ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ለነጻነት የሚታገሉት አርበኞች ላይ የፈበርከውን የፈጠራ ወንጀል ለማጠናከር የሃሰት ምስክር ሆነው የሚቀርቡት ሁሉ የሚጠየቁበት ቀን እንደሚመጣ ሊያውቁት ይገባል ሲል ግንቦት 7 መግለጫ አወጣ
ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በሚያቀነባበረው የፈጠራ ወንጀል በገንዘብ ወይም በሌላ ቁሳዊ በረከት ተገዝተው በሃሰት ለመመስከር የተመለመሉና ስልጠና የወሰዱ ሰዎች ሁሉ ታሪክ ይቅር የማይል ወንጀል እየሰሩ መሆናቸውን ሊያውቁ ይገባል ሲል መግለጫ አውጥቶአል።
ዕሁድ ታህሳስ 8 ቀን “ ሃሰተኛ ብርቱ ወንጀለኛ “ በሚል ርዕስ ግንቦት 7 ያወጣው ይህ መግለጫ፤ ለራሳቸው፣ ለአገራቸውና ለወገናቸው ነፃነት ሲሉ የተቃውሞ ድምጽ ባሰሙ ወገኖቻችን ላይ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በህግ ሽፋን የሚያደርሰው በደል በዝቶ ሕዝብ መሸከም ከሚችለው በላይ ሆኗል ካለ ቦኋላ “ወገኖቻችን በዘረኞች መደብደባቸው፣ መሰደባቸውና መዋረዳቸው ሳያንስ ለዘረኞቹ የፈጠራ ክስ ምስክር ለመሆን ቃለ-መሃላ የሚፈጽሙ፤ በፈጣሪ ስም የሚምሉ ሰዎችን ማየት ህሊና ሊታገሰው ከሚችለው በላይ የሚያሳምም ስቃይ ሆኖአል” ብሎአል።
“በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ዘመን እያንዳንዱ የፍርድ ቤት ውሎ ወደ አሳዛኝ ትያትር መድረክነት መቀየሩ የታወቀ ነው“ የሚለው የግንቦት 7 መግለጫ በትያትሩ ውስጥ እየሆነ ያለው ግን የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን እውነት እራሷ አደጋ ላይ ነች ፤ አገር ጭምር አደጋ ላይ ነች በማለት በዚህ ትያትር የሚተውን ሁሉ በሰው ሕይወት፣ በእውነትና በአገር ላይ ተጨባጭ የሆነ አደጋ እየፈጠረ እንደሆነ ይታወቅ ሲል የቲያትሩ ተዋኒያንን አስጠንቅቆአል።
መግለጫው በማያያዝም “ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የመለስ ዜናዊ ተላላኪዎች በሚያዟቸውና በአሰለጠኗቸው መንገድ በመሃላ እየዋሹ የሚመሰክሩ ሰዎችን መከታተልና መመዝገብ ተገቢ ነው ብሎ ያምናል ። እነሱም ተገቢውን ፍርድ የሚያገኙበት ጊዜ ይመጣል። ለጥቅም ሲሉ በሃሰት ለመመስከር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ማዋረድ፣ መናቅና ማግለል ተገቢ እና ከስነ-ምግባር አኳያ ተቀባይነት ያለው ተግባር ነው ብሎ ያምናል” ብሏል።