የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የቀብር ሥነ ሥርዐት ሪፖርታዥ
- . ‹‹ማወቅ ትርጉም ያገኘው በመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ነው፤ ከካባቸው በላይ ሊቅነታቸው ጎልቶ ይታይ ነበር፤ ሊቅነት ብቻ ሳይኾን ይህ ጎደለህ የማይባል መልካም ጠባይዕ ነበራቸው፤ ለእርሳቸው እንዲህ ያለ አቋራጭ ጊዜ ይመጣል ብለን አልጠበቅንም፤ ሰላምን ለማምጣት በመፋጠን ላይ እንዳሉ ከረጅም መንገድ መጥተው ወደ ረጅም መንገድ ሄዱ – የሰላም መልእክተኛ ኾነው ሁሉንም በፍቅር እና በትዕግሥት እያዩ ነው የሄዱት፤ ይኼ ራሱ ትልቅ ምስክርነት ነው እኮ!!›› (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ)
- . ‹‹በቅንነት እና በታማኝነት ያገለገሏት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፡፡›› (የኀዘን መግለጫው)
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 10/2010፤ ነሐሴ 4/2002 ዓ.ም) ነሐሴ አንድ ቀን 2002 ዓ.ም ጠዋት በድንገተኛ ሕመም በተወለዱ በስድሳ ሰባት ዓመታቸው ያረፉት እና በመ/ፓ/ጠቅ/ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ ሐላፊ የኾኑት የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የቀብር ሥነ ሥርዐት በትናንትናው ዕለት ከጠዋቱ 3፡00 – 9፡00 ሰዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተካሄደ የጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዐት ተፈጸመ፡፡
ከዚህ ቀደም ብሎ አስከሬኑ ከነበረበት ሆስፒታል መኖርያቸው ወደ ኾነው እና ሲያገለግሉበት ወደ ነበረው የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት እና ሙሉ አደራረስ ሲደረግ አድሯል፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መመሪያ ሰጭነት በሌሎች የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራትም ጸሎተ ፍትሐት ተደርጓል፡፡
– ‹‹ጋሻ መመኪያዬ ሰይፈ ሆይ የእኔ አባት፣
ድንገተኛው ሞትህ ፈጀኝ እንደ እሳት፤
ላፍታ ተነሣና ምስጢሩን ተናገር፣
አይቃጠል ወገን አንጀቱም አይረር፤
…..
ድንቁርና ንገሥ ዛሬ ተሳካልህ፣
የዕውቀት ሁሉ ቁንጮ ሰይፈ ታሰረልህ፤››(ባለቅኔው)
-‹‹ለሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ
እንተ ልማዱ ትሕትና
ለቤተ ክህነት ዓይና፣
ለገብረ ሥላሴ ዐወቀ
እንተ ንብረቱ ጽሙና
ለባሕረ ምስጢር ወሰና፣
እስኪ ንገሪኝ እማማ
ትወልጅዋለሽ እንደገና
ያን የቅኔ ጎዳና
ያን የትርጓሜ ሳተና
ያነን የምስጢር ድንቅ ጀግና
ታገኝዋለሽ እንደገና?
እስኪ በይ ይኹና!!››(ባለቅኔው)
ሰኞ ነሐሴ ሦስት ቀን ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የየመምሪያ ሐላፊዎች እና ሠራተኞች፣ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ እና በርካታ ምእመናን በተገኙበት ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ሲደረግ አርፍዷል፡፡ ከቀኑ አምስት ሰዓት በኋላ ባለቦታዎቹን የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህናት ጨምሮ ከተለያዩ የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት በመጡ ሊቃውንት፡-
‹‹በአምሳለ ወፍ ርግበ ጸዐዳ ትመስል
ይእቲኬ ማርያም፣ ማርያም ይእቲ›› የሚለው የአርያም ድርሰት ተወርቧል፡፡ ወረቡ እንደ ተጠናቀቀ በመምህር ቀጸላ፣ በመምህር ዘአማን፣ በመምህር ዲበኵሉ፣ በሊቀ ኅሩያን በላይ መኰነን እና በመጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ የተዘጋጁ ሙሉ አርያም እና ሥላሴ ቅኔያት ቀርበዋል፡፡ ቅኔያቸውን ለማበርከት ጓጉተው በዙርያው ከነበሩት በርካታ ሊቃውንት መካከል በሰዓት መጣበብ ምክንያት ተመርጠው የተሰሙት የመምህራኑ ቅኔዎች ብዙዎቹ ለ75 ዓመታት አራቱን ጉባኤት እና ቅኔ ከነአገባቡ ሲያስተምሩ ኖረው ግንቦት 22 ቀን 2002 ዓ.ም በ102 ዓመታቸው ካረፉት መልአከ ገነት ገብረ ሥላሴ ዐወቀ ጋራ የተሰናሰሉ እና የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴን የቅኔ፣ የትርጓሜ፣ የጽሕፈት እና የስብከት ዐዋቂነት፣ የሥራ ትጋት፣ ትሑት ሰብእና እና የመግባባት ችሎታ የሚመሰክሩ ናቸው፤ አንዳንዶቹም፣ የሞተ ዕረፍታቸው ድንገተኛነት ያጫረባቸውን ቁጭት እና ጥርጣሬ የሚገልጡ ነበሩ፡፡ በተለይም ለመጋቤ ብሉይ የረጅም ጊዜ የሥራ ባልደረባቸው የኾኑት የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ከቅኔያቸው በፊት እምባ ቀድሟቸው ‹‹እንግዲህ መስቀልን ማን ይጽፈዋል? ጥምቀትን ማን ይጽፈዋል?. . .›› በማለት መንሥኤው በውል ያልታወቀው የሊቁ በድንገት መለየት ያሳደረባቸውን ልባዊ ኀዘን በቅኔያቸው ገልጸዋል፡፡ በግእዝ እና አማርኛ የተነገሩትን ቅኔያት ምስጢር በመረዳት፣ ‹‹እውነት ነው!›› እያሉ ሳግ እየተናነቃቸው አሰምተው የሚያልቅሱ፣ እጃቸውን በቁጭት የሚጸፉ የሊቁ ወዳጆች በዐውደ ምሕረቱ ዙሪያ ተስተውለዋል፡፡
መጀመርያ ታመም ዘመድ ይጠይቅህ
ምንህን እንዳመምህ ይወቀው ወገንህ
በምን ተቀየምህን ምንስ አስቀየምንህ
ሹልክ ብለህ ወጥተህ ወገንህን ትተህ
ከቶ ላትመለስ በመቅረትህ ወሰንህ፤
ምንድነው ነገሩ እንዲህ ያስጨቀነህ
ምንድነው ምስጢሩ እንደዚህ ያስከፋህ
ሰይፈ ሆይ ተናገር ወገንህ ይካስህ
እንደወጣህ አትቅር ዐይን ዐይን ስናይህ፤
ድንቁርና ንገሥ ዛሬ ተሳካልህ፣
የዕውቀት ሁሉ ቁንጮ ሰይፈ ታሰረልህ፡፡
ከዚህ በመቀጠል የሊቁ ዜና ሕይወት እና ሥራዎች በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ አማኑኤል አማካይነት በንባብ ተሰምቷል፡፡ በሕይወት ታሪካቸው ሊቁ ከልደት እስከ ዕረፍት የነበራቸው የትምህርት አድማስ፣ የአገልግሎት ትጋት፣ የሥራ ፍሬ፣ ቤተሰባዊ ሕይወት እና መገለጫ ጠባዕያት በስፋት ተዘርዝረዋል፡፡ የድንገተኛ ዕረፍታቸው መንሥኤ ስለሆነው ሕመማቸው ምንም ያልተባለበት ይህው የሕይወት ታሪክ፣ ‹‹በክቡር መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ ዕረፍት መሪር ኀዘን የደረሰባቸው ቤተ ሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ብቻ ሳይኾኑ በቅንነት እና በታማኝነት ያገለገሏት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፤›› ብሏል፡፡
ከጸሎተ ቅዳሴው በፊት የመጨረሻ መርሐ ግብር የነበረው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ቃለ ምዕዳን ነበር፡፡ ‹‹መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ሁሉንም በአክብሮት የሚቀበሉ፣ ይህ ቀረህ የማይባሉ መልካም ጠባይ የነበራቸው ሊቅ እና ወንድም ነበሩ፡፡ ብዙ ምሁራን እንዳሉ ይነገረናል፤ እናያለን፤ የእርሳቸው ግን የተለየ ነበር፤ በካባ እና ባማረ ልብስ የተደበቀ አልነበረም፤ ከካባቸው በላይ ሊቅነታቸው ጎልቶ ይታያል፤ ለሚጠየቁት ሁሉ ‹እሺ፣ ይኹን› ባይ ነበሩ፤ ፍጥነት፣ ጥራት እና ታማኝነት የሚያስፈልገው ተግባር ለመጋቤ ብሉይ ነበር የሚሰጠው፤›› ያሉት አቡነ ጳውሎስ የሊቁ መዋዕለ ዘመን እንዲህ ባጭሩ ይቋረጣል ብሎ የሚያስብ እንዳልነበር በመጥቀስ የመለየታቸውን አስደንጋጭነት አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹እንደ ባሕር ጥልቅነት ያለው መልካም ጠባይ ያላቸው እና ደከመኝ ማለትን የማያውቁ ነበሩ፤ ይህው አሁን እንኳ ሰላምን ለማምጣት በመፋጠን ላይ እንዳሉ ነው ከረጅም መንገድ መጥተው ወደ ረጅም መንገድ የሄዱት – የሰላም መልእክተኛ ኾነው፣ በአውሮፕላን ማረፊያ ጎንበስ ቀና ብለው አብረዋቸው የነበሩትን እየረዱ፣ ሁሉንም በፍቅር እና በትዕግሥት እያዩ ነው የሄዱት፤ ይኼ ራሱ ትልቅ ምስክርነት ነው እኮ!!›› በማለት አንክሯቸውን ገልጸዋል፡፡
በቃለ ምዕዳናቸው መጨረሻ፣ ‹‹ማወቅ ትርጉም ያገኘው በመጋቤ ብሉይ ነው፤ በሰው መተካት ለእግዚአብሔር ልማዱ ስለሆነ ለዚህ ጸሎት ያስፈልገናል፤ ከዚህ በቀር ወደኋላ መመለስ አንችልም፤ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ከማኅበረ መላእክት፣ ከማኅበረ ቅዱሳን ይጨምርልን፡፡›› በማለት ካሳረጉ በኋላ ሥርዐተ ቅዳሴውን መርተው ከድርገት በኋላ፣ ከሠርሆተ ሕዝብ በፊት አስከሬኑን በተዘጋጀለት መካን(ፉካ) በማሳረፍ የቀብር ሥነ ሥርዐቱ እንዲፈጸም አድርገዋል፡፡ ሥርዐተ ቀብሩ በተጣደፈ አኳኋን እንደተፈጸመ የሚገልጹ የአንዳንድ የቤተሰብ አባላት እና ሌሎች ኀዘንተኞች ቅሬታ የተሰማ ሲኾን ከቅዳሴው በፊት የተከናወነው ሥነ ሥርዐት ከቅዳሴ በኋላ እንደሚኾን ጠብቀው ለመጡት ኀዘንተኞችም ኹኔታው ግርታን ፈጥሯል፡፡ ጥድፊያው ምናልባትም ፓትርያሪኩ ለሱባኤው እና ለጤንነታቸው ወቅታዊ ተስማሚነት ወዳለው ወደ ድሬዳዋ ዕለቱኑ ያደርጉታል ተብሎ ከሚታሰበው የመልስ ጉዞ ጋራ ሳይያዝ እንደማይቀር አንዳንድ ተመልካቾች ግምት ወስደዋል፤ ሌሎችም ከቅዳሴው በፊት የተከናወነው መርሐ ግብር በቂ እንደ ኾነና ግብአተ መሬቱ ከድርገት በኋላ መፈጸሙ ሥርዐታዊ መኾኑን በአዎንታ በመጥቀስ ቅሬታውን ያጣጥሉታል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ለሊቁ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ ዕረፍት ከተበረከቱ ቅኔዎች መካከል የቀረቡትን እና በአማርኛም በግእዝም ከተነገሩት አንዳንዶቹን ለዝክረ ነገር መርጠን አቅርበንላችኋል፡፡
ጉባኤ ቃና
፩.እፎኑመ ሞት ለሰይፈ ሥላሴ ዘፈርሆ
፪.መኰንነ አቤል ቃየን ለሰይፈ ሥላሴ ተወክፎ
ሥላሴ ቅኔ
፩. ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ
ሥላሴ
መወድስ
