በአቧሬ ገበያ ሱቆችና መኖርያ ቤቶች ወደሙ
በአዲስ አበባ ከሚገኙ ትላልቅ የገበያ ሥፍራዎች መካከል አንዱ በሆነው አቧሬ ገበያ በተነሳ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ፣ 103 ሱቆችና የመኖርያ ቤቶች መውደማቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ድርጅት መረጃ ግን 70 ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች ናቸው የተቃጠሉት ይላል፡፡ “51 ሱቆችና 52 መኖርያ ቤቶች ናቸው የወደሙት፤” ሲሉ የአካባቢው ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የወረዳ ስድስት የሥራ ኃላፊዎችም በእስካሁኑ ሒደት 100 የሚጠጉ ተጎጂዎችን መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰኞ ለማክሰኞ አጥቢያ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ሱቆቹንና መኖርያ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ትቢያ ለውጧል፡፡
አደጋው በተከሰተበት ሰዓት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ድርጅት ጥሩ በሚባል ሰዓት በአካባቢው ቢደርስም፣ ንብረቶቹን ግን ከቃጠሎ ማትረፍ እንዳልቻለ ተጎጂ ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የእሳት አደጋ ተከላካዮች በስፍራው ሲደርሱ አንድ ሱቅ ወድሞ እሳቱ ወደ ሁለተኛው ሱቅ እየተዛመተ ነበር የሚሉት የአካባቢው ነጋዴዎች፣ ድርጅቱ ግን ንፋስ አጠረኝ! መግቢያ አጣሁ! በሚል ጊዜ በመፍጀቱ እሳቱ ተዛምቷል ሲሉ ምሬታቸው ገልጸዋል፡፡
“አጠገባችን ወንዝ አለ፡፡ ወንዙን ተጠቅመን እሳቱን መቆጣጠር እንችል ነበር፤ ነገር ግን ተከልክለናል፤” ሲሉ የልብስ መሸጫ ሱቃቸው ዓይናቸው እያየ እንዳጡ የሚናገሩ አንድ ነጋዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ያስገረማቸውን ነገር ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ ከአንድ ዓመት በፊት የእሳት አደጋ አገልግሎት ድርጅት በአቧሬ ገበያ እሳት ቢነሳ እንዴት ሊቆጠጠረው እንደሚችል ልምምድ አድርጎ ነበር፡፡ ‹‹ያ ሁሉ ልምምድ የትገባ?›› ሲሉ አግራሞታቸውን ገልጸው፣ የድርጅቱን የብቃት ደረጃ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የድርጅቱ ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት፣ ሱቆቹም ሆኑ ቤቶቹ የተሠሩት ግድግዳቸውም፣ ጣሪያቸውም በቆርቆሮ ሆኖ ነው፡፡ ቆርቆሮ ላይ ውኃ በሚለቀቅበት ጊዜ ወደ ውስጥ የሚገባ ባለመሆኑ የማጥፋቱን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ አቶ ንጋቱ ቀጥለውም ገበያው መኪና የሚያስገባ መተላለፊያ መንገድ የሌለውና ተቀጣጣይ የሆኑ ሸቀጦች ለምሳሌ ጋዝ የሚገኙበት በመሆኑ እሳቱን ለመቆጣጠር ሁለት ሰዓት ተኩል ፈጅቷል፡፡
የልምምዱን ሁኔታ ሲገልጹም ድርጅቱ የልምምድ ፕሮግራሞች አሉት፡፡ የሚለማመደው እንዴት በቅንጅት እንደሚሠራና የትራፊክ ሁኔታን ለመፈተሽ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ያም ሆኖ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ድርጅት የቱንም ቢል ተጎጂዎችን የሚያሳምን አልሆነም፡፡ ተጎጂዎቹ ይህ ጥፋት የደረሰባቸው በድርጅቱ ድክመት እንደሆነ እርግጠኛ ሆነው ይገልጻሉ፡፡
እሳቱን ለማጥፋት ዘጠኝ የእሳት ማጥፊያ ከባድ መኪኖች ተሰማርተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ መኪና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን፣ በሰዓቱ የነበሩ የዓይን እማኞች ለእሳቱ መጥፋት ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው የአየር መንገድ የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ምክንያታቸው መኪናው የሚለቀው የውኃ ኃይል ብዛትና ውኃው ረጅም ርቀት መጓዝ መቻሉ ነው፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 በሚገኘው አቧሬ ገበያ በደረሰው ቃጠሎ 500 ሺሕ ብር መውደሙንና ሁለት ሚሊዮን ብር ከውድመት መትረፉን ድርጅቱ ገልጿል፡፡ ይህንንም ነዋሪዎቹ አይቀበሉም፡፡ ከአንድ ሱቅ ብቻ ከ150 ሺሕ ብር በላይ ንብረት ወድሟል፡፡ ምን ዓይነት ስሌት ነው ሲሉ ለድርጅቱ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡
በዚህ አደጋ አምስት የድርጅቱ የእሳት ማጥፊያ ብርጌድ ሠራተኞችና ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ አንድ ሰው የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ ሲሆን በየካቲት 12 ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡
አቧሬ ገበያ ከመርካቶና ከሾላ ገበያዎች ቀጥሎ ሕዝቡ የሚገበያይበት ትልቅ ገበያ ነው፡፡ በአካባቢው የመኖርያ ቤት ኪራይ ርካሽ በመሆኑ ሸቀጦች በተነፃፃሪ በርካሽ ዋጋ የሚቀርቡበት ገበያ ነው፡፡
አደጋው የደረሰበትን ይህን ቦታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውና የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞቱማ መቃሳን ጨምሮ የተለያዩ የከተማው ባለሥልጣናት ጎብኝተውታል፡፡
አቶ አባተ በሥፍራው ለተገኙ የወረዳው ኃላፊዎች ከከተማው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጋር ጊዜያዊ ኮሚቴ እንዲያቋቁሙና በአስቸኳይ ጊዜያዊ መጠለያና ብርድ ልብስ ለተጎጂዎች እንዲቀርብ አዘዋል፡፡