የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ በዘረፋ ከአገር የሚያሸሸው ገንዘብ መጠን 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተጋለጠ

በዘረኛው መለስ ዜናዊ የሚመራው የትግራይ ገዢ ጉጂሌ ቁንጮዎች እንደ አውሮጵያዊያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ2000 እስከ 2009 ባለው የ9 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ብቻ ከ 11 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ከአገር በማሸሽ በውጪ አገር ባንኮች በግል ሂሳባቸው እንዳከማቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሀግብር ሥር ጥናት ያካሄደው “ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ” የተባለው አለማቀፍ ተቋም ባወጣው የቅድመ ዳሰሳ ሪፖርት አጋለጠ።

ጥናቱን ባካሄደው ተቋም መረጃ መሠረት፦ በስርቆት፣ በሙስናና በተለያዩ ህገወጥ መንገዶች የተገኘ ነው የተባለው ይህ ትልቅ መጠን ያለው ገንዘብ፤ መለስ ዜናዊ እራሱ በተገኘበት አለም አቀፍ መድረክ ከዛሬ 6 ወር በፊት ይፋ ከሆነው 8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ3 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብልጫ ያለው መሆኑም በጥናቱ ተገልጧል። ይህ 3 ቢሊዮን 260 ሚሊዮን ዶላር በአንድ አመት ጊዜ ማለትም የቀድሞው ሪፖርት ባልሸፈነው የ2009 ዓም ብቻ የተዘረፈ መሆኑ ጥናት አድራጊውን ተቋም ሳይቀር አስደንግጦአል።

በአለም በድህነት ከመጨረሻዎቹ አገሮች ተርታ ከሆነቺው አገራችን ተሰርቆ በውጪ አገር ባንኮች የተደበቀው ይህ ገንዘብ ምንጩ፤ ለልማት፤ ለድህነት ቅነሳና ለሰብአዊ እርዳታ ከምዕራባዊያን አገሮች የተገኘ እንደሆነ ሲታወቅ ባለሥልጣናቱ በጫረታ፤ በሙስናና በዘረፋ ገንዘቡን አጭበርብረው በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ሥም ከባህር ማዶ በከፈቱት ባንኮች ያሸሹት እንደሆነም ተገልጾአል።

አሥራ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ማለት በአገራችን ገንዘብ ሲመነዘር ከ 187 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ሲታወቅ፤ ይህ ደግሞ በምድር ላይ ሊሠራ ወደሚችለው ልማት ቢተረጎም መለስ ዜናዊ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 20 አመታት 80 ቢሊዮን ብር በማውጣት 27 ሺ ኪሎሜትር መንገድ ሰርቻለሁ በማለት የሚነዛውን ጉራ ከእጥፍ በላይ በማሳደግ፤ መላውን የአገሪቱን ገጠሮች በአቅራቢያቸው ካለው ትላልቅ ከተሞች ጋር ማገናኘት የሚችል 60 ሺ ኪሎሜትር ርዝመት ያላቸው መንገዶችን መገንባት የሚችል ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ያስችል ይሆናል በሚል ስሌት ያለምንም ጥናትና ዕቅድ በህዝብ ላይ የተጫነውን የአባይ ግድብ መዋጮ 54 ቢሊዮን ብር በቀላሉ በመሸፈን በተቀረው 133 ቢሊዮን ብር ፤ ከ4 ሚሊዮን በላይ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉትን ወገኖች፤ በአሁኑ ጊዜ በምግብ ለስራ ፕሮግራም የታቀፉትን ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች ጎዳናዎች ላይ ወድቀው በቆሻሻ ገንዳዎች ላይ ምግብ እየለቀሙ የሚኖሩትን ዜጎች ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማቋቋም እንደሚያስችል መረጃዎች ያመለክታሉ።

ህብረሰተቡን እያስመረረ ያለው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዬው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትም እንዲሁ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንስ እንደነበር ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህንን ጥናት ያካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ተራዲኦ አካል የሆነው ተቋም “የኢትዮጵያ ህዝብ በዝርፊያ የተነሳ ደሙ ሁሉ ተመጥቶ አልቋል፣ ከማለት አልፎ ፣ “ኢትዮጵያዊያኖች ከድህነት ለመውጣት የቱንም ያክል ቢፍጨረጨሩ፣ አሁን በሚታዬው ዝርፊያ ወደ ታች የሚፈስን ወንዝ፣ ወደ ላይ በመዋኘት ለመጨረስ ሙከራ እንደማድረግ ይቆጠራል።” ሲል የመለስ አገዛዝ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ አሰልፋታለሁ እያለ በየጊዜው የሚያውራውን ወሬ ተረት ተረት አድርጎታል።

በሙስና ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተዘፍቀው ገንዘባቸውን በውጭ አገር ባንኮች በማስቀመጥ ላይ የሚገኙት በአብዛኛው እራሱ መለስ ዜናዊና ባለቤቱ አዜብ መስፍንን ጨምሮ ከፍተኛ ስልጣን የተቆናጠጡ ጥቂት የህወሀት ጄኔራሎችና ባለስልጣናት ናቸው።

አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በቅርቡ ባወጡት ጥናታዊ ጽሁፍ አሁን ይፋ የሆነው ተጨማሪ 3 ነጥብ 26 ቢሊዮን ዶላር ሳይካተት ባለፈው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ይፋ የሆነው ከኢትዮጵያ የተዘረፈውን 8 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ወደ አገር ቤት ቢመለስ ለአባይ ግድብ ማሰሪያ የሚዋጣውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ሸፍኖ፣ 90 የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ 18 ዩኒቨርሲቲዎች፣ 27 ኮሌጆች፤ 36 ዘመናዊ ሆስፒታሎች፤ 180 ጤና ጣቢያዎች፤ 6 የዘይት ፋብሪካዎች፤ 4 የስሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲሁም አራት እጂግ ከፍተኛ የሚባሉ አግሮ ኢንደስትሪዎችን ለማቋቋም ያስችላል።

በትራንስፎርሜሽን እና እድገት ስም የመለስ አገዛዝ ባለፉት 10 አመታት ብቻ ከቻይናና ከህንድ መንግስታት ከ 25 ቢሊዮን ዶላር በላይ መበደሩን ቀደም ተብሎ መዘገቡ ይታወሳል። የመለስ ባለስልጣናት ለሚያካሂዱት ዘረፋ ፣ መጪው ትውልድ ከፍሎ የማይጨርሰው እዳ ውስጥ እየገባ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 10 ዓመታት በሙስና ወደ ውጭ ባንኮች የፈሰሰውን ገንዘብ ለመቆጣጠር ተችሎ ቢሆን ኖሮ ፣ የኢትዮጵያ የዚህ አመት በጀት 300 ቢሊዮን ብር ይደርስ እንደነበር ኢሳት ከባለሙያዎች ያገኘውን ሙያዊ ትንበያ አስደግፎ ዘግቦአል።

እንደኢሳት ዘገባ በከፍተኛ ደረጃ ዝርፊያ ከሚካሄድባቸውና የኦዲት መስሪያቤቶችን የምርመራ ውጤት ለመቀበል ፈቃደኛ ከማይሆኑት መስሪያ ቤቶች መካከል ደግሞ መከላከያ ሚኒስቴር አንዱ ነው።

በሳሞራ የኑስ የሚመራው መከላከያ ሚኒስቴር፣ ለጦር ጀኔራሎችና ለህወሀት ከፍተኛ ባለስልጣናት እቃዎችን ያለቀረጥ እንዲያስገቡ በማድረግ፣ ከፍተኛ ዝርፊያ እንደሚያካሂድ ኢሳት በቅርቡ በሰራው የዶኩመንታሪ ፊልም ማጋለጡ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ጉምሩክ፣ ቴሌኮሚኒኬሽን፣ መብራት ሀይል እና ዋና ዋና የገንዘብ ምንጭ የሆኑ ተቋማትን የተቆጣጠሩት፣ የህወሀት ባለስልጣናት፣ ከመስሪያ ቤቶች ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እየዘረፉ ነው እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። የወያኔ ባለሥልጣናት የለየለት ዘረፋ ላይ የተሰማሩት ከምርጫ 97 ወዲህ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ ተጡዋጡፎ መካሄዱን የፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ዘገባ ያመልክታል።

የአለም መንግስታት በአለም እጅግ ደሀ ከሆነችው እና በምጽዋት ከሚያኖሩዋት ኢትዮጵያ፣ ይህን ያክል ገንዘብ መዘረፉን ከሰሙ በሁዋላ የሚያወጡት መግለጫ በጉጉት እየተጠበቀ ነው ተብሎአል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ቱርክ ላይ ዘረኛው መለስ ዜናዊ በተገኘበት ታላቅ አለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ያጋለጠው 8 ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ዘረፋን አስመልክቶ ወያኔ ሹሞች እስከዛሬ ቃል እልተነፈሱም።

ሰሞኑን ይፋ የተደረገው ሪፖርት አዘጋጆች ” ኢትዮጵያውያን እዬደሙ ነው በማለት” የዝሪፊያውን አስከፊነት በሪፖርታቸው ላይ አስፍረዋል።