ወያኔ የአገሪቱን ለም መሬት ለባዕዳን እየሸጠ በምግብ እራሳችንን እንችላለን የሚለው ዕቅዱ ፋይዳ ብስ መሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው ዩ ኤን ሀብታት ገለጸ

ኢትዮጵያ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለውጭ አገር ባለሀብቶች በመስጠት የወደፊቱን ህዝብ ለመቀለብ ያስችለኛል ብላ ብታስብም እንኳንስ የወደፊቱን ቀርቶ አሁን ያለውንም ህዝብ መመገብ አትችልም ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል የሆነው ዩኤን ሀቢታት ገለጸ::

ድርጅቱ ” የአፍሪካ ከተሞች ሁኔታ በ2010″ በሚል ርእስ ባወጣው ሪፖርት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ እንደ ቤንጉዌላ፣ ሞቃዲሾና ፍሪታውን ህዝብ እጅግ አስከፊ በሆነ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኝ ነው።

በኢትዮጵያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የእርሻ መሬት ለውጭ ባለሀብቶች በስፋት እየተሰጠ ቢሆንም የከተሞችን እና የምግብ ችግርን በመቅረፍ በኩል ያለው ሚና አነስተኛ ነው ሲል ሪፖርቱ ገልጿል።

ቻይና ባለፈው አመት ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ወደ አፍሪካ በመላክ ያመረተችውን ምርት ወደ አገሯ ሰዳለች የሚለው የተመድ ሪፖርት፣ ይህ አይነቱ “ቻይናውያንን ወደ አፍሪካ መላክና የእርሻ ምርቶችን ወደ ውጭ የመላክ አካሄድ” በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግርና የምግብ እጥረት ሊቀርፍ ቀርቶ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር ይበልጥ የሚያባብስ ነው ።

ኢትዮጵያ በአለፈው አመት 150 ሺ ቶን ስንዴ ወደ አገሩዋ ማስገባቷን፣ በ2008 ደግሞ ከ11 ሚሊዮን ህዝብ በላይ መራቡን ያስታወሰው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎችን ለውጭ ባለሀብቶች በመስጠት የወደፊቱን ህዝብ መመገብ ቀርቶ አሁን ያለውንም ህዝብ መመገብ አልቻለም ብሎአል።

በኢትዮጵያና በአንዳንድ ያፍሪካ አገሮች የሚታየው የእርሻ መሬት ሽያጭ ግልጽነት የጎደለውና ለምዝበራ የተጋለጠ በመሆኑ አንዳንዶች አግሮ ኢምፔሪያሊዝም እያሉ ይጠሩታል ሲል ሪፖርቱ አመልክቷል

ተመድ ሀቢታት በአፍሪካ ውስጥ የሚታየውን የመሬት ሽያጭ አጥብቆ እንደሚቃወም ይታወቃል።