‘ውዳሴ’ ወ በረከት
አቶ በረከት ስምዖን መጽሀፍ አሳተመ ሊያስመረቅም ነው የሚል ዜና ከወደ ሸገር ሰማንና ተደመምን ። እ ህ ህ ም አልን። የአረም እርሻን ያስታውሷል ! የደርጉ ካሳዬ አራጋው በዘመነ ደርግ መገባደጃ የሆነ መጽሀፍ ጽፈው ነበር እናም እቀድሞው ወመዘክር አግኝቼ ሳነበው ለአማርኛ አስተማሪዬ አዘንኩላቸው ፤ ለካንስ በእነ ካሳዬ አንጻር እርሳቸው ሊቅ ነበሩና ! ዛሬ ደግሞ ምስጋና ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን ይሁንና የወረቀት ዋጋ አልቀመስ ብሎ ምንቸቶቹ ደራሲያኖቻችን ብዕሮቻቸውን አግተው ጋኖች ደግሞ ‘ይጽፉ’ ያዙ ።
ለማንኛውም ዜናውን እንደሰማሁ ወደ አዕምሮዬ የመጡ አንዳንድ ጉዳዮችን ላንሳ። መጀመሪያ የጋዳፊ አረንጓዴ መጽሀፍ እፊቴ ድቅን አለ። ጋዳፊ ሊቢያን አመጽ ወጥሮ እየለበለባት መጽሀፋቸውን አንግበው እራሳቸው የተበተቡትን ስንክሳር ያነበንቡ ነበር ። አቶ በረከት እልም ያሉ እልህኛ ሰው እንደሆኑ ብዙ ሰው ያውቃል ይህ እልሃቸው እንደ ጋዳፊ የራሳቸውን የፓለቲካ ፈሊጥ እንደ ጽሁፍ በመጽሀፍ ቢጤ እንዲደራርቱት የማያደርግበት ምክንያት የለውምና ለወዳጆቻቸውም እንደው ቁም ነገር ቢገኝበት ብለን ለምናነበውም ኤጭ እንዳያሰኝ እፈራለሁ። ለዚህ ማሳያ በምርጫ 97 የፓለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ጊዜ አቶ በረከት ሲያቀርቡዋቸው የነበሩ ሀሳቦችን መለስ ይበሉና ያስታውሱ። ፓርቲው የከሰረባቸውንና በህዝብ ተአማኒነት ያጣባቸውን የዲሞራሲና ሰብአዊ መብት ችግሮች እርሳቸው እንደ ስኬት አድርገው ጣታቸውን ቀስረው ይሟገቱባቸው ነበር። እዋናው ችግር ያለው አቶ በረከት እንዚያን ለ15 ዓመታት በቲቪ ሲያስነበንቡዋቸው የነበሩ ድሎች ህዝቡ ‘ቁጩ’ እንደሆነ ማወቁ እርሳችው ደግሞ የፓለቲካ ድርሰታቸውን የእውነቶች ሁሉ እውነት አድርገው ማመናቸው ነበር። ከሁሉም ከሁሉም እንደየ አቅሚቲ በሎሌዎቻቸው በስሱ ስትበተን የነበረችው ‘በረከት መጽሀፍ ትራሱ’ ማሞካሻ በችኮና ደረቅ የመከራከሪያ ዘይቤአቸው ገደል መግባቷ ነው ፤ ቡግናዎች ከእኛ ቀድመው ይህን አውቀው ይሆን ምርጫውን በዜሮ የሸኙዋቸው?
በረከት መጽሀፉን ጻፈ አስመረቀም መባሉን ስንሰማ ዋናው አስደማሚው ጉዳይ እንዴት አድርጎ የሞራልን የግብረ ገብነትን (እንጥፍጣፊም ከቀረ እነርሱ ዘንድ ) ነገር አስታረቀው የሚለው ነው። እነ አቶ በረከት በስልጣን በቆዩበት አመታት የተባ ብዕር አለው ብለው የሚያስቡትንና ህዝባዊውን አስተሳሰብ ይገዛል ብለው የፈሩትን ሁሉ ከፈርኦን ቅናት በላቀ የብቀላ ስሜት ሲያስሩ፤ አንዳንዱን ሲገድሉ የተቀረውን ከሀገር ሲገፉ ነው የኖሩት አሁንም ያሉት። መጽሀፍ የሚጽፍ ሰው ደግሞ በሀሳብ ተሟግቶ የሚያሸንፍ ያም ባይቻል የሚሞክር አይነት ሰው ነው እንበል። እንዲህ የዳጎሰ መጽሀፍ የከተቡ ሰው ይህን ሁሉ አመት ተኝተው ኖሯል ብ ዕረኞችን በጉልበት ሲፋለሙ የነበሩት ወይስ የብዕር አድባር ስትለግም የጉልበቱ አማራጭ እግንባር ላይ ተሰድሮ ቆይቶ? ቀድሞውኑስ ይሄ የብዕረኛነት አቅም ከነበረ ጉልበትን ምን አመጣው? ከያዙት የመንግስት ስልጣን አኳያ የመጻፊያ ሜዳው አድማስ የሚገድበው አይነት አልነበረም አዲስ ዘመኑም ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣም፤ ሪፓርተርም አምድ አይነፍጉም ነበር።( በነገራችን ላይ የሀሳብ እጥረት አስቸጋሪ ጉዳይ ነው ። ህወሃት ነጻ ጋዜጦችን በራሳቸው መንገድ ሊሞግታቸው ሞክሮ የራሱን ነጭ ለባሽ ነጻ ጋዜጦች ሞክሮ አልሆነለትም፤ ኔሽን ጋዜጣን ያስታውሱ።) ለማንኛውም ለአቶ በረከትን በሞራል አንጻር መሞገት ተቃዋሚ ወጣቶችን በአልሞ ተኳሽ አስገድለው ሲያበቁ ‘ባንክ ሲዘርፉ ነው የተገደሉት’ የሚለውን ሙታንን እንኳን ሰላም የሚነሳ ክሳቸውን ላስተዋለ እጅግም አስፈላጊ ስላልሆነ እዚሁ እንተወው።
ምናልባትም የአቶ በረከት የዛሬው ጸሀፊነት እስብዕናቸው ውስጥ የሚርመሰመሰውን አጉል ቅናትም ያሳይ ይሆናል። በብዙ በጉልበተኛ መንግስታት ስር ባደሩ ህዝቦች ታሪኮች ይሄ ክስተት የተለመደ ነው። ፓለቲከኞች በኪነ ጥበብ ይሁን አርክቴክቸር፤ ስነ ጽሁፍ ይሁን የተፈጥሮ ሳይንስ ሕዝብን ያስደመሙ ባለሙያዎች ላይ ከፓለቲካ ባላንጣዎቻቸው ያላነሰ ጥላቻ ያድርባቸዋል። የናይጄሪያ የቀድሞ ጉልበተኛ ሳኒ አባቻን ያስታውሱ ፤ አለም ደግማ የማትወልደውን ጸሃፊውን ኬን ሳሮ ዊዋን በአገር ክህደት ወንጅሎ ለእርድ ለማድረስ ሁለት ወራት አልወሰደበትም። አንዳንድ አምባገነኖች ደግሞ ብዕርን ከመፍራታቸው የተነሳ በስደት ባህር ማዶ ያሉ ጸሃፊዎችን ሁሉ ሳይቀር ጸጥ የሚያሰኙባቸውን መንገዶች ሁሉ መቆፈራቸው አልቀረም። ለነገሩ የእኛ ሰዎችስ ከ ‘ ህዳሴ’ ግድብ በተረፈ ፈራንካ ትንሹንም ትልቁንም ኢትዮጵያ ተኮር ድረ ገጽ ለሐገር ውስጥ አንባቢ እንዳይደርስ ያምቁበት የለ? ታሪክን ወደ ኋላ ለመረመረ የአቶ በረከት ጸሃፊነት የሮማኒያውን ቻውቼስኩና ሚስቱን ‘ምርጥ ሰዓሊነት’ ፤ የሳዳምን የጢግሪስ ወንዝ ‘ ስነ ግጥሞች’ እንዲሁም አፈር ይቅለላቸውን ( ለነገሩ እመሬት አይቀበሩም ለካ የሙታን ቤተ መንግስት ውስጥ ነው ከነግርማ ሞገሳቸው አረፍ የሚሉት አፈር ይቅለላቸውን አልቦ ሊያደርጉብን) የቅርቡን የሰሜን ኮሪያውን ኪም ጆን ኢል በፊልም ፤ ዲዛይንና ጎልፍ ሳይቀር ‘ከአለም አንደኝነት’ አስበን ፈገግ ማለታችን አይቀርም። ደግመን እንበለውና ጉልበተኞች የያዙት አይጥማቸውም ሌሎች ጋር ያለው የፈጠራ ችሎታ በተለይም ሕዝባዊ ተቀባይነት ነው አንጀታቸውን የሚያደብነው።
‘ የሁለት ምርጫዎች ወግ’ አስቂኝ ተቃርኖን ከእነርዕሱ ይዞ ብቅ ብሏል። ህወሃት ምርጫን ‘የሚያሸንፍበት’ መንገድ የቸገረው ይመስል የወጉ መነሻም መድረሻም ምርጫን ማሸነፍ መሆኑ 99.6% የሸንጎ ወንበር ለያዘ ፓርቲ ዛሬም ድረስ የሚከነክነው እረፍት የነሳው ነገር እንዳለ ያሳያል ። የሆነ ጉልበተኛ ቆንጅየ ሚስቱን በጉልበቱ አስግብሮዋት ሲያበቃ ‘ የምትወደኝ ቢሆን ኖሮ ምን አይነት ትዳር ይሆን ነበር ?’ አይነት የውስጡን ሮሮ ! ( አንዳንዴ እንደ መንግስት ሰዎች ፓለቲካን ለማስረዳት እኛም ትዳርን እንደምሳሌ መጠቀም ይልመድብን እንጂ) ህወሃት የቅርቦቹንም ይሁን ከዚያም በፊት ተደረጉ የተባሉትን ምርጫዎች እንዴት ‘እንዳሸነፈባቸው’ ጥቅሙ እምብዛም ይሆናል እንጂ የሀሰት የምርጫ ካርዶችን በፎርጅድ ኮሮጆዎች እጃቸው እስኪዝል ሌሊቱን ሙሉ ሲሞሉ ያደሩ የወጣት ሊግ አባላትን፤ እውነተኛ የምርጫ ኮሮጆዎችን ከምርጫ ጣቢያ የዘረፉና ያጓጓዙ የፓሊስ አባላትና የመንግስት ተቀጣሪ ሾፌሮችን ሳይቀር በአስረጅነት አቅርቦ በአምስት ደቂቃ ቃለ ምልልስ ገደል ማግባት ይቻላል። እንዲያውም ለህወሃት እንደ ፓርቲ ለአቶ በረከትም እንደ መንግስት ሹመኛ የምርጫ አሸናፊነታቸው ‘ሂደቱ’ ላይ መተኛታቸው ለተቃዋሚዎቻቸውም ለደጋፊዎቻቸውም ከ 97ቱ ድንጋጤና ብርክና ትራውማ እስከ አሁንም እንዳላገገሙ ነው የሚያሳየው። ፓርቲው የሚያስፈልገው ከህዝብ ጋር የሚያስታርቀው ቢቻል ፓለቲካዊ ርዕዮት ካልሆነም መለስ ከፓርቲ ሰዎቻቸው ጋር ሲጋጩ እንዳደረጉት ማምለጫ አይነት ‘ ተሃድሶ’ ምናምን የሚል ከዚህም ከዚያም ማደናገሪያ ሀሳብ ይዘው ብቅ ቢሉ የሚመረጥ ይሆናል።
ከሁሉ ከሁሉ ደግም የዚህን ርዕዮት ትንተና ጠቃሚነት ከአቶ በረከት ተክለ ስብዕናም ጋር የሚያገኛኘው ሌላም ቸል ሊባል የማይገባ ጉዳይ ነበር እርሳቸው ወይ በአቅም ማነስ ቸል ካላሉት በቀር። አፍቃሪ ህወሃቶች ከቦናፓቲዝም ጨዋታ በኋላና የድርጅቱ ‘ጭንቅላቶች’ ከፓርቲው ተገለሉ ብለው ካዘኑ ወዲህ ፓርቲው ምላስ ብቻ ሆነ ሀሳብ ጠፋበትን ስላበዙ አቶ በረከት ሚዛኑን ለመድፋት ይታትራሉ የሚልም ግምት ነበር ። ደግሞም ተቃዋሚዎች የአቶ መለስ ‘ጎብልስ’ የሚል ትልቅ ሹመት እንደሰጧቸውም ማስታወስ ተገቢ ነው። እሹመት ስፍራ ከነሙሉ ማዕረጉና ጥቅማ ጥቅሙ መገኘትን ለአቶ በረከት አንመክርም ይመክሩን ይሆን እንጂ ። ለማንኛውም እንደው የፓርቲው ልሂቃን ሁሉ አርትኦት ካደረጉበት አይቀር ሕዝብ የተሳለቀበትን እነርሱም ያፈሩባቸውን የምርጫ ተውኔቶች የመጽሀፍ መነሻም መድረሻም አድርጎ ማቅረቡ ያ ቤት አሁንም የአዲስ ሀሳብ እጥረት እንዳለበት ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ የለውም።
መጽሀፉን አላነበብነውም እናም ከርዕሱ ባሻገር እውስጡ ምን ተብሎ ይሆን? ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በአንድ ወቅት አበክረው የሕገ መንግስቱን ባለቤቶች (መቼም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደማይባል ግልጽ ነው) የተጻፈበትን ወረቀት ዋጋ ያወጣልን ? ሲሉ እንደሞገቱት እኛም ውድ አንባቢዎች ይሄ መጽሀፍ የተጻፈበትን ወረቀት ምንዳ እንኳን ይመጥን ይሆን ስንል ከወዲሁ መጠየቃችን አይቀርም። በተለይም የተጻፈበት አላማ አንድ ቦታ ተቸንክሮ የቀረውን የህወሃት ፓለቲካ የውይይት ነፍስ ይዘራበት ይሆን አልያስ እነዚያኑ ላለፉት ሰላሳና አርባ አመታት ከዚያም ከዚህ የተለጣጠፈውን ዶግማ ሲጋቱ የነበሩት የፓርቲ አባላትና ያልታደለውን ሕዝብ መልሶ የሚያሰለችና የሚያታክት ውሃ ወቀጣ ይሆንን? ይህን ጽሁፍ ስጽፍ አንድ የሰማሁት ጨዋታ ትዝ አለኝ። ስዊዘርላንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ኤርትራውያን አንድ ወቅት ላይ የሀገራቸውን ‘የናጽነት’ በዓል ሲያከበሩ እሐገራቸው ያለውን ግፍና መከራ በዚያውም ባህላቸውን ያደንቅ ዘንድ የፍትህ ሚኒስትሩን በእንግድነት ይጋብዛሉ አሉ። የሚነገረውም ተነግሮ የተለመደው የሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ላይ ከበሮአቸውን እየደለቁ ክባቸውን ፈጥረው በእሽክርክሪት እስክስታቸውን ያስነኩታል። የፍትህ ሚኒስትሩ ጸረ ስደተኛ ኖሮ የመጣበትን ጉዳይ ትቶ “ እንዲህ አንድ ቦታ እየዞራችሁ የምትሽከረከሩትን በአንድ ቀጥተኛ መስመር ብታደርጉት አስመራ ትገቡ ነበር” ብሎአቸው አረፈው። ሰው የሚያየው ማየት የሚፈልገውን ነው የሚባለው ይሄው ነው። እኛም አቶ በረከትን እንዲሁ እንጠይቃቸው ። መጽሀፋቸው ያው የፈጀውን የቸከ የዘረኝነት ፓለቲካ ደግመው በለመዱት እሽክርክሪት እየዞሩ ይሉት ፤ የለመዱትን መወድስ ህወሃት ይደግሙበት ይሆን ወይንስ ከምሽጋቸው ወጥተው የማይደፈረውን የሀሳብ ሙግት ፈራ ተባ እያሉም ይሆን ይቀላቀላሉ?
የኋላኛውን መንገድ መርጠው ከሆነ መቸም ከአቶ በረከት እንደ ስማቸው ትልቅ በረከት ተገኘ ማለት ነው። ብረትን መጣል የመሰለ ጀግንነት የለምና። ታዲያ ይሄ መንገድ በአዲስ ዘመንና በአኬልዳማ እንደተለመደው የውሃ መንገድ እንደማይሆን እርሳቸውም አይስቱትም። ሀሳብን በጽሁፍ ማቅረብ የጠራ የንድፈ ሀሳብ ትንተና አቅምን ይህንን ላልደፈረም ፓለቲካዊ ታሪክ አይነት ጽሁፍ ለሚከትብ ደግሞ እውነት ከእርሱ ዘንድ ሲቻል ከነቃጭሏ ካልሆነም በርከት ብላ በተጨባጭ ልትኖር ይገባታል። እንደ አለመታደል ሆኖ የሐገር ቤቶቹ ገዢዎቻችን ከሁሉቱም ሆኖላቸው አያውቅም። ባለፉት ሃያ አመታት የገዚው ቡድን አባላት ወደ መድረክ ለመምጣትና ሀሳብን ለመግለጽ ባለግርማ ሞገስ ሙሉ ልብስ እንጂ ሀሳብ የሚያስፈልግ መስሎ አይታያቸውም ነበር። በ1997 የምርጫ ክርክር ወቅት ይህንን ሁላችንም ይህን ታዝበናል። በረከትም መጣ ዋልዋ ፤የፊት ለፊትን ክርክር ተሽኮርምመው ያለፉትም አቶ መለስ ሳይቀሩ ፓለቲካን በወቅቱ የተቀላቀሉትን አንዳንድ የትርፍ ጊዜ ፓለቲከኞችን ሳይቀር መሞገት ተስኖአቸው ነበር።
ይሄ አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ፤ እኔ ነኝ የማውቀው እናንተ አታውቁም አንድ ታሪክ አስታወሰኝ። ተማሪዎች ሳለን በጋራ በምንጋራው መኝታ ክፍላችን ( ዶርሚተሪ) ፍራሻችንን እመሬት አንጥፈን እናጠናለን። የፈተና ወቅት ሳይሆን አይቀርም ኮሽ የሚልም ነገር አልነበረም። ነገር ግን ሁላችንንም ከንባባችን የሚያስደነብረን የሆነ ጠንካራ የበር መበርገድ ድምጽ ሰማንና ቀና አልን። ለካንስ ጎረቤታችን ያለው ክፍል ውስጥ የሚኖር አይነ ስውር ተማሪ አልኮል ቤጤ ቀማምሶ ኖሮ በእንቅልፍ መሀል ወደ መጸዳጃ ቤት ደርሶ ሲመለስ እመኝታ ክፍሉ የገባ መስሎት ወደ እኛው ክፍል እርቃኑን እየገባ ኖሯል! እኛ እንደተደመምን ነገር ከምላሱ የማያጣው የናዝሬቱ ጓደኛችን ምን አለው ‘ ስማ የእኔ ወንድም አንተ ባታየንም እኛ የማናይህ መሰለህ ወይ እርቃንህን የመጣኽው ? ’ እርሱም ሳቀ እኛም ልባችን እስኪፈርስ ስቀን በገጠመኙ ፋታ ወሰድን። የእኛ ባለስልጣኖች እርቃናቸውን እንደቆሙ እኛ የማናውቅ ይመስላቸዋል ለዚህም የቀድሞውም የአሁኑም ድርሳናቶቻቸው ይህንን ይመሰክራሉ።
አቶ መለስ ዛሬ በህልማቸው የመጣውን ሁሉ ‘ የሻዕቢያ ተላላኪ’ ሲሉ አንዴ በሸንጎአቸው አንዴ በፍርድ ቤቶቻቸው ሊከሱ ከጥቂት አመታት በፊት የኤርትራን የነጸነት ጥያቄ የተረዱበትን መንገድ መጽሀፍ ባሉት ድርሳናቸው ታሪክንም ፤እውነትንም፤ ፓለቲካንም ደገፍ ሳይሉ እንዳሻቸው ጭረዋል። የአቶ በረከትም የምርጫ 97 ሮሮ ለዳመጠ አሁንም በመጽሀፋቸው አሉት እንደተባለው “ ለተቃዋሚዎች ያን ሁሉ ድምጽ የሰጣቸው ነፋስ ነው” ይላሉ ያለ አንዳች ሀፍረት። በዲሞክራሲያዊ ስርዓት የህዝብ ድምጽን ንፋስም ያምጣው ሱናሚ ውጤቱን ከመቀበል የዘለለ ክርክር የእነማን እንደሆነ አለም ያውቀዋል። ታዲያስ እንዲህ እንዲህ አይነቱ ሀሳብ ላይ ለዘመናት ተኝቶ ማላዘን ሕዝብን መናቅ ራስንም ማስገመት አይሆንምን? ለነገሩ ነፋስ የተባለው ሕዝብ አንድ ቀን አውሎ ነፋስ የሆነ እንደሆነ ጋዳፊ ጭንቅ በወጠራቸው ጊዜ ለከበቡዋቸው ደመ ቁጡ ወጣቶች ያነሱትን ጥያቄ ያስነሳል “ የምታደርጉትን ታውቃላችሁን?” አሉ ተባለ ። እርሳቸው 42 አመታት የሚያደርጉትን ሳያውቁ እነዚያ ወጣቶች በዚያች ቅጽበት የሚያደርጉትን እንዲያውቁ መጠበቅ የዋህነት ነው። እኛም ቤት ይሄው አንድ ቀን መሆኑ አይቀርም። ያኔ ገዢዎቻችንን ምን ሲሉ ይጠይቁ ይሆን?
ቸር እንሰንብት
samson11 @me.com