ኃጥዓን በሠለጠኑ ግዜ ህዝብ ያልቀሳል!!!
በአገራችን ውስጥ ህዝብ ማልቀሱን አላቆመም። መለስ ዜናዊ የሚመራው ዘረኛና ነውረኛ ቡድን በስልጣን ላይ ከተቆናጠጠ ወዲህ ደግሞ ሮሮው በጥልቀት ልቅሶው በስፋት ቀጥሏል። በኢትዮጵያችን ውስጥ ህዝብ ያዘነበትና የተከፋበት ዘመን እንዲህ እንደ መለስ ዜናዊ ዘመን ያለ አልታየም።የሮሮው ጥልቀት የኔሰው ገበሬን የመሰለ ዜጋ በራሱ ላይ ላምባ አርከፍክፎ እንዲቃጠል አድርጎታል። ይሄ ብዙ ዜጎችን አሳዝኗል።አስለቅሷል።
አዎን በአገራችን ላይ እግዜርን የማያውቁ ክፉ ኃጥዓን ቡድኖች ተነስተል። የእነዚህ ቡድኖች ድርጊትም ህዝብን ከዳር እስከዳር እያስለቀሰ ነው። ክፉ ድርጊታቸውም ድንበር ተሻግሮ የሩቅ ሰዎችን ጭምር እያሳዘነ ነው።
የአንድ አገር ህዝቦች ባንድነት እንዳይቆሙ ተፋቅረውና ተሳስበው እንዳይኖሩ ሆን ብሎ የሚለያዩበትን መንገድ መፍጠር ኃጢዓት ነው። ወንድምን በሃሰት አስመስክሮ በሃሰት አስፈርዶ ስቃያቸውን ማብዛት ኃጢዓት ነው። በኃይማኖት ድርጅቶች መካከል ጠብና ክርክር ተፈጥሮ ደም እንዲፈስ ማድረግ ኃጢዓት ነው። ይህን የመሰሉ ኃጢአቶች በህወት ሲፈጸሙ ከርመዋል። አሁንም እየተፈጸሙ ነው።መለስና ይህ ክፉ ዘረኛ ቡድኑ ስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ እንዲህ ያሉ ኃጢአቶች በአገራችን ላይ ሲፈጸሙ ይኖራሉ።
በዓለማችን ላይ ህዝብ የህዝብ ጠላት የሆነበት ግዜ ታይቶ አይታወቅም። መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ ግን አማራ የትግራይ ህዝብ ዋነኛ ጠላት ነው ብለው ጽፈው ለትውልዱ አስቀምጠውለታል። ይህንንም እንዲመስክርላቸው ሃውልት አስቀርጸው አቁመዋል። ኦሮሞ አማራን ሊበቀል የተዘጋጀ እንደሆነ አድርገው ሲሰብኩ ሁለት አስርተ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ይህም እውነት እንደሆነ ለማስመለስ በክፉም በደጉም አብረው በኖሩ አማሮችና ኦሮሞዎች መካከል ብጥብጥ ፈጥረው የብዙ ንጹሃን ደም እንዲፈስ አድርገዋል። እንዲህ በየቦታው አብሮ በኖረ ህዝብ መካከል ጥላቻን እየሰበኩ የዜጎች ደም በከንቱ እንዲፈስ ማድረግ ኃጢዓት ነው።መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ ግብራቸው ኃጢዓት ሁኖ አብሮአቸው የከረመ ስለሆነ ክፉ ምግባራቸውን እንደ ጽድቅ እየቆጠሩት በደስታ ሰክረው ይኖራሉ። አገሪቷ እንዲህ ባሉ ቡድኖች በተያዘች ወቅት በእነመለስ ዜናዊ መንገድ አለመሄድ ብጹእነት ነው።
ሌላው ህዝብን የሚያቀያይሙበትና ደም የሚያፋስሱበት መንገድ ኃይማኖት ነው።ሙስሊምና ክርስትያን አብሮ ተፋቅሮና ተከባብሮ የሚኖርባት ጥሩ አገር ኢትዮጵያ ነበረች። መለስና ዘረኛ ቡድኑ ስልጣነ መንበሩን ከተቆናጠጡ በኋላ በሁለቱ ታላላቅ ኃይማኖቶች መካከል ጠብ ተፈጥሮ ብዙ ደም ፈሷል። ህወሃት በፈጠረው መሰሪ ተንኮል ምክንያት በሃይማኖት ምክንያት ግጭት ተፈጥሮ በጎንደር፤ በወሎ፤ በአዲስ አበባ፤ በጂማና በመሳሰሉት ቦታዎች የብዙ ንጹሃን ደም ፈሷል። መለስ ዜናዊ ግን ራሱ በፈጠረው ግጭት የሚገለውን ገድሎ የሚያስረውን አስሮ ዜጎችን አስለቅሶ ወንበሩን እንደያዘ ቀጥሏል። እንዲህ በወንድማማቾች መካከል ጠብንና ክርክርን መዝራት ክፉ ኃጢዓት ነው። እግዚአብሄር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ ሰባተኛውን ግን ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች። እርሷም በወንድማማች መካከል ጠብን የሚዘራውን ነው።ምሳሌ 6 ቁጥር 19.
በገዛ አገራችን ውስጥ ወንድም ወንድሙን በሃሰት እንዲከስ፤ አንዱ በአንዱ ላይ በሃሰት እንዲመሰክር ሲደረገ የአንድ ትውልድ ዘመን ተቆጠረ።” ነገራችሁ እውነት ከሆነ እውነት ሃሰት ከሆነ ደግሞ ሃሰት ይሁን” የተባለው የታላቁ መጽሃፍ ቃል ክብር እንዳይኖረው ሁኗል። ፍትህን እንዲያስጠብቁ የተሾሙ አቃቤ ህግያን ሆን ብለው ዜጎችን በሃሰት ከሰው በሃሰት አስመስክረው የሞት ፍርድ ሲያስፈርዱ የፍትሁን ሥርዓት በኩኔኔ እየተኩት መሆኑን እንዳይገነዘቡ እዝነ ልቦናቸው በዘረኝነትና በሴሰኝነት በሽታ ደንዝዟል። እንዲህ የፍትሁን ሥርዓት ማዋረድ ለአገራችንም ለትውልዱም አይበጅም ያሉ እውነተኞችና በጽድቅ እንቁም ያሉ የሚዋረዱበት ሃሰተኞችና በክፉ ሥራዎቻቸው የበረቱ የሚሾሙባት የሰው ዘር ምድረ በዳ እንድትሆን እየተደረገች ነው።
መለስና ግብረ አበሮቹ አገራችንን አዋርዶ፤ ድንበሯን አፍርሶ፤ ምድሪቱንም ሸንሽኖ ለባእዳን አሳልፎ ሰጥቶ፤ ፍቅራችንንም አጥፍቶ ዘመኑን ሁሉ ለመኖር ምኞት አለው። እንዲህ ያልተመኘ ክፉ አምባገነን የለም።ጋዳፊ እሰከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለመረዳት አእምሮው ደንዝዞ ነበር። ሆሲኒ ሙባረክም እንዲሁ ብዙ ዘመን አእምሮው ማስተዋል ተስኖት ነበር።መለስ ዜናዊ ከእነዚህ አምባገነኖች ለመማር እምቢ ብሎ የንጹሃንን ደም እንዲሁ በከንቱ እያፈሰሰና ክፉ ሃሳብን እያፈለቀ አገራችንን ልንወጣ ወደምንቸገርበት አዘቅት ውስጥ እየነዳት ነው።
ማንም ኩነኔን የሚጸየፍና ጽድቅን የሚፈልግ መለስ ዜናዊንና ግበረ አበሮቹን በሚችለው ሁሉ መዋጋት አለበት። ግንቦት ሰባትም አገራችን የእውነትና የጽድቅ አውድማ እንድትሆን መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ ለፍርድ እስከሚቀርቡ ድረስ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። እነዚህ ኃጥአኖችንም ለመገለበጥ ቆርጦ እየሰራ ነው።
ድል ለኢትዮጵያችን ይሁን !!!!