ወደፊት መውደቅ! (በዶ/ር ታደሰ ብሩ)
ዶ/ር ታደሰ ብሩ – እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 8 ቀን 2010 በለንደን የሰማዕታት መታሰቢያ ዝግጅት ላይ ያደረጉት ንግግር
ክቡራትና ክቡራን!!!
በጥቅምት 1998 ዓም በግፍ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንን ለመዘከር በተጠራው በዚህ ስብሰባ ላይ እንድናገር እድል ስለተሰጠኝ ምስጋና አቀርባለሁ። የሰኔ 97 እና ጥቅምት 98 ጭፍጨፋዎች እና አፈናዎች ሲፈፀሙ በቦታው የነበርኩ፤ በአፈናውም በቀጥታም በተዘዋዋሪም የተነካሁ በመሆኔ መራር ትዝታዎቼ ህያው ናቸው
ሚያዝያ 30 1997 የነበረው የአንድነትና የደስታ ስሜት፤ ግንቦት 7 ቀን የነበረው ልበ-ሙሉነትና ተስፋ በሰኔ ወር ላይ ተነቅንቆ ጥቅምት ወር ላይ ሲደረመስ ማየት ልብን ይሰብራል።
ህፃናት ሲገደሉ፤ እናቶች ሲያለቅሱ፤ ወጣቶች ሲታፈሱ እያዩ ምንም አለማድረግ ራሱን የቻለ ሰቆቃ ነው። ለአሜሪካና እንግሊዝ ኤምባሲዎች የጎረፈው የድረሱልን እና የእወቁልን ጥሪዎች ብዛት እና የእነሱ ዝምታ ሲጤን “እውን የነፃነትና ዲሞክራሲ አጋር ማነው?” ያስብላል።
አዎ በጥቅምት 98 ህፃናት፣ ወጣቶችና አረጋዊያን በግፍ ተጨፍጭፈዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአካል ጉዳተኞች ሆነዋል። በመቶ ሺህዎች የሚገመት ህዝብ ተደብድቧል፣ ተተፍቶበታል፣ ተሰድቧል፣ ተዋርዷል።
ከዚህ ሁሉ ጋርም ለዓመታት የገነባነውን መሪዎቻችንን የመምረጥና የመሻር ህልም ቅዠት ተደርጎብናል። “እያንዳንዷ ድምፅ ዋጋ አላት!” እንዳላልን ሁሉ ኮሮጆ ሙሉ ድምፅ ዋጋ ሲያጣ እያየን መከላከል አቅቶናል።
የጥቅምትን ፍጅት ተከትለው የመጡ ኩነቶች እጅግ አሳዛኝ እና ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ። አንዳንዶቹ ከማሳዘን ብዛት አስቂኝ ነበሩ።
ለምሳሌ የወያኔ ሰላዮች “እኛ ሞተን የገነባነውን ሥርዓት እናንተ ማኪያቶ እየጠጣችሁት ልትንዱ እንዴት ከጀላችሁ?” እያሉ በግልጽ የሚናገሩበት ጊዜ ነበር። እኔ በግል በተደጋጋሚ እንዲህ ተብዬ “እውነት እንዴት ሞኝ ብሆን ነው የሞቱበትን ሥልጣን በካርድ ይለቃሉ ብዬ ያመንኩት?” ብዩ በራሴ ላይ ስቄዓለሁ፤ ራሴን ታዝቤዓለሁ።
ቀድሞ በየስብሰባው አዳራሽ ከኔወዲያ ለዲሞክራሲ መፋለም ላሳር ሲል የነበረ ወዳጃችሁ ከወያኔ ጋር ሲሞዳሞድ ስታነገኙት፤ ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሲረክሱባችሁ ማየት ተስፋ አስቆራጭ ነው።
ስለ ሰኔና ጥቅምት ፍጅቶች እስካሁን ብዙ ተብሏል። ያም ሆኖ ግን ያልተነገረው ከተገረው በእጅጉ ይበልጣል። በዚህም ምክንያት ወደዚህ ርዕስ ደጋግመን መመለሳችን የሚቀር አይመስለኝም። ያኔ ስለተፈጸሙ የጭካኔ ተግባራት መዘከር ጥሩ ነው። ዝክሮቻችን መቋጫ ከሌላቸው ግን ሰማዕታቱንም የሚያስደስት አይመስለኝም።
ለመሆኑ ጥቅምት 1998 የሆነው ምንድነው? ለምንድነው ፍጹም በሆነ ጭካኔ የተደበደብነው፣ የተገረፍነው፣ የተጋዝነው እና የተገደለነው? ምን ስላደረግን ነው ያ ሁሉ ግፍ የተፈፀመብን?
ለእነዚህ ጥያቄዎች የጋራ መልስ ኖሮን ቢሆን ኖሮ ከዚያ ወዲህ የተፈጠሩ ብዙዎቹን ልዮነቶች ባልኖሩም ነበር:: እንደኔ እምነት በጥቅምት 1998 በጭካኔ የተመታው ያዋጣል ብለን ተስፋ ያደረግንበት የትግል ስትራቴጂ ነው። የሰላም እርግብን ለመግደል እርግብ የመሳሰሉ ህፃናትን ገደለ። መለስ በምን ዓይነት መንገድ ሥልጣን በፈቃዱ በእጁ እንዲወጣ እንደማይፈቅድ ከህዝብ ተነጥሎ ሲቀለብ የቆየን ጦርን ከተማ ውስጥ በማሰማራት እምን ደረስ መሄድ እንደሚችል አሳየን። በጥቅምትና ተከታዮቹ ጥቂት ወራት አገሪቱ ሙሉ በሙሉ የምትመራው በጦር ሠራዊትና በሰላዮች ብቻ ነበር። እነዚህ ደግሞ የአንድ ጎጥ ሰዎች ናቸው። ባጭሩ የጥቅምት ጅምላ ጭፍጨፋ መልዕክት “ሥልጣኔን ከምለቅ አገሪቷን ከነህዝቧ ባቃጥል እመርጣለሁ” ነው። ጥቅምት ላይ ስለሆነው ነገር ግልጽ ያልሆነልን ጉዳዩ ውስብስብ ሆኖ አይደለም። “ወያኔ በሚቆጣጠረው ምርጫ ወያኔን ማሸነፍ የማይቻል ከሆነ ምንድነው መደረግ ያለበት?” የሚለው ጥያቄ ምላሽ እረፍት የሚነሳ መሆኑ ነው። የጥያቄው ቀጥታ ምላሽ ግባችንን አሊያም ስልታችንን መቀየር አለብን የሚል ነው። ሁለቱም አማራጮች ምቾት የሚሰጡ አይደሉም።
እንዲህ መንፈሴ በተረበሸበት እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት እየተፈታተነኝ በነበረበት ወቅት ነበር የጆን ማክስዌል “ወደፊት መውደቅ፤ ስህተቶችን ወደስኬት መረማመጃነት መቀየር /Failing Forward: Turning mistakes into stepping stones for success/ የተሰኘውን መጽሃፍ ያነበብኩት። ይህ መጽሃፍ ስለ ውድቀት /failure/ የነበረኝን አስተያየት ሞርዶታል ብዬ አምናለሁ። በተጨማሪም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከስህተቶቻችን የመማር ችግር ያለብን መሆኑ ምንኛ እንደጎዳን እንዳሰላስል ረድቶኛል። ከጥቂት ወራት በፊት “ወደፊት መራመድ እንዴት አቃተን? ለወደፊቱስ ምን ማድረግ እንችላለን?” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት አጭር ጽሁፍ ወደፊ ት እንዳንራመድ ካሰናከሉን ችግሮቻችን አንዱ ከውድቀቶች መማር አለመቻላችን ነው የሚል ሃሳብ አቅርቤ ነበር። ያኔ እንደገለጽኩት ወደፊት መውደቅ ከማዝገም እጅግ ….. እጅግ … እጅግ ይሻላል። ከማይረባ ስኬት ደግሞ ዋጋ ላለው ጉዳይ ታልሞ ያልተሳካ ሙከራ በእጅጉ ይሻላል።
ከዚህ አንፃር ሲታይ የ97ቱ በምርጫ ካርድ መንግሥትን የማውረድ ሙከራ ባይሳካም ሙከራው ብቻውን ከፍተኛ ዋጋ ያለው ታሪካዊ ክስተት ነው። ድህረ ምርጫ 97 ኢትዮጵያ ከዚያ በፊት ከነበረችው ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች ትለያለች። ስለሆነም የሰማዕቶቻችን መስዋዕትነት መና አልቀረም።
እርግጥ ነው በ1998 ውድቀት ደርሶብናል። መውደቅ በራሱ መጥፎ ነገር አይደለም። ውድቀትን በአጠቃላይ በተመለከተ የሚከተሉትን ሰባት ነገሮች ማለት ይቻላል።
- ውድቀትን ለሁልጊዜው ማስቀረት አይቻልም። መውደቅ የማይቀር ነገር ነው፤
- ውድቀት ክስተት አይደለም። እንደ ስኬት ሁሉ ውድቀትም የሥራ ሂደት ውጤት ነው፤
- ውድቀት ግዑዝ ነገር አይደለም። እኛ ነን ውድቀትን ከግዑዝ ነገር ጋር የምናያይዘው፤
- ውድቀት ጠላታችን መሆን የለበትም። እንዲያውም መድከማችንን የሚነግረን ወዳጃችን ነው፤
- ውድቀት የማይጠገን ወይም የማይመለስ ነገር አይደለም፤
- መውደቅ አሳፋሪም አስነዋሪም ነገር አይደለም። እያንዳንዱን ውድቀት ወደ ስኬት የሚያመራ መረማመጃ ማድረግ ይቻላል፤
- ውድቀት የጉዞ መጨረሻ አይደለም። እንዲያውም ወደ ስኬት ለሚደረግ ጉዞ የሚከፈል ዋጋ ነው።
በ98 ወድቀናል፤ ይሁን እንጂ ሁላችንም ወደ አንድ አቅጣጫ አልወደቅንም። ከፊሎች ወደፊት ወድቀው ተነስተው በአዲስ መንፈስ መንገዳቸውን ቀጥለዋል። ሌሎች ደግሞ ወደኋላ ወድቀው እየዳከሩ ነው። እንደማክስዌል ገለፃ
- ወደ ኋላ መውደቅ ፍርሃትን ያነግሳል። ወደኋላ የወደቀ ሰው በድጋሚ ላለመውደቅ አለመነሳትን ሊመርጥ ይችላል። ቢነሳም እንኳም እርምጃው ፍርሃት እና ጥንቃቄ የበዛበት በመሆኑ ከመውደቁ በፊት በነበረው ጥንካሬና እልህ መቀጠል አይችልም፤
- ወደ ኋላ መውደቅ ስንፍናን ያበረታታል። ጊዜን ይገላል፤ ምርታማነት ይቀንሳል፤ አዳዲስ ሃሳቦችን የማፍለቅንም ሆነ የመቀበል ችሎታን ያሽመደምዳል፤
- ወደኋላ መውደቅ ግብን በጣም ስለሚያርቅ ተስፋ ያስቆርጣል። ይህ ደግሞ ከፍርሃት ጋር ሲጣመር ቀድሞ በጣም ውጤታማ የነበሩ ሰዎችን እንኳን ሳይቀር ሽባ ሊያደርግ ይችላል።
በአንፃሩ ወደፊት የወደቀ ሰው ተነስቶ በራሱ ላይ ስቆ አቧራውን አራግፎ መንገድ እየመረጠ ይሄዳል። ወደፊት ወድቆ የተነሳ ሰው ጭራሹን ካልወደቀ ሰው ይሻላል። ይህ ማለት ግን ወድቆ የተነሳ ሰው የሚመርጠው መንገድ አደጋ የሌለው ነው ማለት አይደለም። አደጋ የሌለው መንገድ የለም። እንዲያውም አዲሱ መንገድ ከቀድሞው የባሰ አደጋ ያለው ያለው ሊሆንም ይችላል። ወደፊት ወድቆ የተነሳ ሰው ወድቆ ጠንክሮ መነሳት ለምዷልና ዳግም የመውደቅ ፍርሃት የለበትም።
ከሰኔና ጥቅምት ጭፍጨፋዎችና አፈናዎች በተገቢው ሁኔታዎች አለመማራችን ለተዘበራረቀ አወዳደቃችን ምክንያት ሆኗል ብዬ አምናለሁ። ጊዜ ወስደን ልንመረምራቸው የሚገቡ በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ
- የ97 እና 98 ን ህዝባዊ መነሳሳት በተለየ ሁኔታ መምራት ይቻል ነበር ወይ?
- ለምንድነው ወያኔ የ98ቱን ሰላማዊ መነሳሳትን በፍጹም ጭካኔ የደፈጠጠው?
- ምንድነው የዚያ ጭካኔ ምንጭ? እንደምን ያለ ቅስቀሳ ነው ወታደሮቹ ህፃናት ግንባር ላይ እንዲተኩሱ ያስቻላቸው?
- ማነው የትግላችን አጋር? ለምንድነው አሜሪካ እና እንግሊዝ የሰሙትን እንዳልሰሙ፤ ያዩትን እንዳላዩ የሚሆኑት? ከዚህ ውጭ መሆን ይችሉ ነበር ወይ?
ጥያቄዎቹ በርካታ ናቸው። አንዳንድ ሰዎች እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ማንሳትና ማውጠንጠን ባለመፈለጋቸው ለወደኋላ መውደቅ አጋለጣቸው። በ1998 በርካታ ዜጎቻችን ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል። የዚያኑ ያህል ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ወገኖቻችን ስነ-ልቦናዊ ሞት ሞተዋል።
ንግግሬን ልቋጭ። በ1998 ወገኖቻችን በግፍ ተገድለውብናል። በርካታ ዜጎች ተደብድበዋል፣ተገርፈዋል። በ1997 ተስፋ ሰጪ የነበረው የትግል ስልት በ1998 ሳንካ ደርሶበታል። “ከዚህ ሳንካ ምን ተማርን?” የሚለው ነገር የወደፊቷን ኢትዮጵያ እድል ይወስናል:: ከውድቀታችን ተምረን መስመራችንን አስተካክለን ከሆነ እሰየው!!! ሰማዕታቱን የምንዘክራቸው እዚያው እወደቅንበት ቦታ ላይ ሆነን ከሆነ ግን ባንዘክራቸው ይሻላል።
ወገኖቼ መውደቅ ያለ ነገር ነው። ወደፊትም ብዙ መውደቆች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ወደፊት ለመውደቅ ዝግጁዎች እንሁን!!!
ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ!!!