አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ከወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ ጫና እየተደረገበት ነው የተባለውን አስተባበለ ተባለ
ዝነኛው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ከዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት ነው ሲል ታዋቂው ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የሯጩን ማኔጀር ጠቅሶ ዘግቧል። ከሁለት ቀናት በኋላ ግን አትሌቱም ማናጀሩም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ዘገባውን አስተባብለውታል።
ሃይሌ ገብረስላሴ ኖቬምበር 7 ቀን የተካሄደውን የኒው ዮርክ ከተማ ማራቶን በጉልበት ህመም ሰበብ ማቋረጡ እና ከእስፖርቱ አለም ጡረታ መውጣቱን አውጆ እንደነበር ይታወሳል። ባለፈው ሰኞ ግን በቤተሰብ እና ጓደኞች ጉትጎታ ምክንያት ውሳኔውን ማጠፉን አረጋግጧል።
የአትሌቱ ማኔጀር የሆነው ኔዘርላንዳዊው ጆስ ሄርመንስ፥ ሃይሌ በወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ጫና እየደረሰበት እንዳለ ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግሯል። የሃይሌ ስልክ መጠለፉን እና ማስፈራሪያ እየተደረገበት እንዳለም አስረድቷል። ሚስተር ሄርመንስ ጨምሮም፥ ሯጩ የኒው ዮርክ ማራቶንን አቋርጦ መውጣቱን ተከትሎ ያስተላለፈው የጡረታ አዋጅ ከዚህ ሁሉ ጫና የተነሳ ያደረበት የስሜት መረበሽ ውጤት ነው ብሏል።
ሃይሌ ገብረስላሴ ባለፉት አምስት አመታት የወያኔን ጉዳይ የሚያስፈጽመው የሽማግሌዎች ቡድን አባል ሆኖ ከመቆየቱ በተጨማሪ፤ በመስከረም ወር በአዳማ በተካሄደው የገዢው ቡድን ጉባኤ ላይ ተገኝቶ የድጋፍ ንግግር ማድረጉና ለዘረኛው አምባገነን ስጦታ ማበርከቱ ይታወሳል። ሬከርድ ሲሰብር ለብሶት የነበረውን ከነቴራ ለመለስ ዜናዊ የሰጠበት ምክንያት ምን እንደሆነ በፍትህ ጋዜጣ የተጠየቀው ታዋቂ አትሌት፤ አምባገነኑ ስጦታው እንደሚገባው ገልጾ፣ መጽሃፍ ቅዱስም ቢሆን ንጉስህን አክብር ይላል ሲል ተናግሮ ነበር።
ወደፊት የፖለቲካ መሪ የመሆን ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ተናግሮ የነበረው የእስፖርት ሰው፣ ከዘረኛው አገዛዝ ጋር የፈጠረው ቅርበት በህዝብ ዘንድ ባልጠበቀው መንገድ ከፍተኛ ቅሬታን እንዳስከተለበት ሲረዳ የስሜት መረበሽን ፈጥሮበት እንደነበር ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የአትሌቱን የቅርብ ምንጮች ጠቅሶ ባለፈው አርብ ዘግቦ ነበር።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ኒው ዮርክ ታይምስ ለሃይሌ እና ለማናጀሩ ማስተባበያ መልስ አልሰጠም። ይሁን እንጂ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች፥ ሃይሌ ጉዳዩን እንዲክድ በወያኔ ባለስልጣናት ጫና እንደሚደረግበት አስቀድመው ግምታቸውን ሲገልጹ ነበር።