በጉጂ ዞን በሚኖር አንድ አናሳ ማህበረሰብ ላይ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑ ተዘገበ
በኦሮምያ ክልል በጉጂ ዞን በሚኖሩ የጌዴዮ ብሔረሰብ አባላት እና በንብረታቸው ላይ ጥቃት እየተካሄደ መሆኑን ከኢትዮጵያ የደረሰን ጥቆማ አመልክቷል።
ለግንቦት 7 ድምጽ የዝግጅት ክፍል እና ለሌሎችም መገናኛ ብዙሃን የደረሰው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፥ በጉጂ ዞን በአዶላ ረዴ ወረዳ ከሃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ የሰፈሩ እና አሁን 767 አባወራዎች የደረሱ የጌዴዎ ብሔረሰብ አባላት ይኖራሉ። በስፍራው ከሰፈሩበት ዘመን አንስቶም በቡና፣ በእንሰት እና በጫት ልማት ስራ ተሰማርተው ሲኖሩ ቆይተዋል። ደርግ የማህበረሰቡን ይዞታ በደን አካባቢነት እንዳካለለ የጠቆመው መረጃ፤ ህዝቡ በወቅቱ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፣ ደኑን ሳይነካ ይዞታውን ግን በነበረበት ሁኔታ እንዲጠቀም ተፈቅዶለታል ብሏል። በዚህ አኳኋንም እስካሁን ድረስ ግብር እየከፈለ በሰላም ሲኖር ቆይቷል።
ይሁን እንጂ፥ ከጥቅምት 1 እስከ 6፣ 2003 አመተ ምህረት ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ የቡና፣ የእንሰት፣ የሙዝ እና የጫት ተክላቸው እንደተጨፈጨፈ እና ለምግብነት በተዘጋጀ ቆጮ ላይም አፈር እንደተጨመረ ለማወቅ ተችሏል።
ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰውን መረጃ በመከተል ለማጣራት ባደረግነው ሙከራ፤ ምንም ምክንያት ሳይሰጥ ንብረታቸውን ያወደመው የመንግስት የግብርና ቢሮ እንደሆነ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ነግረውናል።
ተጎጂዎቹ ጥቃቱ እንደተፈጸመባቸው ለአዶላ ረዴ ወረዳ አስተዳደር አቤቱታ ለማቅረብ በብዛት ጉዞ ቢጀምሩም፤ የፌዴራል አድማ በታኝ ፖሊስ ከስፍራው ደርሶ እንዳስቆማቸው እና በአስለቃሽ ጭስና በጥይት የታጀበ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽሟል። በርካታ ንጹሃን ቆስለዋል፤ ዘጠኝ ዜጎችም ታስረዋል። ሪፖርቱ፥ ችግሩ በተከሰተበት ስፍራ የማይኖሩ እና በወቅቱም በስፍራው ያልነበሩ ሰዎች የጌዴኦ ብሔረሰብ አባላት በመሆናቸው ብቻ መታሰራቸውን ገልጾ፤ ሁኔታውን በጌዴኦ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረ “ዘረኛ ጥቃት” ብሎታል።
የግንቦት 7 ድምጽ ጥቆማውን ተከትሎ ወደ አካባቢው ስልክ በመወደወል ጥቃቱ መፈጸሙን ያረጋገጠ ሲሆን፤ ህዝቡ እስካሁን መፍትሄ እንደተነፈገም ለማወቅ ተችሏል።
በጉጂ ዞን ከዚህ ቀደም ከአላሙዲ የወርቅ ማእድን ጣቢያዎች ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።