ዶ/ር ነጋሶ የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ሆኑ

(አቡጊዳ) – የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዛሬ እሁድ ታህሳስ 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔዉን አጠናቀቀ። ለሚቀጥሉት አመታት ድርጅቱን በሊቀመንበርነት የሚመሩትን እንዲሁም የድርጅቱ የላእላይ ምክር ቤት አባላትን ጠቅላላ ጉባዔዉ የመረጠ ሲሆን ስብሰባዉ በተሳሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያመለክታል።

የድርጅቱ ሊቀመንበር ለመሆን ዶር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የአዲስ አበባ የአንድነት ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶር ንጋት አስፋዉ እንዲሁም ከአንድነት ፓርቲ ጋር የተዋሃደዉ የብርሃን ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ፣ ለእጩነት ቀርበዉ እንደነበረ መዘገባችን ይታወሳል።

ከስብሰባዉ በፊት ዶር ንጋት እራሳቸዉን ከእጩነት በማንሳታቸዉ፣ ፉክክሩ በዶር ነጋሶና በኢንጂነር ዘለቀ መካከል ብቻ እንደነበረ የደረሰን ዘገባ አክሎ ያትታል።

ከጠለቀ ዉይይትና ዲሞክራሲያው ክርክሮች በኋላ የጠቅላላ ጉባዔዉ አባላት፣ ዶር ነጋሶ፣ አሁን የያዙትን ሃላፊነት እንዲቀጥሉና የፓርቲዉ ሊቀመንበር ሆነዉ እንዲቀጥሉ በአብላጫ ድምጽ ወሰኗል። የብዙ አባላትን ድምጽና ድጋፍ ያገኙት ኢንጂነር ዘለቀም፣ ያሸነፉት ዶር ነጋሶ ሳይሆኑ ያሸነፈዉ ዲሞክራሲ እንደሆነ በመግለጽ ፣ የጠቅላላ ጉባዔዉን ዉሳኔ በጸጋ እንደሚቀበሉ፣ ከዶር ነጋሶም ጋር ተያይዘዉ በመስራት፣ ፓርቲዉ የቆሞለትን አላማ ከግቡ ለማድረስ የድርሻቸዉን እንደሚወጡ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።

ጠቅላላ ጉባኤዉ የድርጅቱን ሊቀመንበር ከመምረጥ ባሻገር፣ የላእላይ ምክር ቤት አባላትን የመረጠ ሲሆን የድርጅቱ ምክትል የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ በላይ፣ የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ ዳዊት አስራደ፣ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች የምክር ቤቱ አባላት እንደሆኑም ለማወቅ ችለናል።

ለሊቀመንበርነት እጩ ተወዳደሪ ሆነዉ ቀርበዉ የነበሩት ዶር ንጋትንና ኢንጂነር ዘለቀን እንዲሁም በእሥር የሚገኙት አቶ አንዱዋለም አራጌንና አቶ ናትናዔል መኮንንን በሌሉበት፣ እንዲሁም ከአሜሪካ አገር ሆነዉ በስካፕይፒ ስብሰባዉ የተካፈሉትን የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር አቶ ስዬ አብርሃን የምክር ቤቱ አባላት እንዲሆኑ ጉባዔዉ መርጧቸዋል።

ከቀድሞ የአመራር አባላት መካከል ዶር ኃይሉ አራያ ፣ አቶ አስራት ጣሴ በድጋሚ የምክር ቤቱ አባል እንዲሆኑ የተመረጡ ሲሆን፣ የድርጅቱ አንጋፋ መሪ የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸዉ የምክር ቤቱ አባል እንዳልሆኑም ለማወቅ ችለናል። ኢንጂነር ግዛቸዉ፣ ወጣቶች ወደ ድርጅቱ አመራርነት መምጣት አለባቸው በሚል እነ አቶ አንድዋለም አራጌን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ወደ አማራር እንዲመጡ ያደረጉ ሲሆን፣ ከብርሃን ፓርቲ ጋር ዉህደት እንዲመሰረት፣ ኢትዮጵያዉያን በዘር ሳይከፋፈሉ ለአንዲት ኢትዮጵያ በጋራ መስራት ይቻል ዘንድ የአንድነት ፓርቲ በመድረክ ዉስጥ እንዲሰራ ቁልፍ ሚና ተጫዉተዋል።

ዛሬ በተደረገዉ ጉባዔ የታሰሩ የአንድነት አመራር አባላት ቤተሰቦች፣ የመድረክ አባል ድርጅቶች አመራር አባላት ፣ ዲፕሎማቶች እንደተገኙም ለማወቅ ችለናል። የመድረክ አመራር አባላት በተለይም የአንድነት ፓርቲን የብርሃን ፓርቲ መዋሃዳቸዉን እንደ ትልቅ ስኬት በመግልጽ መድረክም ከግንባርነት ወደ ዉህደት መገስገስ እንዳለበት ገልጸዋል።

የድርጅቱ ሊቀመንበር እንዲሆኑ የተመረጡት ዶር ነጋሶ ጊዳዳ ካቢኔያቸዉን (የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን) የሚሰየሙ ሲሆን፣ የተሰየሙት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በአብላጫ ድምጽ የምክር ቤቱን ድጋፍ ካላገኙ ተቀባይነት እንደማይኖራቸዉ የድርጅቱ ሕገ ደንብ ይገጻል።የምክር ቤት አባላት ያልሆኑ የድርጅቱ አባላት፣ በሊቀመንበሩ ከተሰየሙና በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኙ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሊሆኑ እንደሚችሉም የድርጅት ሕገ ደንብ ይገልጻል።

ለተሰብሳቢዉ በሳካይፒ ንግግር ያደረጉት የሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶ ሊቀመንበር አቶ አሎግ ልመንህ ፣ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገር ቤት የሚደረገዉ ትግል ለመደገፍ ቆርጠው መነሳታቸውን በመግልጽ፣ በተለይም በድርጅቱ ሊቀመንበር የሚመረጠዉና በምክር ቤቱ የሚጸድቀዉ የስራ አፈጻሚ ኮሚቴ በርካታ ወጣቶችን ያቀፈ እንዲሚሆን ያላቸዉን ተስፋ ገልጸዋል።