የሕዝብ ቁጣ በዘረኞችና ሰቆቃ ፈፃሚዎች ላይ ይወርዳል ያኔ “ታዝዤ ነው የፈፀምኩት” ማለት አያድንም !!!

አምረን እየታገልነው ያለው ወያኔ ራሳቸውን ጀግኖችና ምርጦች አድርገው በመውሰድ የሚኩራሩ፤ “የጀግንነታቸው” ምንጭ ደግሞ ዘራቸው እንደሆነ ከልብ ያመኑ የስነልቦና ችግር ያለባቸው ሰዎች ስብስብ ነው። እነዚህ ድውያን በውስጣቸው ባለው የትንሽነት ስሜት ምክንያት በአስተሳሰብም ሆነ በሙያ የሚበለጣቸውን ሰው ማዋረድና ማሰቃየት ያስደስታቸዋል። እነዚህ ሰዎች በሃብት እንጂ በመንፈስ አላደጉምና እራስን ከሌላው ጋር እኩል አድርጎ የማየት ብቃት እና ሆደሰፊነትን ማዳበር አልቻሉም::

መንግሥቴን ለመገልበጥ ሙከራ አድርጋችኋል በሚል በወያኔ ተከሰው እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖቻችን ላይ አስከፊ ሰቆቃ እያደረሰ ያለው ይኸው ከመንፈስ−ትንሽነት የሚመነጭ የስነልቦና ቀውስ ነው::

ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ዓይናቸው እስኪጠፋ ድረስ እየተቀጠቀጡ ክብራቸውን የሚነኩ በርካታ ስድቦችን መሰደባቸውና ከሁሉም የባሰባቸው ግን “አማሮች ሽንታሞች ናችሁ” መባላቸው መሆኑን ፍርድ ቤት ውስጥ ተናግረዋል። ምን ዓይነት አንደበት ያለው ሰው ነው እንዲህ ዓይነቱን የዘቀጠ ነገር የሚናገር? ከስደቡ ይልቅ ከእንዲህ ዓይነቱ ዝቃጭ ጋር እኩል ዜጋ መሰኘቱ የሚያሳፍር አይደለምን? ወያኔዎች በሰው ፊት ላይ የሚተፉ ባለጌዎች መሆናቸውን ድሮም እናውቃለን። አንድን ሕዝብ “ሽንታም” ማለት ግን ከብልግናም በላይ ነው።

የወያኔ ቅልብ አግዓዚዎች በበደኖ፣ በአዋሳ፣ በሀረር፣ በጋምቤላ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባ እና በሶማሊያ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጽሙ በተመሳሳይ የጅምላ ስድብ እየተበረታቱ እንደነበር እናውቃለን። ይህ የትንሽነት ስሜት የፈጠረው የስነ ልቦና ቀውስ በቶሎ መፍትሄ ካልተበጀለት መጨረሻው የከፋ ይሆናል።

ሰቆቃ መፈፀም ዓለም ዓቀፍ ወንጀል ነው። በመሆኑም ዛሬ በወገኖቻችን ላይ ዘግናኝ ሰቆቃዎችን በማድረስ ላይ የምትገኙ የወያኔ ቅጥረኞች በሙሉ ነገ በገባችሁበት ገብተን ዋጋችሁን እንድታገኙ የምናደርግ መሆኑ በጥብቅ ልናስገነዝባችሁ እንወዳለን። ሰቆቃ ፈጽሞ ማምለጥ እንደማይቻል በቁጥጥራችሁ ሥር ካለው ቀልቤሳ ነጌዎ ትምህርት ውሰዱ እንላለን።

አንድን ዘር በጅምላ ማንቋሸሽና በዚህም ምክንያት ግለሰቦችን ማጥቃት ደግሞ ከላይኛው የባሰ ዓለም ዓቀፍ ወንጀል ነው። ለነፃነት እየከፈሉት ባለው የህይወት መስዋዕትነት የምናደንቃቸው ጀግኖቻችን በዘራቸው ምክንያት መሰደብና መደብደብ ያንገበገበን መሆኑን እንድታውቁት እንፈልጋለን።

ሰቆቃንንና የዘር ጥላቻን አድበስብሳችሁ የምታልፉ የወያኔ ካድሬ−ዳኞች፣ አቃብያነ ህግ፣ ፓሊሶችና ሌሎችም ሹማምንት ተገቢውን ቅጣት የምታገኙበት ቀን ቅርብ መሆኑን እናስገነዝባለን።

ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ደጋግሞ እንደገለፀው ይህንን እኩይ ሥርዓትና ባህል ያመጣብንን ወያኔን የማስወገድ ኋላፊነት የወደቀው የበደሉ ገፈት ቀማሽ በሆነው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ነው። ይህን ግፍና ውርደት ማስቆም የሚችለው የተደራጀ የሕዝብ ትግል ነው። በታሳሪዎች እና በሌላውም ሕዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ሰቆቃ እንዲያበቃ ወያኔን ከሥልጣን ማባረርና በምትኩ ለሰብዓዊ መብቶች ክብር ያለው ፍትሃዊ ሥርዓት መመሥረት ይኖርበታል። ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል፤ ለዚህም መላው ሕዝብ በጋራ እንዲነሳ ጥሪ ያደርጋል።

ሰቆቃና ዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን ማድረስ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ዓለም ዓቀፍ ወንጀሎች በመሆናቸው ይዋል ይደር እንጂ የማይቀር እና በይቅርታ የማይታለፉ ተጠያቂነትን በውስጣቸው ይዘዋል። በእነዚህ ወንጀሎች የተሳተፋችሁ ሁሉ መጠየቃቸሁ በፍጹም አይቀርም። ያ ቀን ደግሞ ቅርብ ነው። ያኔ “ታዝዤ ነው የፈፀምኩት” ማለት ተቀባይነት አይኖረውም። ሽራፊ እንኳን ህሊና ያላችሁ ካላቸሁ እጃችሁን ሰቆቃ ከመፈጸም አውጡ፤ ሰቆቃን አጋልጡ፣ ታገሉ። አለበለዚያ ግን የሕዝብ ቁጣ በእናንተ ላይ ይወርዳል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!