የቴሌ ስብራት ዋልተንጉስ ዳርጌ

በማርች ወር፣ 2008 አመተ ምህረት፣ በ 22ው International Conference on Advanced Information Networking and Applications (http://www.aina-conference.org/2008/) ላይ ለመካፈል ወደ ጃፓን፣ ኦኪናዋ ሄጄ በነበረበት ወቅት፣ በኮንፍራንሱ ላይ በእንግሊዝ አገር በአንድ ዪኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ከሆነ ቻይናዊ አዛውንት ጋር ተዋወቅሁ፡፡ የትውልድ ሀገሬን ጠይቆኝ ኢትዮጵያዊ እንደሆንኩ ሲረዳ በደንብ ተግባባን፡፡ በቆይታችንም ወቅት፣ በአዲስ አበባ ጥቂት ቻይናዎችን እንደሚያውቅና ስራቸውም ስለመጪው ዘመን የቴሌኮሙኒኬሽን እና የኮምፒውተር ድሮች (Next Generation Networks) የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽንን ማማከር እንደነበር ነገረኝ፡፡ አዛውንቱ ፕሮፌሰር፣ ገራገር ፈገግታ እያሳየኝ፣ ወጣቶቹ ቻይኖች ምንም እንኳን የኤሌክትሪክ ወይንም የኮምፒውተር ምህንድስና ባያጠኑም፣ ለተሰየሙበት ሀላፊነት በቂ ልምድ እንደሚኖራቸው እምነቱን ገለጠልኝ፡፡
በአመቱ፣ በማርች ወር፣ 2009 አመተ ምህረት፣ የአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ፣ ቴክኖሎጂ ፋካልቲ፣ በኤሌክትሪክ ምህንድስና የመጀመሪያ ዙር የፒ ኤች ዲ ተማሪዎቹን ኦፕቲካል ኔትወርክ (Optical Networks) እንዳስተምርለት ጋበዘኝ፡፡ ጥያቄውን በታላቅ ደስታ ነበር የተቀበልኩት፣ ምክንያቱም በየትኛውም አለም፣ ኦፕቲካል ኔትወርኮች የኢንተርኔትና የቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርኮች የጀርባ አጥንት ስለሆኑ፣ የፒ ኤች ዲ እጩዎቹ ስለነዚህ ኔትወርኮች ቢያውቁ ለሀገሪቱ ታላቅ ጥቅም እንደሆነ ስላመንኩኝ፡፡ በዪኒቨርሲቲው ላይ እንዳልከብድ በማሰብ፣ የመጓጓዣ ወጪዬን የምሰራበት ዩኒቨርሲቲ እንዲሸፍን ጥያቄ አቅርቤ፣ ጥያቄዬም ተቀባይነት አገኘ፡፡
አዲስ አበባ እንደደረስኩ፣ ማንም መምህር እንደሚያደርገው፣ ትምህርት ከመጀመሬ በፊት፣ ወደ ዪኒቨርሲቲው ቤተመጽሐፍት በመሄድ፣ ለተማሪዎቹ ይጠቅማሉ ያልኳቸውን መጽሐፍት መፈለግ ጀመርኩ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ላስተምረው ካሰብኩት ጭብጥ ጋር በርቀት እንኳ ዝምድና ያላቸው መጽሐፍት ያገኘሁት በቁጥር ሶስት ብቻ ነበር፡፡ ያውም በእድሜ በጣም ያረጁ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፣ የመጽሐፍቱ ይዘት በፍጹም ከተማሪዎቹ ደረጃ ጋር የማይጣጣም ነበር፡፡ እንኳን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የሚያክል አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ ይቅርና፣ አንድ የቴክኒክ ትምህርት ቤት እንኳ እኔ ካገኘኋቸው መጽሐፍት ቁጥርና ይዘት የሚበልጥ በርካታ መጽሐፍት ስለ ኦፕቲካል ኔትወርክ ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ ቆይታዬ፣ ኦኪናዋ ላይ ያገኘሁት ቻይናዊ ፕሮፌሰር የነገረኝን አስታወስኩና፣ ቴሌኮሙኒኬሽን የማውቃቸውን አንዳንድ ሰዎች ስለ ቻይናውያኑ አማካሪዎች ጠየቅኳቸው፡፡ የሁሉም መልሶች ተመሳሳይ ነበሩ፣ ይሄውም፣ ቻይናውያኑ ስለመጪው ትውልድ ኔትወርኮች ምንም አይነት እውቀትም ይሁን ልምድ እንዳልነበራቸውና፣ ከችሎታቸው ጋር በፍጹም የማይመጣጠን ደመዎዝ እንደሚከፈላቸው (በወር ወደ ሁለት መቶ ሺህ ብር ገደማ) ተረዳሁ፡፡
የማስተምረው ትምህርት በቂ ጊዜ ስላልሰጠኝ፣ አዲስ አበባ በነበርኩበት ጊዜ ስለ ቻይናውያኑ ብዙም አላሰብኩም፡፡ ስራዬን አጠናቅቄ፣ ወደ ጀርመን ስመለስ ግን፣ በአውሮፕላን ላይ እያለሁ፣ የዩኒቨርሲቲው ቤተመጽሀፍት አንገብጋቢ በሆነ ትምህርት ላይ በቂ መጻሕፍት አለመሩና የቻይናውያኑ አማካሪዎች ጉዳይ አእምሮዬን በጣም ረበሹኝ፡፡ በአፕሪል 7 ቀን፣ 2009 አመተ ምህረት፣ በጊዜው የቴሌኮሙኒኬሽን የቦርድ ሊቀመንበር ወደነበሩት፣ ወደ አቶ ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ስልክ ደወልኩና፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽኑን የመጪውን ዘመን የኮምፒውተርና የቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርኮችን በተመለከተ በምችለው ሁሉ ልረዳቸው እንደምፈልግ ሀሳቤን ገለጽኩላቸው፡፡ ሰውዬውም ስልክ ስለደወልኩላቸው አመስግነውኝ፣ በምን ጉዳይ ላይ ብረዳቸው እንደሚሻል ለመወሰን እንዲረዳቸው፣ የትምህርት ደረጃዬንና የስራ ልምዴን የሚያስረዳ፣ ካሪኩለም ቪቴ እንድልክላቸው ጠየቁኝ፡፡ በዛኑ ቀን፣ በርሊን ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደውዬ፣ ላናገሩኝ አምባሳደር ለአቶ ደብረጽዮን የነገርኳቸውን ደግሜ፣ ጊዜ ካላቸውና የምሰራበትን ዩኒቨርሲቲ መጥተው ለመጎብኘት ቢወዱ፣ በደስታ እንደምቀበላቸው ገለጽኩላቸው፡፡ በአፕሪል 8 ቀን፣ 2009 አመተ ምህረት፣ ለአቶ ደብረጽዮን የጠየቁትን ዶኩሜንት ላኩላቸው፡፡
በአፕሪል 9 ቀን፣ 2009 አመተ ምህረት፣ ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ቺፍ ቴክኒካል ኦፊሰር (CTO)፣ ከአቶ ዘላለም በቀለ፣ አንድ ኢሜይል ደረሰኝ፡፡ በአጭሩ የመልዕክቱ ይዘት፣ አቶ ደብረጽዮን ካሪኩለም ቪቴዬን እንደላኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑም ለመጪው ዘመን ኔትወርኮች የሚሆኑ የ10 ሺህ ኪሎ ሜትር ፋይበር ኦፕቲክ መስመሮች በአገሪቱ ሁሉ ለመዘርጋት ቅድመ ዝግጅቱን ሁሉ እንዳጠናቀቀና፣ እኔም በዚህ ረገድ ለመርዳት የምወድ ከሆነ፣ ኦፕቲካል ኔትወርክን በተመለከተ ያለኝን ልምድ በአጭሩ እንድጽፍላቸው የሚጠይቅ ነበር፡፡
እኔም፣ ከ2002 አመተ ምህረት እስከ 2005 አመተ ምህረት፣ በካስል ዩኒቨርሲቲ እሰራ በነበረበት ወቅት፣ ኦፕቲካል ኔትወርክ አስተምር እንደነበር፣ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ፣ በኤሌክትሪክ ምህንድስናና ኮምፒውተር ሳይንስ ዲፓርትመንት ውስጥ ደግሞ የኦፕቲካል ኔትወርክ ላብራቶሪ ሲቋቋም፣ ፕሮጀክቱን በሀላፊነት እቆጣጠርና ከቤል ላብራቶሪ ጋር አብሬ እሰራ እንደነበር፤ አሁንም በምሰራበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዋናው የምርምር ትኩረቴ የኮምፒውተር ኔትወርኮች ላይ እንደሆነ፣ ጻፍኩላቸው፡፡
በአፕሪል 13 ቀን፣ 2009 አመተ ምህረት፣ ከኒሁ ሰው ሌላ መልዕክት በኢሜይል ደረሰኝ፤ ለጥያቄያቸው ፈጣን መልስ ስለሰጠኋቸው አመስግነው፣ በምን መልክ አብሬያቸው ልሰራ እንደምፈልግ (Mode of Engagement) ጠየቁኝ፡፡ ለጥያቄያቸው መልስ ከመስጠቴ በፊት በደንብ ያሰብኩባቸው ነጥቦች የሚከተሉት ነበሩ፣
1) ከአገራችን ዪኒቨርሲቲዎች በኤሌክትሪክና በኮምፒውተር ምህንድስና በባችለርና በማስተርስ ዲግሪ የሚመረቁ ተማሪዎች በየትኛውም ደረጃ ስለ ኦፕቲካል ኔትወርኮች የሚማሩበት እድል ባለመኖሩ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽኑ ያለጥርጥር የኤክስፐርት እጥረት ይኖረዋል፤ እና፣
2) ምንም እንኳን ታዳጊ አገሮች የመገናኛ ኢንፍራስትራክቸሮችን ለመዘርጋት የአቅም ችግር ቢኖርባቸውም፣ ብዙውን ጊዜ ግን የተዘረጉፍን ኔትወርኮች መጠበቅና ሲበላሹም መጠገን የከፋና ብዙ ወጪ ሊያስወጣቸው የሚችል የባሰ ችግር ነው፡፡
ስለዚህም፣ ለአቶ ዘላለም (ግልባጭ ለአቶ ደብረጽዮን አድርጌ)፣ በመጀመሪያ ደረጃ፣ የቴሌኮሙኒኬሽኑን የቴክኒክ ሰራተኞች ስለ መጪውን ዘመን ኔትወርኮች፣ በተለይም፣ ስለ ኦፕቲካል ኔትወርኮች፣ “Advanced” ስልጠና ልሰጥና፣ በአገሪቱ የሚዘረጉትን የኔትወርክ መስመሮች በተመለከተ ደግሞ፣ የሚገዙትን እቃዎች ጥራት ልቆጣጠርላቸው እንደምችል ጻፍኩላቸው፡፡
ከዚያን ጊዜ በኋላ ከአቶ ዘላለምም ይሁን ከአቶ ደብረጽዮን ምንም አይነት መልዕክት አልደረሰኝም፡፡ ደጋግሜ ለአቶ ዘላለምም ብጽፍም፣ ሰውዬው የውሀ ሽታ ሆኑ፡፡
ትላንትና፣ ኖቬምበር 25 ቀን፣ 2010 አመተ ምህረት፣ የሪፖርተር ድረ ገጽ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የስራ አመራር ለፍራንስ ቴሌኮም ሊሰጥ እንደሆነ አነበብኩ፡፡ ከሀያ አመታት አሳዛኝ እንቅልፍ በኋላ፣ ቴሌ እጅ መስጠቱ በፍጹም አልገረመኝም፡፡ ሊታደጉት የሚችሉ ኢትዮጵያውያን በመጥፋታቸው ግን አይደለም ስብራቱ፡፡ በሪፖርተር ዜና ላይ ያሳዘነኝ ነገር ቢኖር፣ አመራሩ ከሁለት አመታት በኋላ ለኢትዮጵያውያን እንደሚመለስ መጻፉ ነው፡፡ ምን ማለት ይሆን? ኢትዮጵያ ለሀያ አመታት ያልቻለችውን አመራር፣ ከሁለት አመታት እረፍት በኋላ፣ በምን ምትኀት ነው እንደገና መረከብ የምትችለው? ፍራንስ ቴሌኮምስ ቢሆን በሁለት አመታት ውስጥ ምን አይነት ለውጥ ነው የሚያመጣው፣ የሰው፣ የአስተሳሰብ፣ የቴክኒክ?