ሃሰተኛ – ብርቱ ወንጀለኛ!!!

ከግንቦት 7 የተሰጠ መግለጫ ታህሳስ 8  2004

ሰለ ሃሰት – በተለይም በሃሰት ስለመመስክር – አባቶቻችንና እናቶቻችን ያቆዩልን በርካታ ሥነ-ቃሎች አሉን። አንዱ በአርዕስትነት የተጠቀምንበት “ሃሰተኛ፤ ብርቱ ወንጀለኛ!” የሚለው ነው።

ለራሳቸው፣ ለአገራቸውና ለወገናቸው ነፃነት ሲሉ የተቃውሞ ድምጽ ባሰሙ ወገኖቻችን ላይ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በህግ ሽፋን የሚያደርሰው በደል በዝቶ ሕዝብ መሸከም ከሚችለው በላይ ሆኗል። ወገኖቻችን በዘረኞች መደብደባቸው፣ መሰደባቸውና መዋረዳቸው ሳያንስ ለዘረኞቹ የፈጠራ ክስ ምስክር ለመሆን ቃለ-መሃላ የሚፈጽሙ፤ በፈጣሪ ስም የሚምሉ ሰዎችን ማየት ህሊና ሊታገሰው ከሚችለው በላይ የሚያሳምም ስቃይ ነው።

በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ዘመን እያንዳንዱ የፍርድ ቤት ውሎ ወደ አሳዛኝ ትያትር መድረክነት መቀየሩ የታወቀ ነው። በትያትሩ ውስጥ ግን የእውነት እየሆነ ያለ ነገር ግን አለ። የሰው ሕይወት አደጋ ላይ ነው። እውነት አደጋ ላይ ነች። አገር አደጋ ላይ ነች። በዚህ ትያትር የሚተውን ሁሉ በሰው ሕይወት፣ በእውነትና በአገር ላይ ተጨባጭ የሆነ አደጋ እየፈጠረ እንደሆነ ይታወቅ።

የሰውን ሕይወት፣ አገርምና ነፃነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጨዋታ ሊኖር አይገባም።

የመለስ ዜናዊ ቅጥረኞች ለሚፈጥሯቸው ክሶች ተስማሚ የሆኑ የሃሰት ምስክሮችን ማሰልጠን ራሱን የቻለ ሙያ እየሆነ ነው። “የሃሰት ምስክሮች ሥልጠና” የሥልጠና መርሃ ግብርና የሥልጠና ማንዋል ሳይቀር ተቀርጾለታል፤ በጀት ተመድቦለታል። ልክ እንደ ሙያ ስልጠና ሆቴል ውስጥ በሃሰት መመስከርን በቲዎሪም በተግባርም ተለማምደው ዋሾ መስካሪዎች ይመረቃሉ።

ይህ እጅግ አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊት ማኅበረሰባችን የቆመበትን “ይሉኝታ” የተባለውን የስነ-ምግባር ምሰሶ ንዶታል። “ተመራቂ ዋሾ መስካሪዎች” ያላዩትና ያልሰሙትን ነገር እንዳዩና እንደሰሙ አድርገው በፈጣሪ ስም ምለው ይዋሻሉ።

በውሸት መመስከር ጥቂት ጥቅሞችን ያስገኛል፤ ሆኖም ግን የማያልቅ ፀፀትና ለትውልድ የሚተርፍ ሃፍረትን ያከናንባል። በተለይም ደግሞ በሃሰት ምስክርነት የአምባገነኖች መጠቀሚያ መሆን እና ንጹሃን ዜጎችን ለሰቆቃ መዳረግ ይቅርታ የሌለው ወንጀል ነው።

ሃሰት እያደር ይቀላል። ሃሰተኛም ይቀላል፤ ይዋረዳል። ሃሰተኛ ምስክር በገዛ ራሱ ቤተሰቦች ሳይቀር የተናቀ ይሆናል። ከሁሉም በባሰ ሃሰተኛ ምስክር በገዛ ራሱ ህሊና የተናቀ ሰው ይሆናል።

በአንፃሩ ደግሞ “እውነት የተናገረ በመርከብ የተሻገረ” ይባላል። በእንዲህ ዓይነት ወቅት እውነትን ለመናገር ድፍረት ያገኙ እነሱ ታላላቆች ናቸው። ዛሬ እውነትን በመናገራቸው ጥቃት ይደርስባቸው ይሆናል። ሆኖም በሕዝብ ተከብረው፤ ከህሊናቸው ጋር ታርቀው ኮርተው ይኖራሉ። ቢሞቱም ስማቸው ከመቃብር በላይ ነው።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የመለስ ዜናዊ ተላላኪዎች በሚያዟቸውና በአሰለጠኗቸው መንገድ በመሃላ እየዋሹ የሚመሰክሩ ሰዎችን መከታተልና መመዝገብ ተገቢ ነው ብሎ ያምናል። እነሱም ተገቢውን ፍርድ የሚያገኙበት ጊዜ ይመጣል። ለጥቅም ሲሉ በሃሰት ለመመስከር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ማዋረድ፣ መናቅና ማግለል ተገቢ እና ከስነ-ምግባር አኳያ ተቀባይነት ያለው ተግባር ነው ብሎ ያምናል።

የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በሽብረተኝነት የፈጠራ ክስ በሚያንገላታቸው ወገኖቻችን ላይ በሰየመው የይስሙላ “ችሎት” ቀርበው መሃላ ፈጽመው እንዲዋሹ የሰለጠኑ ሰዎች የሚያደርጉትን ማየት በእጅጉ ያሳፍራል። ኅብረተሰባችንም ለእንዲህ ዓይነቶች ውሸታም ምስክሮች የሚሰጠው አንዳችም አዘኔታ ሊኖር አይገባም። “ተገድጄ ነው የመሰከርኩት” ማለት ተቀባይነት ያለው ምክንያት አይደለም። እነዚህ ሰዎች በመሃላ ዋሽተዋልና ስብዕናቸውን አርክሰዋል። የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት ለገዳዮች አሳልፈው ሰጥተዋልና፤ ከገዳዮች ለይተን አናያቸውም።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ