የአማራ ክልል መንግስት ለብአዴን የልደት በአል 58.6 ሚሊዮን ብር ወጪ አደረገ
ህዳር 11 ቀን፣ ለተከበረው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ – ብአዴን – የልደት በዓል፣ በአስርት ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ከአማራ ክልል መንግስት ካዝና ወጪ መደረጉን የግንቦት 7 ድምጽ ምንጮች ገለጹ።
በብአዴን ውስጥ ያሉ የዝግጅት ክፍላችን ምንጮች የላኩት ዝርዝር መረጃ እንደሚያሳየው፥ በባህርዳር ከተማ የተከበረው በዓል በሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶችን አስተናግዱአል። ለተጋባዦቹ መስተንግዶ እና በአሉን ለማሳመር ለተደረጉ ዝግጅቶች ያለፈቃዱ ወጪውን የሸፈነው ደግሞ የአማራ ህዝብ ነው።
ለበአሉ ቅስቀሳ ለሚቀርበው የኪነት ቡድን ወጣት ሴቶችን እና ወንዶችን ለማሰልጠን፤ ለተለያዩ ስብሰባዎች የቀን አበል፤ ለትራንስፖርት፤ በከተማ ኮሪደሮች ለሚንጠለጠሉ እና የብአዴንን አርማ ለያዙ ሪቫኖች እና አምፖሎች፤ እንዲሁም ለተጓዳኝ ተግባራት 5 ሚሊዮን ብር፤ በአሉን ለማድመቅ ለተዘጋጁት 240 ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ዘይትና ለሾፌሮች አበል 8 ሚሊዮን ብር፤ የከተማዋን እና በአጠቃላይ የክልሉን ጸጥታ ለማስጠበቅ በሚል ሰበብ 16 ሚሊዮን ብር፤ ከተለያዩ ክልሎች እና ከአማራ ክልል ዞኖችና ወረዳዎች የሚመጡ 5000 እንግዶችን ለማስተናገድ 29.6 ሚሊዮን ብር፤ በድምሩ 58.6 ሚሊዮን ብር ከአማራ ክልል ካዝና ወጪ መደረጉን ምንጮቻችን ገልጸዋል። የህዝብ ገንዘብ ለፓርቲ ጉዳይ መዋሉ ህገ-ወጥ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ዝግጅቱ ይህንን ያህል ገንዘብ እንደማይፈጅ እና አገዛዙ ለዘረፋ እንዲመቸው የፈጠረው ስልት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው፥ በበአሉ ሰሞን ጸጥታ ለማስከበር የክልሉ ፖሊስ፣ ሲቪል ደህንነት፣ መከላከያና ልዩ ሃይል አልበቃ ብሎ፤ የፌዴራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ መጥቶ በባህርዳር እንዲሰማራ ተደርጓል። ከትግራይ ክልል የመጡ ወጣት ሰላዮችም በከተማዋ ማእዘናት ሁሉ ተሰማርተው ጥበቃ እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል። እነዚህ ወጣቶች ከዚህ ቀደም ዘረኛው አገዛዝ ልዩ ስልጠና ሰጥቶ በወረዳ አማካሪነት ሽፋን በአገሪቱ ዙሪያ የመደባቸው እንጂ ለበአሉ ሲባል አዲስ የመጡ እንዳልሆኑ መረጃው ገልጿል።
ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የአማራን ህዝብ እወክላለሁ ይበል እንጂ፤ በክልሉ ህዝብ ከመጠላቱ በተጨማሪ፣ የአማራ ብሔር አባላት ባልሆኑ ግለሰቦች መመራቱ በድርጅቱ የዝቅተኛ ደረጃ አባላት ዘንድ የረዥም ጊዜ የምሬት ምንጭ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።