የሚሰማ ጆሮ ያለው፤ ይስማ!!!
“ጄኖሳይድ ዋች” ወደ ዘር ማጥፋትና ጅምላ ፍጅት የሚያመሩ ሁኔታዎችን በመከታተል ለመከላከል፤ የዘር ማጥፋትና የጅምላ ፍጅት ከተፈፀመም የወንጀሉ ፈፃሚዎችን ወደ ህግ ለማቅረብ የተቋቋመ ዓለም ዓቀፍ ተሟጋች ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት መንግሥታትና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት የዘር ማጥፋትና የጅምላ ግድያዎችን እንዲከላከሉ፤ ወንጀለኞች ተከሰው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ወትውቷል፤ እየወተወተም ነው። ጄኖሳይድ ዋች የዘር ፍጅትና የጅምላ ጭፍጨፋዎችን በመቃወም የሚደረጉ ህዝባዊ ንቅናቄዎችን በግንባር ቀደምትነት መርቷል፤ አሁንም በመምራት ላይ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በካምቦዲያ፣ በዩጎዝላቪያ፣ በሩዋንዳ፣ በካሜሮን፣ በሱዳን እና ሌሎች በርካታ አገራት ውስጥ የደረሱ የዘር ፍጅቶችን መርምሮ ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድርግ የቻለ፤ በሥራው ውጤትም ዓለም ዓቀፍ ከበሬታን ያገኘ ድርጅት ነው።
ይህ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ በጋምቤላ፣ በኦጋዴን፣ በሃዋሳ፣ በአዲስ አበባ እና ሌሎችም አካባቢዎች የተደረጉ የዘር ፍጅቶችና ኢሰብዓዊ ግድያዎችን በመመርመር፤ በሶማሊያ ውስጥ በሰላማዊ ዜጋ ላይ የተፈፀሙ የጦር ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በመዘርዘር የዚህ ሁሉ ግንባር ቀደም አስተባባሪ የሆነው አረመኔው መለስ ዜናዊ ሄይግ በሚገኘው ዓለም ዓቀፍ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በህግ እንዲታይ ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታትን ጠይቆ ጉዳዩን እየተከታተለ ይገኛል።
በጥቅምት ወር 1998 ዓም በግፍ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንን ለማስታወስ በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ በተጠራው የሰማእታት መታሰቢያ ዝግጅት የዚህ ታዋቂ ድርጅት ፕሬዚደንት የሆኑት ዶ/ር ግሪጎሪ ስታንተን በክብር እንግድነት ተገኝተው ነበር።
ዶ/ር ስታንተን በዚህ ዝግጅት ያደረጉትን ንግግር ጆሮ ያለው ሁሉ ሊሰማው፤ አዕምሮ ያለው ሁሉ በአንክሮ ሊያጤነው የሚገባ ነው። ዶ/ር ስታንተን የመለስ ዜናዊን አገዛዝ “የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ” ብለውታል። በዚሁ ንግግራቸው “የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የመለስ አገዛዝ መውደቁ የማይቀር ነገር ነው” ካሉ በኋላ ለመለስ ወንጀሎች የትግራይ ህዝብ ዋጋ ከፋይ ሊሆን የሚችል መሆኑ እያስጨነቃቸው መሆኑን ገልፀዋል። ለዚህ ግምትም መነሻ የሆኗቸውን በቅርብ ጊዜ የተፈፀሙ የዘር ማጥፋት ፍጅቶችን በምሳሌነት አንስተዋል። በሩዋንዳ፣ ካምቦዲያ፣ እና ሱዳን የደረሱት የዘር ፍጅቶች መሠረታቸው የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ላይ ያጠላውን አደጋ ለመወጣት የነፃነት ኃይሎች ተባብረው መቆም እንዳለባቸው መክረዋል። በተለይም የትግራይ ልሂቃን ላይ የወደቀው ኃላፊነት ከፍተኛ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተውበታል።
ከዶ/ር ስታንስተን ንግግር ውስጥ ሁለት ዓበይት ነጥቦች ላይ ማትኮር እንፈልጋለን
- “የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ” ምን ማለት ነው? ውጤቱስ ምንድነው?
የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኝ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ከራሱ ወገን ውጭ የሆኑትን የአገሪቱን ዜጎች ወሮ እንደያዘው አገር ህዝብ አዋርዶ የሚገዛበት ሥርዓት ነው። የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ መሠረቱ ዘውግ፣ ቋንቋ ወይም ሃይማኖት ሊሆን ይችላል። በብዙ ሁኔታዎች የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ እና የባዕድ ቅኝ አገዛዝ ተመሳሳይ ናቸው። በሁለቱም ውስጥ የሚደረጉ የነፃነት ትግሎችም ተመሳሳይ ባህርይ አላቸው። ሁለቱም ዓላማቸው ህዝብንና አገርን ማዳን ነው። የአገር ውስጥ ቅዥ ተገዢዎች የራሷ ሰንደቅ ዓላማ ባላት አገር ውስጥ መሆናቸው ትግላቸውን ያከብደው እንደሆን እንጂ የሚደርስባቸውን ጥቃት አያቀለውም።
- በዚህ ጉዳይ ላይ የትግራይ ምሁራን ሚና ምን መሆን ይኖርበታል?
ዶ/ር ስታንተን እንደገለፁት፤ እኛም እንደምናውቀው የመለስ አገዛዝ የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ ነው። ይህ አገዛዝ መሠረቱ ያደረገው ትግራይን ነው። በግልጽ ተነገረም አልተነገረ የሥርዓቱ ግብ የትግራይን የበላይነት እና የሌሎች ኢትዮጵያዊያንን የበታችነት ማረጋገጥ ነው። የትግራዩ ጉጅሌ እስካሁን ብዙ ተሳክቶለታል። እንደማንኛውም ቅኝ ገዢ ቁልፍ ቦታዎችን በጉጅሌው አባላት እየተቆጣጠረ በወረራ የያዘዘው ግዛት ከዚያው አካባቢ በተገኙ ባንዳ ምስለኔዎች ተከልሎ ይገዛል። ዶ/ር ስታንተንን ያሰጋቸው ይህ ሥርዓት የተናጋ እለት ምን ይሆናል የሚለው ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ እኛንም በእጅጉ ያሳስበናል።
የትግራዩ ጉጅሌ ሥልጣን ከእጁ የወጣ እለት በቅኝ አገዛዝ የተማረረው ህዝብ የሚወስደውን እርምጃ መቆጣጠር ያዳግት ይሆናል። የዘር ፓለቲካ መለስ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥታዊ ፓሊሲ ሆኖ ሲሰራበት የቆየ በመሆኑ ሊያመጣ የሚችለው መዘዝ ቀላል እንደማይሆን መገመት ብልህነት ነው። በዚህ መዘዝ ደግሞ ክፉኛ ተጠቂ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንፃራዊ መልኩ የትግራይ ምሁራን ከወያኔ መስመር እየወጡ መሆኑ በጎ ጅምር ነው። ቀድሞ የመለስ ዜናዊ አማካሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ተኮላ ሃጎስ፤ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ እና በህዝቧ ላይ የሚፈጽማቸውን ግፎች ያለ ትግራውያን እርዳታ ሊያደርገው ባልቻለ ነበር ሲሉ ከሣምንታት በፊት ለንባብ ባበቁት ጽሁፍ መግለፃቸው እና የትግራይ ተወላጆች የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርገውን ትግል እንዲቀላቀሉ ማበረታታቸው መልካም ነገር ነው።
ሆኖም ግን ከትግራይ ምሁራን ከዚህ በላይ እንጠብቃለን። ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ማስቀረት የምንችለው አሁን ነው። የትግራይ ህዝብ ጥቅም በዘላቂነት የሚከበረው የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት ሲረጋገጥ መሆኑ ለሁሉም የትግራይ ምሁራን ግልጽ ሊሆን ይገባል እንላለን። ስለሆነም ለራሳችሁ፣ ለትግራይ ህዝብ፣ ለትግራይ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለኢትዮጵያ ደህነት ስትሉ የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝን ለማጥፋት በምናደርገው ትግል ከሌሎች ወገኖቻችሁ ጎን እንድትሰለፉ ጥሪዓችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!