አቡጊዳ – አንድነት ነገ ጠቅላላ ጉባኤ ያደርጋል፤ ፓርቲዉን ለመምራት ዲሞክራሲያዊ ፉክክር እየታየ ነዉ !
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ነገ ጠቅላላ ጉባዔዉን ያደርጋል። በአገሪቷ ካሉ ክልሎች በሙሉ፣ በአካባቢዉ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተመርጠዉ የመጡ የአንድነት ፓርቲ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ፣ የፓርቲዉ የላእላይ ምክር ቤትም የሚመርጡ ሲሆን፣ የድርጅቱ የወደፊት አቅጣጫ ላይ ሰፊ ዉይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በተሻሻለዉ የድርጅቱ ደንብ መሰረት ጠቅላላ ጉባዔዉ የድርጅቱን ፕሬዘዳንት የሚመርጥ ሲሆን የተመረጡት ፕሬዘዳንት የካቢኔዉ ወይንም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ሰይመዉ በላእላይ ምክር ቤቱ ያጸድቃሉ።
የአንድነት ፓርቲን በሊቀመንበርነት ለመምራት ሶስት አባላት እራሳቸዉን ለእጩነት ያቀረቡ ሲሆን ፣ የአባላትን ድምጽ ለማግኘት ዘመቻ እያደረጉ እንደሆነም ለማወቅ ችለናል።
አሁን የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነዉ የሚሰሩት፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ዶር ነጋሶ ጊዳዳ፣ በድጋሚ ሊቀመንበር ለመሆን እጩ ሆነዉ የቀረቡ ሲሆን፣ በዪኒቲ ዪኒቨርሲቲ በመምህርነት ያገለገሉት፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ፣ ዶር ነጋት አስፋዉ፤ እንዲሁም ከአንድነት ፓርቲ ጋር የተዋሃድዉ የብርሃን ለዲሞርካሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት፣ በኢሰመጉ ዉስጥ የሰሩትና በኢንጂነሪንግ ሞያ ላይ የተሰማሩት አቶ ዘለቀ ረዲ ሊቀመንበር ሆነን ፓርቲዉ መምራት እንችላለን እያሉ ነዉ።
በአገራችን ባሉና በነበሩ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ልማድ ከሆነዉ ከሚስጥራዊና የድብቅ አሰራር ዉጭ፣ ነጻና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ፣ የፓርቲዉ ፕሬዘዳንት ለመሆን የተለያዩ እጩዎች መቅረባቸዉና እየተፎካከሩ መሆናቸዉ ፣ የአንድነት ፓርቲ ዲሞክራሲን፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማዉራት ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር እያሳየ እንደሆነ የሚያመለክት እንደሆነ አባላት እየተናገሩ ሲሆን ፓርቲዉ ከላይ ወደ ታች ሳይሆን ከታች ወደ ላይ የሆነ አሰራር እንዳለዉም የሚያሳይ ነዉ።