“ሽብርተኛ”፣ “በአኬልዳምኛ” – ለእኩልነት የሚታገል አርበኛ!

በደል በዛ!!! ፍትህ በሌለበት አገር መኖር አልችልም!!! በዚህ ሁኔታ መኖር ኑሮ አይባልም!!! ግፍና መከራ እያየሁ መኖር አልችልም!!! እኔ ለእናንተ አርዓያ ለመሆን እሞታለሁ!!! እናንተ ታግላችሁ ነፃ ውጡ!!!

እነዚህ ነበሩ በመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ተማሮ በራሱ ላይ እሳት የለኮሰው የመምህር የኔሰው ገብሬ የመጨረሻ ቃላት። እነዚህ ቃላት በአዕምሮዎቻችን ውስጥ እየጮሁ እረፍት ነስተውናል። እውነትም ግፍና መከራን እየተቀበሉና እያዩ እንዴት መኖር ይቻላል?

የእርምጃው ግዝፈትና የመልዕክቱ ክብደት ነው የየኔሰውን ዜና እረፍት በመላው ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያም ውጭ ከመቅጽበት እንዲሠራጭ ያደረገው። መምህር የኔሰው ገብሬ ራሱን በእሳት ማቃጠሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ የደረሰበት የምሬት ደረጃ ገላጭ ነው።  የመለስ ዜናዊ አሽከሮች መምህሩን የአዕምሮ ሕመምተኛ ለማስመሰል መሞከራቸው ዜናውን አባባሰው፤ የመለስ ዜናዊን አረመኔነት አጎላው።

ከመምህር የኔሰው በኋላም እዚያው ዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ ውስጥ አንድ ሌላ እጩ መምህር በደረሰበት የአስተዳደር በደል ተማርሮ በትምህርት ቢሮ ግቢ ውስጥ በሚገኝ ዛፍ ላይ ራሱን ሰቅሎ  ለመግደል ሞክሮ የነበረ መሆኑ ተጨማሪ የማስጠንቀቂያ ደወል ነበር።

መምህር የኔሰው ገብሬ ወደ ሁላችንም አዕምሮ የላከውን ይህንን ጠንካራ መልዕክት ለማደብዘዝ ሲሉ ነው የመለስ ዜናዊ ተላላኪዎች “አኬልዳማ” የተሰኘውን ውስጠ-ባዶ ጯሂ ፊልም ያቀነባበሩልን።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለመለስ ዜናዊ ጆሮ ጠቢዎች የማይመች መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ለዚህ ፊልም ምላሽ መስጠት አስፈላጊ አይደለም። መለስ ዜናዊ ንቀት በወጠረው ቁጥር ለሚያሰማቸው የውሸታሙ እረኛ “ቀበሮ  መጣብኝ!!!” ጩኸቶች የኢትዮጵያ ህዝብ  ጆሮ መስጠት ካቆመ ውሎ አድሯል።

ያም ሆኖ ግን “የአኬልማ” አዘጋጆች ባልጠበቋቸው ምክንያቶች የፊልሙ መታየት ጠቀሜታ ያለው ሆኖ ተገኝቷል። እስቲ ከቻሉ ፊልሙን ደግመው በጥሞና ይመልከቱና ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምላሽ ይስጡ።

  • ሽብርተኛ ማነው?
  • ሽብርተኛ እንዴት ያለ  ሰው ነው?

በፊልሙ “ሽብርተኛ” ተብለው የሚጠሩ ሰዎች የታወቁና የተከበሩ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። እነዚህ ዜጎች የሚታወቁት ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለዲሞክራሲ በመቆማቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ፍቅርን እንጂ ጥላቻን ሲሰብኩ አልተሰሙም።

ስለዚህም “አኬልዳማ”

“ሽብርተኛ” ማለት የመለስ ዜናዊን ዘረኛ አገዛዝ በመቃወም ለሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት የሚታገል ኢትዮጵያዊ ማለት ነው።

የሚል ትርጉም ይሰጣችኋል።

“ሽብርተኛ እንዴት ያለ ሰው ነው?” ለሚለው ጥያቄም የፊልሙ ምላሽ

“ሽብርተኛ” ቅን፣ ትሁትና ህሊናው የሚገዛው ሰው ነው።

የሚል ምላሽ ታገኛላችሁ።

ታድያ “በአኬልዳማ” ትርጉም መሠረት ሽብርተኛ መሆን የማይፈልግ ማነው? በአኬልዳማ ትርጓሜ መሠረት ሽብርተኛ መሆን የማይፈልግ ዘረኛ፣ ሆድ-አደር፣ አድርባይ፣ ብልጣ ብልጥ እና ፈሪ ነው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች እና አዛውንቶች፤ ወንዶችና ሴቶች በዘረኞች፣ በሆድ-አደሮች፣ በአድርባዮችና ፣ በብልጣ ብልጦች እና ፈሪዎች የሚደርስባቸውን ወከባ ተቋቁመው በአኬልዳምኛ ሽብርተኛ ሆነው ራሳቸውንና አገራቸውን ነፃ ማውጣታቸው አይቀሬ ነው።

በአኬልዳምኛ “ሽብርተኛ” ማለት አገር ወዳድ፤ ነፃነት ወዳድ፤ ፍትህ  ወዳድ ማለት ነው። በአኬልዳምኛ ሽብርተኛ መሆን ክብር ነው።

ግንቦት 7 : የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በመለስ ዜናዊና ዘረኛ ቡድኑ “ሽብርተኛ” መባል የሕዝባዊነትና የአርበርኝነት ኒሻን እንደሆነ ተረድተን ትግላችንን በበለጠ ጥንካሬና ቁርጠኝነት እንድናፋፍም ጥሪ ያደርጋል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

(ግንቦት 7)