልን ያለፈውን ጥሪ ለመመለስ በሰከነ መንገድ መወያየት፣ መደጋገፍ፣ የተዘበራረቁና የሚተራመሱ ሀይሎች ቋሚ መፍትሄ መፈለግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ወያኔ በግንቦት 7 አመራር አባልነትና የቤልጂዬም ተወካይነት በቅርቡ ክስ የመሰረተባቸው አቶ መስፍን አማን በበኩላቸው ሙስና፣ ዘረኝነት፣ አድልዋና ራስ ወዳድነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ ፣ የኔሰው የከፈለው መስዋትነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ የየኔሰው ጥያቄ ተመለሰ የሚባለው አሁን በስልጣን ላይ ያለውን ዘረኛ መንግስት ታግለን ስናስወግድ ብቻ ነው በማለት ገልጠዋል። አቶ መስፍን አክለውም የቱኒዚያው አምባገነን መሪ የነበሩትን የቤን አሊን አስተዳደር በመቃወም በራሱ ላይ ያንን አይነት እርምጃ የወሰደውን ሞሃመድ ቡአዚዝ ራሱን ባቀጣለበት ጊዜ የቀድሞ የአገሪቱ መሪ ቤን አሊን ሆስፒታል ድረስ ሂደው ሲጎበኙት የእኛዎቹ ግን ስሙን ለማጥፋት መሽቀዳደማቸው፣ የምንታገለው መንግስት ምን ያክል እኩይ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።

የየኔሰው ገብሬን መስዋዕትነት ለመዘከር ሆላንድ ላይ በተዘጋጀው በዚህ ሥነሥርዓት ላይ የተለያዩ ሰዎች ስለወያኔ አስከፊነትና በአገራችን ስለሰፈነው ኢፍትሃዊነት በመዘርዘር ሁሉም አምርሮ መነሳት እንዳለበትና ለነጻነት የሚካሄደውን ትግል ማጠናከር እንደሚኖርበት ጥሪ አስተላለፈዋል።