የዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ገዳይ ሃይል በአኝዋክ ወገኖቻችን ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ 8ኛ አመት ታስቦ ዋለ

ህዝባችንን በመሳሪያ ሃይል አፍኖ ለመግዛት መለስ ዜናዊ በልዩ ስልጠና አዘጋጅቶ ያሰማራው ገዳይ ሃይል የዛሬ 8 አመት በአኝዋክ ወገኖቻችን ላይ የፈጸመውን የዘር እልቂት ለማስታወስ የአኝዋክ ጀስቲስ ካውንስልና ጥምረት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ በመለስ ዜናዊ የሚታዘዘው ልዩ ወታደራዊ ሃይል እንደፈረንጆች አቆጣጠር ከዲሰምበር 13 እስከ 15 ባሉት ሶስት ቀናት 424 አኝዋኮችን መግደሉን አስታውሰዋል።

ከመጀመሪያዎቹ 3 ቀናት ቦኋላ በነበሩት ተከታታይ አመታት በድምሩ 1500 አኝዋኮች መገደላቸውን ይፋ ያደረገው የድርጅቶቹ መግለጫ፤ ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በአኝዋኮች ላይ የወሰደው የጭፍጨፋ እርምጃ ምክንያት የአካባቢውን መሬት፣ ውሀ፣ የተፈጥሮ ጋዝና ማእድናት ለመቆጣጠር እንደሆነ ግልጽ ነው ብሎአል።

“ዛሬ አኝዋኮችን የመግደያ ቀን ነው” በሚል መፈክር ነፍስ የማያውቁ ህጻናት፣ አሮጊቶች፣ ወጣቶችና አዋቂዎች ሳይቀሩ መጨፍጨፋቸው ተደጋግሞ መዘገቡ አይዘነጋም።

ዳውህ ማክ ጊል የተባለው ጋዜጠኛ በ2003 ባወጣው ሪፖርት፣ አሜሪካ 113 አኝዋኮች መገደላቸውን ማጣራት እንደቻለች ከመግለጡም ባሻገር የመለስ አገዛዝ የዘር ማጥፋት ወነጀል ለመፈጸም ሙከራ ማድረጉን የአይን እማኞችን አነጋግሮ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል።

በ2004 ሰርቫይቨርስ ራይትስ ኢንተርናሽናልና ጄኖሳይድ ወች የተባሉት አለማቀፍ ድርጅቶች የጸጥታው ምክር ቤትና የአፍሪካ ህብረት በጋምቤላ ክልል እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ እንዲያስቆሙ ጠይቀዋል።

ሂውማን ራይትስ ወች በ2005 ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት 424 አኝዋኮችን መግደላቸውን፣ ከ400 በላይ ቤቶችን ማቃጠላቸውን፣ እንዲሁም በርካታ ንብረት መዝረፋቸውን ይፋ በማድረግ ጉዳዩ በሰው ልጆች ላይ በተፈጸመ ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ገልጧል።

ዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በጋምቤላ የፈጸመውን ዘግናኝ እልቂት በወቅቱ ለመደበቅ የቻለውን ሁሉ ጥረት ቢያደርግም በክልሉ ተወላጆች አማካይነት ዜናው አፈትልኮ ከወጣ ቦኋላ ያስከተለውን አለም አቀፍ ትኩረት ለማድበስበስ የራሱ ታማኝ ሰዎች ያሉበትን አጣሪ ቡድን አቋቁሞ እንደነበረና ከህወሃት ቀንደኞች አንዱ በሆነው አባጸሃይዬ አማካኝነት ለወያኔ ምክር ቤት ቀርቦ የነበረው ሪፖርት ሃላፊነቱን የእልቂቱ ሰልባ በሆኑት ወገኖቻችን ላይ ለማላከክ ሞክሮ እንደነበር አይዘነጋም።

ወያኔ ከጋምቤላ የዘር ማጥፋት ወንጀል ወዲህ በጋምቤላ የሚገኘውን ሰፋፊ የእርሻ መሬት ለህንድ ባለሀብቶች እዚህ ግባ በማይባል ገንዘብ እየሸነሸነ በመሸጥ ላይ እንደሚገኝ ሲታወቅ ተቀማጭነቱ በአሜሪካን አገር የሆነ የኦክላንድ ኢንስቲትዩት ከሳምንታት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ የአካባቢውን መሬት እየተቀራመቱ ካሉት ባለሃብቶች መካከል ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑቱ የህወሃት አባላት የሆኑ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን አጋልጦአል። ከመንግሥት ባንኮች ከወለድ ነጻ የሆነ ብድር እየተሰጣቸው የጋምቤላን መሬት በነጻ እየተቀራመቱ ያሉት ህወሃቶች ለዘመናት የኖረውን የደን ተክሎች በመመንጠር ከሰል እያከሰሉ ወደጎሬቤት ሱዳን ጭምር በመሸጥ ሃብት እያካበቱ እንደሆነ ይሄው የኦክላንድ ኢንስቲትዩት ጥናታዊ መረጃ ይፋ አድርጎአል።