የኮ/ል መንግስቱ “ትግላችን” መጽሐፍ በገበያ ላይ ይውላል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ታህሳስ 7 ቀን 2004 ዓ.ም. December 17, 2011)፦ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት እና በአሁኑ ሰዓት በስደት ዚምባቡዌ የሚገኙት፤ በመጥፎነታቸው የሚታወቁት የኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ባለ ሶስት ቅጽ መጽሐፍ የመጀመሪያው ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት በገበያ ላይ ሊውል ነው።
የኮ/ል መንግስቱ “ትግላችን” የተሰኘው ይህ መጽሀፋቸው በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ታሪካዊና ዝነኛ ሰዎች ስራዎችን በማሳተም በሚታወቀው ጸሐይ አሳታሚ በኩል በገበያ ላይ የሚውል መሆኑም ታውቋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም ሶስቱን ቅጾች በወቅቱ በተከሰቱ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚያትቱ የታወቀ ሲሆን አሁን በገበያ ላይ በሚውለው የመጀመሪያ ክፍል በተለይ ወደ አራተኛ ክፍለጦር ተመርጠው የመጡበትን ሂደትና በደርግ አመሰራረት ዙሪያ የነበራቸውን ትውስታ እስከ ንጉስ ኃይለ ስላሴ ህልፈተ ህይወት በዝርዝር እንደሚያቀርቡ ለመረዳት ችለናል።
“ትግላችን” የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ በሚል ርእስ የሚቀርበው አዲስ መጽሐፍ በቅጽ አንድ እትም በርካታ ከታሪኩ ጋር የተዛመዱ ፎቶግራፎችን የያዘ ከመሆኑም በላይ 514 ገጾችን የያዘ በአለም አቀፍ የህትመት ደረጃውን የጠበቁ ህትመቶችን በመስራት ላይ በሚገኘው ጸሐይ አሳታሚ በኩል የሚታተምና የሚሰራጭ ሲሆን የአንድ መጽሀፍ ዋጋ $39.95 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
መጸሀፉ የአጼ ኃይለ ስላሴ መጨረሻ፣ የጄ/ል አማን አምዶምና ሌሎች ቱባ ባለስልጣናትን ህልፈት የሚዳስስና የሚፈትሽ መሆኑ ተገልጿል።
የኮ/ሉን ትልቅ የማስታወስ ችሎታ የሚታይበት ነው የተባለለት ይህ መጽሐፍ በተለይ በዚያን ዘመን የነበረውን ሂደት ከነበሩት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ሽኩቻዎች አንጻር ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱት ዋንኛ ሰው ለመስማት በርካቶች ሲጠባበቁት እንደነበር ይታወቃል።
“ትግላችን” በመጭውወ ሳምንት ዲሴምበር 20/2011 ዓ.ም በገበያ ላይ እንደሚውል ታውቋል።