የህወሀት ጄኔራሎችና ኩባንያቸው ኢፈርት በጦር መሳሪያ ሺያጭ ውስጥ እንደተዘፈቁና በጎሬቤት አገር ዘረፋ እያካሄዱ መሆኑ ተዘገበ

ድርጅታቸው ህወሃትን ለድል በማብቃታቸው ለጄኔራልነት ማዕረግ የበቁት የቀድሞ “የትግራይ ታጋዮችና” የንግድ ድርጅታቸው ኢፈርት በአገር ውስጥ የሚያካሂዱትን ዘረፋ አድማስ በማስፋት ከሁለት አስርተ አመታት በላይ በጦርነት እየተታመሰች ካለቺው ጎሬቤት አገር ሱማሊያ ተገንጥላ ካለቺው ፑትላንድና ከአዲስቷ የደቡብ ሱዳን ተለይታ የራሷን አስተዳደር ለመመስረት ትግል የጀመረቺውን የጁባ አማጽያን ጋር በመሻረክ ከፍተኛ ጥቅም በሚያስገኝ ዘረፋ ላይ መጠመዳቸውን የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን ኢሳት ዘገበ።

ኢሳት ታማኝ ምንጮቹን በመጥቀስ እንደዘገበው፤ የህወሀት ጄኔራሎች ከኢትዮጵያ ህዝብ በተሰበሰበ ግብር የተገዙትንና የመከላከያ ሚኒስቴር ንብረት የሆኑትን የጦር መሳሪያዎች ለፑንትላንድ እና በቅርቡ ነጻነቷን ካወጀቺው ደቡብ ሱዳን ለመገንጠል እየታገሉ ላሉ የጦር መሪዎች በከፍተኛ ደረጃ በመቸበቸብ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብት በማጋበስ ላይ ናቸው።

የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ የሚከናወነው በጥሬ ገንዘብ እጅ ለእጅ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከሽያጩ ስለሚገኘው ገንዘብ ምንም መረጃ የለውም ።

በአገሪቱ መከላኪያ ከሎጂስቲክስ አቅርቦት እስከ ጦር መሳሪያዎች ግምጃ ቤት ያሉት የሃላፊነት ቦታዎች በሙሉ በህወሀት አባላት የተያዙ በመሆናቸው፣ የኦዲት ስራ ለመስራትና የንብረት ቁጥጥር ለማድረግ አስቻገሪ ሆኗል ያለው የኢሳት ዘገባ፤ በጄኔራልነት ማእረግ የሚጠራው ሳሞራ የኑስ ከአመት በፊት የመከላከያ ወጪ ኦዲት እንዲደረግ ሲጠየቅ “የትኛው ባለስልጣን ነው መከላከያን ኦዲት ሊያደርገው የሚችለው? በማለት ዝቶ እንደነበር መዘገቡን አስታውሶአል።

እንደኢሳት ምንጮች መረጃ የህወሀት ጄኔራሎች ለፑንትላንድ እና ለጁባ የጦር አበጋዞች የሚሸጡዋቸው የጦር መሳሪያዎች በአብዛኛው ፣ በትከሻ ላይ የሚተኮሱ ላውንቸሮች፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ጥይቶች፣ የተለያዩ የእጅ ቦንቦች እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ናቸው ። በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ አንድ ክላሽንኮቭ እስከ 12 ሺ ብር በመሸጥ ላይ ነው የሚለው የኢሳት ዘገባ የህወሀት ባለስልጣናት ከሸጡዋቸው በሺዎች የሚቆጥሩ የጦር መሳሪያዎች በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንዳካበቱ መረጃዎች ያመለክታሉ ብሎአል።

የወያኔ ጀኔራሉች በሁለቱ ጎሬቤት አገሮች እያጧጧፉ ያለውን ዘረፋ የዘገበው ኢሳት በፑንትላንድ እና በጁባ ከሚቸበችቡት የጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ፣ የህወሀት ኩባንያ የሆነው መስፍን ኢንጂነሪንግ ደግሞ በጦርነቱ ጊዜ በእነዚህ አገሮች የወዳዳቁትን የጦር መሳሪያዎች እና የተለያዩ ብረታ ብረቶች በመሰብሰብ መቀሌ ወደ ሚገኘው ፋብሪካው እያጋዘ መሆኑን ገልጾአል። መስፍን ኢንጂነሪንግ የወዳደቁ የግብርና ብረታ ብረቶችን፣ ከፈራረሱ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሀይል ማመንጫዎች የተገኙ የአርማታ ብረቶች፣ የወዳደቁ መኪኖች፣ የከባድ ጦር መሳሪዎች የተሰሩባቸውን ብረቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ የእንጨት ውጤቶችን የህወሀት እህት ኩባንያ በሆነው ትራንስ ኢትዮጵያ እየጫነ በመውሰድ ላይ ነው ያለው ኢሳት መስፍን ኢንጂነሪንግ ለፑንትላንድ እና ለጁባ የጦር አለቆች ክፍያ መፈጸምና አለመፈጸሙ እንዳልታወቀ ገልጾአል።

ይሁን እንጅ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ከዩክሬን እና ከቱርክ ያስመጣ የነበረውን የብረታ ብረት አቅርቦት በመቀነስ፣ ያለቀረጥ ከሁለቱ አገሮች እያስገባ ያለው ብረታ ብረት የተለያዩ ድጎማዎች የሚደረጉለትን ኩባንያ እጅግ ትርፋማ ሊያደርገው ይችላል ብሎአል።

የፑንትላንዱ መሪ አብዱረህማን ሙሀመድ ፋሩሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመላለስ ኢሳት በዘገባው ገልጾ በመለስ ዜናዊ የሚመራው የወያኔ አገዛዝ በአንድ በኩል ጁባ ላንድ የራሷን አስተዳደር ለመመስረት የጀመረቺውን ትግል የማይደግፍ እየመሰለ በጎን ግን በጄነራሎች አማካይነት ለጦር መሪዎቹ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሺያጭ በማጧጧፍ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በማጋበስ ላይ መሆኑን አጋልጦአል።