ዝርፊያም ዘረኝነትም፤ በቃን !!!!
የኢትዮጵያን ፓለቲካና ኢኮኖሚ ተቆጣጥረው የድሆችን ደም እየመጡ ያሉት የትግራይ ገዢ ጉጅሌ አባላትና ሎሌዎች እአአ ከ1990 መጀመሪያ እስከ 2007 መጨረሻ በነበሩት 18 ዓመታት ውስጥ 8.3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ ማሸሻቸው የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሃግብር (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) በጥናት ማረጋገጡን ይፋ ካደረገ አንድ ዓመት አልሞላውም።
ስምንት ቢሊዮን ሶስት መቶ ሚሊዮን (8.3 ቢሊዮን) የአሜሪካ ዶላር ማለት ዜናው በተነገረበት ወቅት 150 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ነበር። ይህን ያህል መጠን ባለው ገንዘብ ደግሞ 50, 000 የጤና ጣቢያዎችን ወይም 150, 000 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መሥራት ይቻል እንደነበር በጊዜው ተወስቷል።
አንድ መቶ አምሳ ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር፣ በወሬው ብቻ የኢትዮጵያን ሕዝብ እያራቆተ ያለውን የአባይ ግድብ ወጪን ሸፍኖ በአዋሽና በተከዜ ወንዞች ላይ ለምግብ የሚሆኑን እህሎችን ለምናመርትበት መስኖ ሥራ የሚያገለግሉን አራት ተጨማሪ መለስተኛ ግድቦችን ይሰራ እንደነበር በወቅቱ ተዘግቧል።
ያኔም ቢሆን “የዩ.ኤን.ዲ.ፒ ጥናት የተሟላ ላይሆን ይችላል፤ ዘረፋው ከዚህ በላይ ነው” ያሉ ነበሩ። “የዩ.ኤን.ዲ.ፒ ጥናት ባላካተታቸው ቅርቦቹ ዓመታት ዘረፋው በዝቷል” በማለት የተከራከሩ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ትክክል የነበሩ መሆናቸው የሚያረጋግጥ ተጨማሪ መረጃ ሰሞኑን ይፋ ሆኗል።
የዓለም የፋይናንስ ኢንቴግሪቲ (Global Financial Integrity) ባደረገው ጥናት መሠረት እአአ ከ2000 መጀመሪያ እስከ 2009 መጨረሻ ባሉት 10 ዓመታት ውስጥ 11.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ ወጥቶ መቅረቱ አረጋግጧል።
አስራ አንድ ቢሊዮን ሰባት መቶ ሚሊዮን (11.7 ቢሊዮን) የአሜሪካ ዶላር ማለት በአሁኑ ምንዛሪ 202.2 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ነው። አገሪቱን ከጫፍ እስከጫፍ በባቡር ለማገናኘት ያስፈልጋል ተብሎ የተነገረን የገንዘብ መጠን 170 ቢሊዮን ብር ነው። የተዘረፈው 202 ቢሊዮን ብር ነው።
እአአ በ2009 – በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ – የተዘረፈው መጠን 3.26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማለትም 56.34 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ነው። ይህ ደግም በ2007ም ሆነ በ2008 ከተዘረፈው የገንዘብ መጠን ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ይበልጣል። በ2009 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የወጪ ንግድ 2 ቢሊዮን ያህል ነበር። የተዘረፈው ገንዘብ ከአጠቃላዩ የወጪ ንግድ በምን ያህል መጠን እንደሚበልጥ ልብ ይሏል!
የመለስ ዜናዊ ዘረኛና ዘራፊ አገዛዝ እየተደራረቡ የመጡበትን የሙስና ክሶችን ማስተባበል ከማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ እያቅማማም ቢሆን ዘረፋ መፈጸሙን አምኖ በሌሎች ላይ ማላከኩን ተያይዞታል። በዚህ ረገድ ምዝበራው እየተደረገ ያለው “በንግዱ ማኅበረሰብ አካላት በተለይም በወጪና ገቢ ንግድ በተሰማሩ ነጋዴዎች በሚቀርቡ የሃሰት ደረሰኞች ነው” የሚል ማደናገሪያ እያቀረበ ነው።
ይህ ማደናገሪያ እውነትነት አለውን?
አዎ። እውነትነት አለው። ደረሰኝ በማምታታት የኢትዮጵያ ሃብት እየተዘረፈ መሆኑ መለስ ዜናዊ ከመናገሩ በፊትም የታወቀ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን እዚህ ላይ ሁለት አበይት ጥያቄዎችን ማንሳት ያስፈልጋል።
- የአገሪቱ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ዋጋ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሆኖ እያለ ደረሰኝ በማምታታት ብቻ እንደምን “የተጣራ” 3.26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማጭበርበር ይቻላል? እንዴት ዓይነት የሂሳብ፣ የጉምሩክ እና የንግድ ሥርዓቶች ናቸው ይህን ዓይነቱን ግዙፍ ምዝበራ “ማየት” የማይችሉት? ወይስ ከንግዱ በተጨማሪ ገንዘብ የሚወጣበት ሌላም መንገድ አለ?
- በደረሰኝም ሆነ በሌላ መንገድ ለዘረፋ መንገድ የተመቻቸለት ነጋዴ ማነው? የኤፈርት አስራ አምስት፣ የደጀና ኢንዶውመንት ሰባት እንዲሁም በአክሲዮን ሽፋን የተቋቋሙ ሠላሳ በድምሩ አምሳ ሁለት ግዙፍ የወያኔ ኩባንያዎችም “ነጋዴዎች” ተብለው ነው የሚጠሩት?
ቀድሞ የዩ.ኤን.ዲ.ፒ አሁን ደግሞ የዓለም የፋይናንስ ኢንቴግሪቲ ጥናቶች ውጤት ይፋ መደረጋቸው ጠቃሚ ነገር ነው። እነዚህ ሁለት ጥናቶች የመለስ ዜናዊ አገዛዝን ዓይን ያወጣ ዘረፋን ሙሉ በሙሉ ይገልፃሉ ማለት ግን አይደለም። ገና ብዙ መመርመር ያለባቸው ነገሮች አሉ።
- እውን ሰነዶች እንደሚያሳዩት፣ ለም መሬታቶቻችን ለቻይናና አረብ ቱጃሮች ለ99 ዓመታት የተሰጣቸው በሄክታር ከ10 ዶላር ባነሰ ሂሳብ ነው፤ ወይስ ቀሪውን በእጅ አዙር የሚቀበል አለ?
- እስከዛሬ በልማት ርዳታ ስም የገባው ተሰፍሮ የማያልቅ ገንዘብ በምን ሥራ ላይ ዋለ? አሁንስ በምን ላይ እየዋለ ነው? ያ ሁሉ ገንዘብ የምናያቸውን መንገዶች ብቻ ነው የሚሠራው፤ ወይስ እነሱም የተሰሩት “ለአሳይቶ መለመኛነት” ነው?
- በግድብ ግንባታ ስም ከድሃው የተሰበሰበውና እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብ በተመሳሳይ መንገድ ከአገር ላለመውጣቱ ወይም አገር ውስጥ ሆኖም ላለመዝበሩ ምን ማረጋገጫ አለን?
- በየአመቱ ይኸን ያህል ገንዘብ እያሸሹ ያሉ ሰዎች ከተሞች ውስጥ ሕንፃ የሚገነቡት ድሃውን “እንቁልልጭ” ለማለት ነው፤ ወይስ የድሆች ጎጆዎች በትዕዛዝ ፈርሰው ህንፃዎቻቸውን ለመኖሪያነት በማከራየት ሌላ ዘረፋ ለማካሄድ?
- ዋነኛው ጥያቄ ደግሞ ይህ ነው። ከዚህ ሁሉ ዝርፊያ ተጠቃሚዎቹ እነማን ናቸው? ምን ያህል ናቸው? ተጎጂዎቹስ እነማን ናቸው? ምን ያህል ናቸው?
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ንብረታችን ሲመዘበር፤ የድሃው አጥንት ሲጋጥ በዝምታ ማለፍ የለብንም ብሎ ያምናል። በተጨማሪም የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ዝርፊያን ለዘረኛ ዓላማው ማስፈፀሚያነት እየተጠቀመ ስለሆነ አገዛዙ ሳይወገድ ዝርፊያን ማቆም አይቻልም የሚል እምነት አለው። በአገራችንና በሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ዝርፊያ ለከት ማጣት ያንገበገበን ሁሉ ትኩረታችን ማረፍ ያለበት የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝን በአስቸኳይ ማስወገድ እና በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ የሰፈኑበት ሥርዓት መገንባት ነው ብሎ በጽኑ ያምናል።
ስለሆነም ግንቦት 7 “ዝርፊያ በቃን!!!” ሲል “የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በቃን!!!” ማለቱ ጭምርም እንደሆነ ማስገንዘብ ይወዳል።
በዘረኛ ዘራፊዎች መገዛት በቃን!!!!
በቃ!!! ጋዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጊዴስ!!!