በበረከት ስሞኦን ቁጥጥር ሥር ያለው ብአዴን በግምገማ እየተተራመሰ ነው። ለአገዛዙ ያልተመቹ ሁሉ በግንቦት 7 አባልነት እየተፈረጁ መሆኑ ተዘገበ

ዘረኛው መለስ ዜናዊ በበላይነት በሚመራው ህወሃት ሥር ተቀጥያ በመሆን ላላፉት 20 አመታት የህወሃትን ጸረ አማራ ፖሊሲ ሲያስተገብሩና ሲያስፈጽሙ የኖሩ በዚህም የተነሳ የገዛ ወገኖቻቸውን ህዝብ መከራና ሲቃይ ዕድሜ ሲያራዝሙ የቆዩ የብሄረ አማራ ድርጅት የክልልና የዞን አመራርና አባላት በሌላ ዙር ግምገማ እየተተራመሱ መሆኑን የግንቦት 7 ዘጋቢ ከባህር ዳር ባስተላለፈው ዜና ገለጸ።

በአማራ ክልል ያሉትን አባላት በግምገማ የማተራመሱ ሥራ የተጀመረው ፤ በክልሉ ያሉ ወጣቶች ቁጥሩ እየጨመረ በመጣው የሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት እጅግ እየተማረሩ በአገዛዙ ላይ የሚያሰሙት ግልጽ ተቃውሞ በአደባባይ ላይ መሰማት በመጀመሩ፤ በክልሉ ታምቆ ከኖረው ጸረ ወያኔ ስሜት ጋር ተዳምሮ ባልተጠበቀ ሰዓት ህዝባዊ አመጽ ሊቀሰቅስ ይችላል ተብሎ ስለተሰጋ፤ ነባር የብአዴን አባላትን በሙስናና በዲስፒሊን ሰበብ ከሥራ አሰናብቶ ወጣቶችን ሥራ ለማስያዝ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ነው ተብሎአል።

ከበረከት ስሞኦንና ከአዲሱ ለገሰ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው አንዳንድ የክልሉና የዞኑ ብአዴን አመራር አባላት በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸው እየታወቀ ለበርካታ አመታት ዝም ሲባሉ እነደነበረ የዘገበው ዘጋቢያችን፤ በሙስና የአስተዳደር በደል ውስጥ እጃቸው ያልገባው በርካታ አባላቱ እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በኑሮ ውድነቱ እየተሰቃዩ በመሆናቸዉ በአገዛዙ ላይ የምር ተቃውሞ እያሰሙ መምጣታቸው አገዛዙ ያልጠበቀው ሌላ እራስ ምታት እንደቀሰቀሰበት ገልጾአል።

የበርካታ አባላቶቹ ልብ መክዳት ያሳሰበው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ ቡድን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት እምነት ሊጣልባቸው የማይችሉቱ ተባረው በምትካቸው ትምህርታቸውን ከከፍተኛ ትምህረት ተቋማት ጭምር አጠናቀው ለአመታት ሥራ አጥ ሆነው የተቀመጡት እየተመለመሉ እንዲገቡና የመንግሥት ሥራ እንዲሰጣቸው እንቅስቃሴ በመጀመሩ፤ የእርምጃው ሰለባ በሆኑት ነባር አባላትና ውሳኔውን በሚያስፈጽሙ አመራሮች መካከል ከፍተኛ የሆነ ግጭት ተፈጥሮአል።

በምስራቅ ጎጃም የምርጫ 97 ውጤት ተጭበርብሮአል ተብሎ እንዲጣራ በተወሰነበት ወቅት የዳኝነት ሥልጣኑን በመጠቀም ፍርድቤት የሰጠውን ውሳኔ ገልብጦ ለወያኔ ታማኝነቱን ያስመሰከረውና ለበረከት ስሞኦን ቀረቤታ እንዳለው የሚነገርለት የሺጥላ እምሩ የተባለ፤ በአሁኑ ሰዓት የምስራቅ ጎጃምና የአዛ ዞን የጸረ ሙሲና ኮሚሽን ሃላፊ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው የብአዴን አባል ሰሞኑን በግምገማ ስም ከሃላፊነቱ ተወግዶ በቁም እስር ላይ እንደሚገኝ ዘጋቢያችን አረጋግጦአል።

ይህ በዚህ እንዳለ ወያኔ አገር አቀፉን የመምህራን ማህበር አፍርሶ በምትኩ ታማኝ አባላቶቹ የሚመሩት ማህበር በክልል ደረጃ ካዋቀርበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ ክልል መምህራን ማህበር ውስጥ በመንቀሳቀስ የክልሉ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቃውን መምህር መንግስቱ አህመዴን፣ ከስልጣን ለማስወገድ ወያኔ ዘመቻ መጀመሩን ለማወቅ ተችሎአል።

እንደምንጮቻችን መረጃ ወያኔ መምህሩን ከስልጣኑ ለማስነሳት የፈለገው ናዝሬት ተካሂዶ በነበረው አለማቀፍ የመምህራን ጉባኤ ላይ “የመምህራንን የደሞዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እድገትንና የማስተማርና ሀሳብን የመግለጽ መብቶች ፣ ከሁሉም በላይ መምህራን ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ እንዲሆኑ፣ በሰለማዊ ሰልፍ ሳይቀር መብታቸውን እንዲጠይቁ ሊፈቀድላቸው ይገባል” የሚሉ ሀሳቦችን በመሰንዘሩ እንደሆነና እርሱ ያቀረበው ሃሳብ ለውይይት አለመቅረቡ አበሳጭቶት ስብሰባውን ረግጦ በመውጣቱ ነው።

መምህር መንግስቱ አህመዴ የኢህአደግ አባል እንደሆነ ሲታወቅ የመምህራንን መብት መከበርንና የመማር ማስተማር ነጻነትን አስመልክቶ ከአለቆቹ ጋር እየተጋጨ በመምጣቱ በበርካታ መምህራን ዘንድ አድናቆትና ፍቅር ለማተረፍ የበቃ እንደሆነ ይነገርለታል።

በአማራ ክልል የመምህራን ፕሬዝዳንት አቋም ያልተደሰቱ የወያኔ ባለስልጣናት በተለያዩ የወረዳ ትምህርት ቤቶች ተገኝተው “የማህበሩ ሊቀመንበር የግንቦት7 አባል ነው፤ መምህራን የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርጉ እና ከመንግስት ጋር እንዲጋጩ እየቀሰቀሰ ነው” በማለት ግለሰቡን ለማጥቃት ቅስቀሳ እንደጀመሩበት ተያይዞ የደረሰን ዜና አረጋግጦአል።

ሆኖም የክልሉ መምህራን ከሊቀመንበራቸው ጎን በመቆም “የማህበሩ ሊቀመንበር ከስልጣን የሚወገድ ከሆነ፣ መምህራን የራሳቸውን እርምጃ ይወስዳሉ” በማለት በማስጠንቀቃቸው ና በአቋማቸውም በመጽናታቸው አገዛዙ ያሰበውን እርማጃ ለመውሰድ እንደተደናገጠና፣ ነገር ግን ከአገር አቀፉ መምህራን ማህበርም ሆነ ከሌሎች ንኡስ ማህበራት ጋር እንዳይገናኝ እንዳደረገው ታውቆአል።

በአማራ ክልል የብአዴን አባላት መካከል በተነሳው ክፍፍል በቅርቡ መሳሪያ በመማዘዝ እስከመጋደል የደረሱ እንደነበሩና በጎንደር ከ180 በላይ አባላት በፈቃዳቸው ከአባልነት መሰናበታቸውና አብዛኛዎቹ ለድርጅቱ የነበራቸውን ታማኝነትና ታዛዝነት ትተው አገዛዙን በማማረር እንደተጠመዱ መዘገባችን ይታወሳል።