ኩማ ደመቅሳ የአዲስ አበባ አስተዳደር በባለሃብቶች ላይ ዘመቻ ጀመረ
ውድነህ ዘነበ | ሪፖርተር
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁለት ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ ቦታ ወስደው ባላለሙና ከተፈቀደላቸው ዓላማ ውጭ ቦታውን በሚገለገሉ አልሚዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ጀመረ፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ከአስተዳደሩ ጋር በገቡት ውል መሠረት ግንባታ ያላካሄዱ፣ ግንባታ ያካሄዱትም ቢሆኑ ለወሰዱት ዓላማ ቦታውን አላዋሉም በሚል ነው አስተዳደሩ ዕርምጃውን መውሰድ የጀመረው፡፡
ዕርምጃው እየተወሰደ የሚገኘው በክፍለ ከተማ ደረጃ ሲሆን፣ ከፍለ ከተሞቹ በኢንቨስትመንት ኤጀንሲው የተካሄደን ጥናት መሠረት አድርገው ከወር በፊት ምንም ዓይነት ግንባታ በአካባቢው እንዳይካሄድ ለአልሚዎቹ በደብዳቤ ገልጸው ነበር፡፡ ከዚህ በመቀጠል ባለፈው ሳምንት ሁለቱ ክፍለ ከተሞች ግንባታ ሳይካሄድባቸው ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችንና ለሌላ ዓላማ ግንባታ የተካሄደባቸውን ቦታዎች ግንባታቸውን በማፍረስ መሬቱን ወደ መሬት ባንክ ማስገባት መጀመራቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ክፍለ ከተሞቹ አቃቂ ቃሊቲና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ሲሆኑ፣ በቃሊቲ የኢንዱስትሪ ዞን 166 አልሚዎች ቦታ ወስደዋል፡፡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በለቡ የኢንዱስትሪ ዞን ደግሞ 168 አልሚዎች ቦታ ወስደዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ዞኖቹ በከተማው አስተዳደር ለኢንዱስትሪ የተዘጋጁ የመጀመሪያዎቹና ብቸኞቹ ዞኖች ሲሆኑ፣ የተዘጋጁትም በቀድሞው የከተማው ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን ነው፡፡
በ1996 ዓ.ም. ከተዘጋጁት ከእነዚህ የኢንዱስትሪ ዞኖች ውጭ በእስካሁኑ ቆይታ አዲስ የኢንዱስትሪ ዞን የመሠረት ልማት ተሟልቶለት ለአልሚዎች ክፍት አልሆነም፡፡
የአቶ ኩማ አስተዳደር 1600 ሔክታር መሬት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ለኢንዱስትሪ ለማዘጋጀት ዕቅድ መንደፉን፣ አቶ ኸይሩ ኑሩ የከተማው ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች የሥራ ሒደት መሪ ከአንድ ሳምንት በፊት ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡
በከተማው አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ አስተባባሪነት በሁለቱ ዞኖች ውስጥ ቦታ ካገኙት የኢንዱስትሪ አልሚዎች መካከል ወደ ሥራ የገቡት እጅግ ጥቂቶች መሆናቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የኤጀንሲው ጥናት እንደሚያመለክተው በአቃቂ የኢንዱስትሪ ዞን ቦታ ከወሰዱት 166 አልሚዎች ውስጥ ማምረት የጀመሩት 45 ብቻ ናቸው፡፡ ቦታውን አጥረው ያስቀመጡ 18 ኩባንያዎች ሲሆኑ ከተፈቀደላቸው ዓላማ ውጭ ግንባታ አካሂደው የሚጠቀሙ 15 ኩባንያዎች ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ 14 ኩባንያዎች የሊዝ መብታቸውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈዋል ተብለው የተመዘገቡ ሲሆን፣ አራት ኩባንያዎች ደግሞ ቦታውን ማከራያታቸውንና የተቀሩት ግንባታ ቢጀምሩም በእስካሁኑ ቆይታ ግንባታቸው እንዳልተጠናቀቀ መረጃው ይጠቁማል፡፡
የኤጀንሲው መረጃ አንደሚያመለክተው በአቃቂ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ቦታ ወስደው ግንባታ ካላካሄዱ አልሚዎች መካከል ሚስስነት ሞላ ቡና ለመፍጨት ቦታ ቢወስዱም በወሰዱት ቦታ ላይ ግን ግንባታ አላካሄዱም በሚል ተመዝግበዋል፡፡ አረጋሽ ገበየሁ የተባሉ ባለሀብት እንዲሁ ልብስ ስፌት ፋብሪካ ለመገንባት የወሰዱትን ቦታ ለሦስተኛ ወገን አሳልፈዋል ተብሏል፡፡ አካካስ ሎጀስቲክ ካርቶን ለማምረቻ በወሰደው ቦታ ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ እስካሁን አላካሄደም ተብሏል፡፡ ሁሴን ወልዴ ለልብስ ስፌት ፋብሪካ ግንባታ በወሰደው ቦታ ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ አላካሄደም፡፡ ዘኪ አህመድ ለዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ በወሰደው ቦታ ላይ እስካሁን ግንባታ አላካሄደም በሚል ስማቸው ከሰፈሩት መካከል ይገኙበታል፡፡
በለቡ ኢንዱስትሪ ዞንም እንዲሁ ቦታ ከወሰዱ 168 አልሚዎች መካከል 61 አልሚዎች ብቻ ማምረት የጀመሩ ሲሆን፣ 20 አልሚዎች ከተፈቀደላቸው ውጭ መጋዘን ገንብተዋል፡፡ 14 አልሚዎች በሌላ ተግባር ቦታውን አከራይተውታል፡፡ ሦስት ኩባንያዎችም ቦታውን አጥረው መቀመጣቸውን ጥናቱ ያመለክታል፡፡
ከእነዚህ መካከል ኤ ዜድ ኩባንያ ለብረት ውጤቶች ማምረቻ የወሰደውን ቦታ አከራይቷል፡፡ ስላስት ኩባንያ የወሰደውን ቦታ ለከባድ ተሽከርካሪ መኪና ማቆሚያ አከራይቶታል፡፡ በቀለ ተሰማ ለእንጨት ውጤቶች ቦታውን ቢወስድም መጋዘን ገንብቶበታል፡፡ ጤናለም ትሬዲንግ ለወረቀትና ካርቶን ማምረቻ የወሰደውን ቦታ የስቴሽነሪ መጋዘን ገንብቶበታል፡፡ ኦርጋኒክ ሥጋ ላኪ ሥጋ ለማቀነባበር በወሰደው ቦታ ላይ ግንባታ አላካሄደም በማለት ኤጀንሲው በጥቁር መዝገብ ላይ ካሰፈራቸው ኩባንያዎች መካከል ይገኙበታል፡፡
በዚህ የሥራ አፈጻጸም ደካማነት ያልተደሰተው የከተማው አስተዳደር ዕርምጃ ወደ መውሰድ የገባ ሲሆን፣ ባለሀብቶቹ ግን ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ ለልማት ወስደው ባዶውን ባስቀመጡት መሬት ምክንያት ዕርምጃ ሲወስድባቸው ዕርምጃውን በፀጋ አልተቀበሉትም፡፡
በጥናቱ እንደተመለከተውና ሪፖርተር ያነጋገራቸው አልሚዎች እንደሚገልጹት፣ ግንባታ ያላካሄዱበት ምክንያት በግንባታ ዕቃዎች የዋጋ ንረት፣ በብድር አቅርቦት ማነስ፣ በውጭ ምንዛሪ ችግር፣ በተሰጣቸው ቦታ አነስተኛ በመሆኑ ከሥራቸው ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ፣ የመንገድና የፍሳሽ ማስወገጃ አለመኖርንና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ያለመሆን እንደችግር ይጠቅሳሉ፡፡
ይሁንና አስተዳደሩን እነዚህ ምክንያቶች ያላሳመኑት በመሆኑ ወደ ዕርምጃው መግባቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡