ስምንት ሕፃናት ደቡብ ክልል ማሳደጊያ ውስጥ ሞቱ

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ፍራንቼስኮ በተባለ የሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ፣ ስምንት ሕፃናት በኩፍኝ ሞቱ ሦስቱ ሕፃናት ለአሜሪካውያን አሳዳጊዎች በጉዲፈቻ ተሰጥተው የነበሩ መሆኑን፣ ማሳደጊያው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ፍትሐ ብሔር ቦሌ ምድብ ችሎት ህዳር 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ገልጿል፡፡ ማሳደጊያው ይህን ሊያሳውቅ የቻለው ከክልሉ በአደራ የተረከባቸውን 14 የጉዲፈቻ ውሳኔ ያረፈባቸውን ሕፃናት ለጉዲፈቻ አድራጊዎቹ ወኪል እንዲያስረክብ በታዘዘው መሠረት ቀርቦ ባስረዳበት ጊዜ ነው፡፡

ማሳደጊያው ሕፃናቱ መሞታቸውን ባስረዳበት ደብዳቤ ከሞቱት ሕፃናት ውስጥ ውሳኔ ያረፈባቸው ተረፈ ኃይሉ፣ ምህረት መሐመድ፣ ተገኝ ታደሰና ተረፈች አቡኮ የተባሉ ሕፃናት እንደሚገኙበት ይግለጽ እንጂ፣ የመጨረሻዋ ሕፃን ሞት ያልተረጋገጠ መሆኑን ከፍርድ ቤቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ማሳደጊያው አሥራ አራቱን ሕፃናት ለጉዲፈቻ አድራጊ ቤተሰቦች ወኪሎች እንዲያስረክቡ በፍርድ ቤቱ ታዞ የነበረ ቢሆንም፣ ሕፃናቱ ከዚህ በፊት ያድጉበት የነበረው ስፔሻል ሚሽን ፎር ኮሚዩኒቲ ቤዝድ ዴቨሎፕመንት የሚባል ማሳደጊያ በክልሉ መንግሥት ከተዘጋ በኋላ፣ በአደራ የተረከባቸው በመሆኑ ማስረከብ እንደማይችል ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱም ማሳደጊያው ሕፃናቱ የጉዲፈቻ ውሳኔ ያረፈባቸው በመሆኑ ለህጋዊ ወላጆች ወኪል እንዲያስረክብ በድጋሚ ትዕዛዝ ሊያስተላልፍ ችሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ የደቡብ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሕፃናቱን ተረክቦ በአደራ የሰጠ አካል በመሆኑ፣ ሕፃናቱን ቀርቦ እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም በትዕዛዙ መሠረት ቀርቦ ባለመፈጸሙ፣ የቢሮው ኃላፊ በፌዴራል ፖሊስ ታስረው እንዲቀርቡና ልጆቹን እንዲያስረክቡ ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

በዚህ ትዕዛዝ መሠረት የቢሮው ኃላፊ አቶ ስኳሬ ሸዳ፣ የሴቶች ዘርፍ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ኃይሉና የሕፃናት ዘርፍ ዳይሬክተር ወ/ሮ አሸነፈች አድማሱ ከሞት የተረፉትን ሕፃናት በፌዴራል ፖሊስ አማካይነት ይዘው ህዳር 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ ቀርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ሕፃናቱ ውሳኔ ካረፈባቸው ከሐምሌ ወር ጀምሮ እንዲያስረክቡ ሲጠየቁ ለምን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳላከበሩ ሲጠይቃቸው፣ ሕፃናቱን ማሳደጊያ ከተዘጋባቸው ሌሎች ሕፃናት ጋር ወደ ሌሎች ማሳደጊያዎች በአደራ ያስገቧቸው መሆኑን ገልጸው፣ ሕይወታቸው በድጋሚ ይጣራ በሚል መነሻ እንዲቆዩ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤት በሕፃናቱ ላይ ውሳኔ አስተላልፎ እያለ የክልሉ መንግሥት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ያልፈጸመው በክልሉ ስም የመጣ ትዕዛዝ ባለመኖሩ ነው በሚል ምክንያት ባቆየበት ወቅት፣ ልጆቹን በአደራ ባስቀመጠበት ማሳደጊያ ውስጥ በተከሰተው ኩፍኝ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ልጆች ውስጥ አራት ሕፃናት መሞታቸውንና በተጨማሪም ሌሎት አራት ሕፃናት መሞታቸውን ኃላፊዎቹ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ኃላፊዎቹ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት ያልፈጸሙት በክልሉ ስም የመጣ ውሳኔ ባለመኖሩ ባለማወቅ መሆኑንና ወደፊት ለሚሰጡ ትዕዛዞች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ ፍርድ ቤቱን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ቢሮው በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት ያልፈጸመው በቂ ግንዛቤ ሳይኖረው መሆኑን በመግለጽ፣ በሕጉ መሠረት በማስጠንቀቂያና በተግሳጽ እንዳሰናበታቸው ህዳር 12 ቀን 2004 ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ ያስረዳል፡፡
የጉዲፈቻ ውሳኔ ተሰጥቶባቸው በኩፍኝ ምክንያት ሕይወታቸው ካለፈው ሕፃናት አንዱ ሕፃን ተገኝ ታደሰ፣ በርናርድ ፍራንክሊን ሉዊስ ጁኒየርና ኤሪን ክርስቲና ሉዊስ ለተባሉ አሜሪካውያን ጥንዶች በጉዲፈቻ ተሰጥቶ ሒደቱ እስኪያልቅ በመጣበበቅ ላይ ነበር፡፡
ሕፃን ተገኝ ለጉዲፈቻ ከመሰጠቱ በፊት የሁለት ወር ዕድሜ እያለው መጋቢት 21 ቀን 2003 ዓ.ም. ተጥሎ የተገኘ መሆኑን፣ ቀደም ሲል ያድግበት በነበረው ስፔሻል ሚሽን ፎር ኮሚዮኒቲ ቤዝድ ዴቨሎፕመንትና በጉዲፈቻ አድራጊ ቤተሰቦቹ ወኪል ወርልድ አሶስዬሽን ፎር ችልድረን ኤንድ ፓረንትስ መካከል ግንቦት 3 ቀን 2003 ዓ.ም. የጉዲፈቻ ውል ተፈጽሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህን የጉዲፈቻ ውል ሐምሌ 6 ቀን 2003 ዓ.ም. አጽፅቆታል፡፡

በኩፍኝ ምክንያት ከሞቱት ሕፃናትና የፍርድ ቤት ውሳኔ ካረፈባቸው መካከል ሁለተኛው ተረፈ ኃይሉም እንዲሁ ብሬክዌል ዳቢህ ኢንግና ታና ኤሪን ራይችትኒክ ኢንግ በተባሉ አሜሪካዊያን ጥንዶች በጉዲፈቻ ተሰጥቶ ሒደቱ እስኪያልቅ በመጠባበቅ ላይ ነበር፡፡
ሕፃኑ የ10 ቀናት ዕድሜ እያለው መጋቢት 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ተጥሎ የተገኘ ሲሆን፣ ጉዲፈቻ አድራጊ ወላጆቹ በወኪላቸው ወርልድ አሶስዬሽን ፎር ችልድረን ኤንድ ፓረንትስ አማካይነት ከተመሳሳይ ማሳደጊያ ጋር ሚያዝያ 21 ቀን 2003 ዓ.ም. የጉዲፈቻ ውል ተፈራርመው ፍርድ ቤቱ ሰኔ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. ውሉን አፅድቆታል፡፡

ሦስተኛዋ የኩፍኝ ሰለባ የሆነችው ሕፃን ምህረት መሐመድ ዶ/ር ኢላና ናሽ ለተባሉ አሜሪካዊት ሴት ለጉዲፈቻ ተሰጥታ የነበረ መሆኑን፣ ወላጅ እናቷ የልጅቷን አባት የማታውቅ መሆኑንና ማሳደግ እንደማትችል በመግለጽ፣ ሕፃኗ በጉዲፈቻ እንድትሰጥ ተስማምታ የነበረ መሆኑን ከውሳኔው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ዶ/ር ናሽ የ11 ወራት ዕድሜ የነበራትን ሕፃን በጉዲፈቻ ወስዶ ለማሳደግ በተመሳሳይ ወኪል ከተመሳሳይ የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅት ጋር ግንቦት 10 ቀን 2003 ዓ.ም. የጉዲፈቻ ውል የተፈራረሙ ሲሆን፣ ውሉን ፍርድ ቤቱ ሰኔ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. አፅድቆታል፡፡
የክልሉ መንግሥት ውሳኔ ካረፈባቸው ሕፃናት መካከል ሞተዋል ተብለው ለፍርድ ቤቱ ሪፖርት ከተደረገባቸው ሕፃናት ውስጥ፣ ሕፃን ተረፈች አቡኮ የተባለችውን ልጅ የእኔ ናት ብሎ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ያቀረበ አካል ባለመኖሩ፣ ሞቷ እርግጠኛ አለመሆኑን ከፍርድ ቤቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሕፃናቱን ሞት ከማሳደጊያው ቅዱስ ፍራንቼስኮና ከክልሉ ኃላፊዎች ከተረዳ በኋላ የፌዴራል ፖሊስ የሕፃናቱን ሞት ምክንያት በምርመራ አጣርቶ ውጤቱን ታህሳስ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. እንዲያቀርብ አዟል፡፡