580 ሺህ ኢትዮጵያውያን ዲቪ ሎተሪ መሙላታቸው የአገሪቱን አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ያንጸባርቃል ተባለ
በ2003 አመተ ምህረት አምስት መቶ ሰማንያ ሺህ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካን አገር የመሄድ እድል ለማግኘት ዲቪ ሎተሪ መሙላታቸው ታውቋል።
ይህ ቁጥር፥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ጥለው ለመውጣት እንደሚጓጉ ተጨማሪ ማስረጃ ነው ተብሏል። ኢትዮጵያ በተመዝጋቢዎች ቁጥር ከአለም አራተኛውን ደረጃ ብትይዝም፣ የዝግጅት ክፍላችን ያናገራቸው የፖለቲካ ተንታኝ የኢንተርኔት አገልግሎት ስርጭት ሰፊ ቢሆን ኖሮ ከዚህ በብዙ እጥፍ ድርብ የሚበልጥ ህዝብ በተመዘገበ ነበር ብለዋል።
ለምሳሌ ያህልም 1.47 ሚሊዮን ሰዎችን በማስመዝገብ ሁለተኛ ደረጃ የያዘችውን ናይጄሪያን እና ኢትዮጵያን አነጻጽረዋል። የናይጄሪያ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ህዝብ ቁጥር ወደ 44 ሚሊዮን እንደሚጠጋ የሚገመት ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ግን ከግማሽ ሚሊዮን በታች ነው።
ታዲያ በናይጄሪያ ከ29 ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ውስጥ አንዱ የዲቪ ሎተሪ ሲሞላ፤ በኢትዮጵያ ግን ከዚህ ቀደም ኢንተርኔት ተጠቅመው የማያውቁ ሰዎች ሁሉ የሌሎችን እርዳታ ጠይቀው ወይም የኢንተርኔት ካፌ አገልግሎት በመጠቀም ሞልተዋል ማለት ነው።
በነሓሴ ወር የወጣ የጥናት ጽሁፍ እንደሚያሳየው፣ ለአቅመ አዳም ከደረሱ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 46% በመቶ የሚሆኑት እድሉን ቢያገኙ አገራቸውን ጥለው የመውጣት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጹ ይታወሳል። ብዙዎች እውነተኛው ቁጥር ከዛ እጅግ የላቀ እንደሚሆን ግምታቸውን ይገልጻሉ።
በየአመቱ እየጨመረ የሄደው የስደተኞች ቁጥር፥ የኢኮኖሚ እድገት እና የፖለቲካ መብት በማስከበር መልካም የኑሮ ሁኔታን ፈጥሬያለሁ ለሚለው የወያኔ ዲስኩር ፍቱን ማርከሻ እንደሆነ በርካታ ተንታኞች ይናገራሉ።