“የብሄር፣ ብሄረሰቦች ቀን” – የአገር ውስጥ ቅኝ ገዢዎች ድግስ
ሰሞኑን “የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን” የሚል የማስመሰያ ስያሜ የተሰጠው ድግስ በመቀሌ ከተማ ተጥሎ ሲበላና ሲጨፈር ተከርሟል። ይህ ዓመታዊ ድግስ እንደ ነገሥታት ግብር ተገዢዎች ተገዢነታቸውን፤ ምስለኔዎች ደግሞ ታማኝነታቸውን ለገዢዎቻቸው የሚያረጋግጡበት መድረክ ነው።
ይህ በዓል የትግራይ ገዢ ጉጅሌ በትግራይ ላይ ብቻ ሳይሆን በአማራም፣ በኦሮሞም፣ በሲዳማም፣ በወላይታም፣ በአፋርም፣ በሶማሊም፣ በጉራጌም፣ በሃድያም፣ በአንዋኝዋክም፣ … በሁሉ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ላይ ያለውን “የበላይነት” ለትግራይ ሕዝብ እና ለዓለም የሚያሳይበት ቀን ነው።
ድግሱን ለማድመቅ ከየማኅበረሰቡ የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ጨፋሪዎች ወደ መቀሌ ተጉዘዋል። ታማኝነታቸውን የሚመሰክሩ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ምስለኔዎች ከዋነኛቹ የበዓሉ ባለቤቶች እኩል ሽር ጉድ ሲሉ ሰንብተዋል። የውጭ አገር እንግዶችም በተመልካችነት ተጋብዘዋል።
የድግሱ መርሃ ግብር የሚከተለውን ይመስላል –
- በቅድሚያ ነፃነታቸውን የተገፈፉ፤ በገዛ አገራቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ዜጋ የሆኑ የኅበረተሰብ ክፍሎች እንወክላለን የሚሉ ሰዎች በትግራዩ ገዢዎችና ምስለኔዎቻቸው መረገጣቸው የፈጠረላቸውን ደስታ በመግለጽ ንግግሮችን ያደርጋሉ። ንግግሮቻቸው በፋሺስት ጣልያን ወረራ ወቅት ለጠላት ያደሩ ባንዳዎች ያደርጉት የነበረውን አንገት ሰባሪ ንግግሮችን ያስታውሱናል።
- ቀጥሎ ከየክልሉ የመጡ ምስለኔዎች የትግራይ ገዢዎች በመላው አገሪቱ ባሰፈኑት አገዛዝ ስለተገኘው ልማትና ዲሞክራሲ ይደሰኩራሉ። የድግሱ መድመቅ፤ የምግቡ መትረፍረፍ፤ የመጠጡ ሞልቶ መፍሰስ፤ ይህ ልማት ባመጣው ብልጽግና ረሃብ የሚገርፈው፣ የኑሮ ውድነት የሚለበልበው ዜጋ ታሪክ ሆኗል የሚል መልእክት ማስተላፊያ ነው። የተገዥዎቹ ዲስኩር በፋሽት ጣልያን የወረራ ክፉ ዘመን የየአውራጃዎች ገዢዎች ለግራዚያኒ ያቀርቡት የነበረው ራፖርት ዓይነት ነው።
- በመጨረሻም የተገዢ ማኅበረሰብ ተወካዮች ለትግራይ ገዢ ቡድን አባላት ረዥም እድሜ እየተመኙ በጭፈራና በሆታ “በነገሥታቱ” ፊት በሰልፍ ያልፋሉ።
ይህ ነው “የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን” የሚል የማስመሰያ ስም የተሰጠው ድግስ። ኢትዮጵያዊያን ለአጭር ጊዜም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱን አዋራጅ ድግስ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ያውቁታል። የአሁኑ ልዩነቱ ወራሪዎችና ተወራሪዎች፤ ቅኝ ገዢዎቹና ቅኝ ተገዢዎች በመልክ መመሳሰላቸው ብቻ ነው። በተግባር ረገድ ፋሽስት ጣሊያን ከሠራው ግፍ በላይ የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ዛሬ እየሠራ ነው።
ይህንን ሃቅ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም። ለመሆኑ
- የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ወርሮ የያዘውን አገር ከራሱ ብቻ በወጡ ሰዎች በሚመራ ሠራዊትና የስለላ ተቋም አማካይነት እየገዛ መሆኑን የማያውቅ ማነው?
- በሃብት ዘረፋውስ ቢሆን መዝባሪው ማን፤ ተመዝባሪው ማን እንደሆነ ለይቶ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አለ?
- እስር ቤቶች ውስጥ አሳሪውና ደብዳቢው ከየት የመጣ እንደሆነ፤ ታሳሪውና ተደብዳቢው ደግሞ ማን እንደሆነ የማያውቅ ማነው?
- መሬት ቢታደል፤ ጨረታ ቢወጣ፤ ብድር ቢሰጥ፤ የትምህርት ወይም የሥራ እድል ቢኖር ቅድሚያው የማን እንደሆነ እስካሁን የማያውቅ የዋህ አለ?
ይህንን የአረጀ፣ የበሰበሰ ከቅኝ ገዥዎች ሰነድ የተገለበጠውን አሠራሩን ነው መለስ ዜናዊ “ፌደራላዊ፣ ዲሞክራሲያዊ” እያለ የሚያቆላምጠው። ይህንን የዜጎች ራስን አዋራጅ የተገዢነት ማረጋገጫ ዝክርን ነው “የእኩልነት ማረጋገጫ” የሚለው።
በዝምታ የመገዛታችንን ውጤት ግን እያየነው ነው። በየዓመቱ የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ በትዕቢት ይበልጥ እያበጠ፤ የተገዢዎች ውርደት ደግሞ እየባሰ ነው። የኦሮሞና አማራ ማኅበረሰቦች ለይስሙላም ቢሆን ከሥልጣን መባረራቸውቸው የዚህ ዝምታው ውጤት ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት የተያዘው ታሪክን ከልሶ የመፃፍ ፕሮጀክት ሌላው የዝምታ ውጤት ነው። በአዲሱ ታሪክ መሠረት ትግራዋይ ሁሉ ጀግና፤ ሌላው ሁሉ ፈሪ ነው። በአዲሱ ታሪክ መሠረት በቀድሞው ሥርዓትም ቢሆን የትግራይ መሳፍንትና ነገሥታት ደጋግ፣ ተጠቂዎች እና ተበዳዮች ናቸው። በአንፃሩ የአማራ መሳፍንትና ነገሥታት በሙሉ መሰሪዎችና ክፉዎች ናቸው። ይህ መንገድ የት ያደርሰናል?
በትግራይ እና በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ቅራኔ ለማስረጽ መለስና ቡድኑ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። የተመኙትን ያህል ባይሆንም ጥረታቸው መና እንዳልቀረ ማየት ይቻላል። እነሆ መቀሌ ድረስ ተጉዘው ተገዢነታቸውን በደስታ የሚናገሩ ሰዎችን አፍርተዋል። በዚህ ደረጃ ራሳቸውን አዋርደው ብሄረሰቦቻቸውን እንዲያዋርዱ በማድረግ ለሚፈጸመው ወንጀል የሃገሪቱ ህዝብ በዋንኛነት ተጠያቂ የሚያደርገው የትግራዩን ገዥ ጉጅሌና ከዚህ ጉጅሌ ጋራ በመጠጋት ከየትኛውም የሃገራችን ማህበረሰብ ክፍል እጅግ የላቀ ከፍተኛ የስልጣንና የጥቅም ተካፋይ የሆነውና እየሰፋ የመጣውን የትግራይ ገዥ መደብ ነው። ይህ አካሄድ አገራችንን የት ያደርሳት ይሆን የሚለው ስጋት ከኢትዮጵያዊያን አልፎ የውጭ አገር ሰዎችን ጭምር እያሳሰበ ነው።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የትግራዩን ገዢ ጉጅሌ ከሥልጣን ካላባረርን አባቶቻችና እናቶቻችን ከአምሳ ዓመታት በፊት ያባረሩትን ቅኝ ተገዢነት፤ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ከ15 ዓመታት በፊት የተገላገሉትን የአፓርታይድ ፌደራሊዝም ለልጆቻችንና ለመጪው ትውልድ ማውረሳችን የማይቀር ነው።
ይኸ ሁሉ በደል አስመርሮት ነው የዳዉሮ ዞን፣ የዋካው ወጣት፣ መምህር የኔሰው ገብሬ
በደል በዛ!!! ፍትህ በሌለበት አገር መኖር አልችልም!!! በዚህ ሁኔታ መኖር ኑሮ አይባልም!!! ግፍና መከራ እያየሁ መኖር አልችልም!!! እኔ ለእናንተ አርዓያ ለመሆን እሞታለሁ!!! እናንተ ታግላችሁ ነፃ ውጡ!!!
ብሎ በራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክቶ ተቃጥሎ የሞተው። መች ነው እኛስ መሮን የምንነሳው?
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሁላችንም እንደመምህር የኔ ሰው ገብሬ “በደል በዛ!!!” ብለን አምርረን እንድነሳ ሆኖም ክንዶቻችንን በራሳችን ላይ ሳይሆን በበዳዮች ላይ እንዲሆን ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!