በዲላ ዩኒቨርስቲ በተቀሰቀሰ ሁከት ተመሪዎች ተጎዱ

(ሙሉ ገ.)

ቅዳሜ ህዳር 4 ቀን 2003 ዓ.ም ብዙነሽ ብርሃኑ የተባለች የሦስተኛ ዓመት የታሪክ ዲፓርትመንት ተማሪ በዋናው ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ አድራ ወደ አዲሱ ሰመራ ካምፓስ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ የሚያስጉዘውን መንገድ ስታቋርጥ ዋለሜ በተባለው ወንዝ ውስጥ ሰጠመች። ይህንኑ የመስጠም አደጋ ተማሪዎች ለዩኒቨርስቲው አስተዳደር ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ልጅቷን በሕይወት ለማትረፍም ኾነ አስከሬኗን ለማግኘት ፈጣን የኾነ ምላሽ ባለማግኘታቸው ምክንያት ባነሱት የተቃውሞ ድምፅ  በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሁከቱ እንደተቀሰቀሰ አንድ የዩኒቨርሲቲው መምህር ለአዲስ ነገር ሪፖርተር በስልክ አስረድተዋል።

ትላንት ሕዳር 8 ቀን 2003 ዓ.ም ረፋድ ላይ በዲላ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በተፈጠረው በዚሁ የተማሪዎች ሁከት ምክንያት የተፈነከቱ ተማሪዎችም ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ከዚህም በተጨማሪ በሁከቱ የዩኒቨርሲቲው መስኮቶች እና በሮች ተሰባብረዋል፤  የመመገቢያ ቁሳቁሶች ወድመዋል፤ በአካባቢው ፌዴራል ፖሊስ ጣልቃ በመግባት ግቢውን ተቆጣጥሯል።

እንደ መምህሩ ገለጻ ለተማሪዎቹ ቁጣ መቀስቀስ ምክንያት የኾነውን የተማሪ ብዙነሽን አስከሬን ለማግኘት እና ለማውጣት ዲላ ዩኒቨርስቲ የአካባቢውን ዋናተኞች እየተጠቀመ ቢኾንም ዋናተኞቹ ወንዙ የአምልኮ ሥርዐት የሚካሄድበት እና በየዓመቱም የሰው ግብር የሚበላ ነው በማለት ወደ መሀል እና ወደ ታች ዘልቀው ለመግባት ድፍረት በማጣታቸው ሳይሳካ እንደቀረ  ጨምረው ገልጸዋል።

ከትላንት ጠዋት ጀምሮ “መጀመሪያ ልጅቷ ትፈለግ! አትኩሮት ታግኝ!” በሚል ትምህርት ያለመማር እና ምግብ ያለመመገብ አድማ የመቱት ተማሪዎች ሁከት ፈጥረው መስታዎቶችን በመሰባበር የመማር- ማስተማር ሂደቱን በማስተጓጎል፣ በምሳ ሰዓት ላይ ምግብ ለመመገብ ካፌ ከገቡ ተማሪዎች ጋራ በተፈጠረ ግርግር ቁጥራቸው በውል ባልታወቀ ተማሪዎች ላይ የመፈንከት አደጋ ደርሶባቸዋል። በመስታዎት የመቆረጥ እና በግርግሩ እና በተቃውሞው በተነሳው ሁከት የመረጋገጥ አደጋ ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ተማሪዎች እንደነበሩም አንድ የተማሪ ካውንስል የአመራር አባል ለሪፖርተራችን አስረድቷል።

ትላንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ በርካታ የመንግሥት የደኅንነት እና የመረጃ ሠራተኞች እንዲሁም የድንጋይ መከላከያ ሙሉ ትጥቅ ያደረጉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ዋናውን ግቢ ከተቆጣጠሩ በኋላ ለሁለት ተከፍለው የነበሩት ተማሪዎች አንድ ላይ በመኾን ተቃዉሟቸውን ሲገልጹ ነበር። ፌዴራል ፖሊስ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የነበሩትን ተማሪዎች ቀስ በቀስ ከግቢው እንዲወጡ በማድረግ ከግቢው ውጭ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል።

ማምሻውን ይህን ዜና እስከምናጠናክርበት ጊዜ ድረስ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ካፌ መመገባቸውን አቁመው በጩኸት አና በመዝሙር ቁጣቸውን እየገለጹ ሲኾን ፌዴራል ፖሊስም ከግቢው ውስጥ በተጠንቀቅ እየጠበቀ ነው። የሦስተኛ ዓመት የታሪክ ተማሪ የነበረችው ብዙነሽ ብርሃኑ ቤተሰቦቿ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ክፍለ አገር እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።