አቡጊዳ – “ስልታችን እየሰራ ነዉ ፤ በሰላማዊ ትግል ላይ ያለንን ጠንካራ አቋም እናድስ” አቶ ስዬ በአንድነት ጉባዔ ካደረጉት ንግግር
የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር የነበሩት፣ አቶ ስዬ አብርሃ፣ ዛሬ ታህሳስ 1 ቀን የአንድነት ፓርቲ ያደረገዉን የጠቅላላ ጉባዔ በሳካይፒ የተካፈሉ ሲሆን ፣ ድርጅታቸዉ በፈታኝና ከባድ ሁኔታ ዉስጥም እያለ አሁን ያለበት ደረጅ መድረሱ በጣም የሚያስደስት እንደሆነ ገልጸዋል።
አቶ ስዬ ገዢዉ፣ ፓርቲ ከጦር በላይ የሚፈራዉ የሰላማዊ ትግል እንደሆነ በማስመር፣ የሰላማዊ ትግሉ ከመቼዉም በላይ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡ ሲሆን፣ በተለይም የነ አቶ አንዱዋለም መታሰር የቀሰቀሰዉ ከፍተኛ የትግል ስሜትን በመጥቀስና ገዢዉ ፓርቲ ጠንካራ ታጋዮችን ማሰሩን ቢቀጥልም፣ ትግሉ የበለጠ ይጠናከራል እንጂ እንደማያቆም አስረድተዋል።
አቶ ስዬ ያደረጉትን ሙሉ ንግግር እንደሚከተለዉ አቅርበነዋል፡
የተከበራችሁ የአንድነት ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች
ጤና ይስጥልኝ እንደምን ከረማችሁ፡፡ እንኳን ለሁለተኛው መደበኛ የፓርቲያችን ጉባኤ አደረሳችሁ፤ አደረሰን በማለት የከበረ ስላምታየን አቀርባለሁ፡፡
ጉባኤው እንደወትሮውም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየተካሄደ መሆኑ ቢታወቅም አሁንም እንደወትሮው በተሳካ ሁኔታ ተከናውኖ አንድነት ፓርቲንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልን አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚወስደው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አንድነትን በግልጽ በታወቁ ግቦች፤ ፖሊሲዎች፤ስትራተጂና ስልቶች የሚመራ የምር ፓርቲ እናድርገው ብለን በዚሁ መሰረት መንቀሳቀስን ከጀመርን ቆይቶአል፡፡ ይህ መንገድ ቀላል እንዳልሆነ አስቀድመን ተገንዝበነዋል፡፡ በአንድ በኩል ከእኛ ብዙ ጥረትና ብዙ ምክክርን ይጠይቃል በሌላ በኩል ደግሞ ገዢው ፓርቲ በእኛ ላይ ብዙ እንዲያተኩርና እኛን የምር እንዲወስደን ያደርገዋል፡፡ እየሆነ ያለውም ይህንኑ ነው፡፡
እነ አቶ አንዱአለም እነ አቶ እስክንድር ከታሰሩ ወዲህ በርካታ ዜጎች ‹‹እኔ አንዱአለም ነኝ›› ‹‹እኔ እስክንድር ነኝ›› በማለት የታሰሩት ወገኖቻቸው የጀመሩትን የሰላማዊ ትግል መንገድ ለማስቀጠል ቃል ሲገቡ ተደምጠዋል፡፡ በዚህ መልእክት ውስጥ ሁለት ቁምነገሮች እናገኛለን፡፡ የመጀመርያው አንዱአለም ይፈታ፤ እስክንድር ይፈታ፤ ናትናኤል ይፈታ ማለት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግም ትግሉ አይቆምም እነሱ ቢታሰሩም እኛ እናስቀጥለዋለን ብሎ በግልጽ ማወጅን ያመለክታል፡፡ ይህ ቃል የአንድነቶች ቃል እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡ ቃሉ የአንድነቶች ቃል ብቻ ሆኖ እንዲቀር ግን አይጠበቅም፡፡ የመላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ወጣቶች ቃል መሆን አለበት፡፡ ይህንን እውን በማድረግ ረገድ ይህ ጉባኤ መነሻ ይሆናል ብየም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ክቡራትና ክቡራን
አንድነት የተመሰረተው በኢትዮጵያ አሁንም ለአገራችን ትክክለኛው የትግል ስልት ሰላማዊ የትግል ስልት ነው፤ መንገዱ አስቸጋሪ ቢሆንም አሁንም በሰላማዊ መንገድ ታግሎ በኢትዮጵያ ዴሞክራስያዊ ሽግግርን እውን ማድረግ ይቻላል በሚሉ ወገኖች መሆኑ ይታወቃል፡፡ አቶ አንዱአለምን ጨምሮ ቆየት ብሎ አንድነትን የተቀላቀልነው ወገኖችም አንድነትን የተቀላቀልነው ከዚህ እምነት በመነሳት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህ መሆኑ እየታወቀ ከዚህ በፊት ወይዘሪት ብርቱካንን አሁን ደግሞ አቶ አንዱአለምን የመሳሰሉ የፓርቲውን ቁልፍ የአመራር አባላትን ለእስርና ለእንግልት መዳረጉን ተያይዞታል፡፡ ድርጊቱን ለመሸፈን የተለያየ ስምና ምክንያት ቢሰጠውም ሁሉም እርምጃዎች የሚያመለክቱት የአገራችን ገዢዎች ሰላማዊ ትግልን ከጦርና ከፈንጂ በላይ የሚፈሩት መሆኑን ነው፡፡ አንድነት እነሱ በማይችሉበት መንገድ መምጣቱ እጅጉን ያስጨነቃቸው መሆኑን ነው፡፡ ስልታችን እየሰራ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ጊዜ በያዝነው አካሄድ ላይ አንዳችም ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም፡፡ ይልቁንሰ ይህ ጉባኤ በሰላማዊ ትግል ላይ ያለንን የጸና አቋም የምናድስበት፤ ስልቱ ይበልጥ ጥልቀት አግኝቶ የሚቀጥልበትን መንገድ የምንመክርበት አጋጣሚ ይሆናል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ክቡራትና ክቡራን ጉባኤተኞች
በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ላይ መሆኔ ታውቁ ይሆናል፡፡ ሰሞኑ የመጀመርያው መንፈቅ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተናዎች ወቅትም ነው፤ ቅዝቃዜውም የሚጀምርበት ወቅትም ነው፡፡ ጉባኤው ወደ አገሬ ለመምጣትም ከብርዱ ለማምለጥም አጋጣሚ ይፈጥርልኛል ብየ ጠብቄ ነበር፡፡ መምጣት ባልችልም ጉባኤው እንዲሳካ እመኛለሁ፤ የታሰሩት ወገኖቼንም ሁሌ አስባቸዋለሁ፡፡
ከታላቅ አክብሮት ጋራ
ስየ አብርሃ ሐጎስ
ቦስትን፤ ሃገረ አሜሪካ