አዲስ አበባ መስተዳደር በቢፒአር አስጠንቶ ተግባራዊ አድርጋለሁ ያለውን መርኀ ግብር አጠፈ

(ሙሉ ገ)

በአቶ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው የአዲስ አበባ መስተዳድር በ2003 ዓ.ም የበጀት ዓመት የዲግሪ ምሩቃንን በመቅጠር በዐሥሩም ክፍለ ከተሞች ልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች ላይ በመመደብ እና በቦታው ላይ ብቃት ጎደላቸው ባላቸው ሠራተኞች ምትክ ብቁ የኾነ የአሠራር ለውጥ ለማምጣት በቢፒአር አስጠንቶ ተግባራዊ አድርጋለሁ ያለውን መርኀ ግብር አጠፈ።

አርብ ሕዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም ከመስተዳድሩ ለዐሥሩም ክፍለ ከተሞች የወረደው መመርያ እንደሚያሳስበው ክፍለ ከተሞች በበጀት ዓመቱ በቋሚ ቅጥር ሂደት ላይ የያዟቸውን ምሩቃን ሁሉ ውል እንዲያቋርጡ በማዘዝ፣ ቀድሞ በነበረው የሰው ሐይል ሥራው በአግባቡ እንዲቀጥል አሳስቧል። በአጠቃላይም ከ1500 በላይ የሚኾኑ ጊዜያዊ  ሠራተኞች ውላቸው ተቋርጦ  ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የስንብት ደብዳቤ እንዲደርሳቸው የኩማ አስተዳደር ውሳኔ አስተላልፏል።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በአስተዳደር ሥራ ላይ የተሰማሩ የዜና ምንጫችን ለአዲስ ነገር ሪፖርተር እንደገለጹት በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለውን የደመወዝ ጭማሪ በማስላት በጀት ለመቀነስ ሲባል ብቻ የተወሰነው ውሳኔ ወጥነት የጎደለው እና በመስተዳድሩ ውስጥ ሥራን ለሞያተኛ ብቻ በመስጠት ቀልጣፋ የኾነ አገልግሎት ለማምጣት የሚያስችለውን በጎ ጅምር የሚያጨናግፍ ብለውታል።

ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ለሞያተኞች ከፍ ያለ ግምት መስጠት የጀመረ መስሎ ነበር የሚሉት እኚኹ የአዲስ ነገር ምንጭ መሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ (ቢፒአር) ተካሂዶ በተጠናው ጥናት መሠረት ለልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች የሚያስፈልጉንን የሞያተኛ ዐይነት እና ብዛት እንዲሁም የቢሮ ቁሳቁሶች ዝርዝር አሳውቀን ነበር ብለዋል።

በዚሁ መሠረት በተያዘው የበጀት ዓመት አዲስ የቢሮ አደረጃጀት ያካሄድን ሲኾን መስተዳድሩም ለሥራ የሚያስፈልጉትን ኮምፒዩተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ ስካነሮች፣ የፎቶ ኮፒ ማሽኖች እና የቢሮ ጠረጴዛዎችን አሟልቶ ስለነበር ቅጥር አካሂደን አብዛኞቹ ሠራተኞች በሥራ ላይ እንዲሠማሩ ተደርጓል። ቀሪዎቹን ደግሞ በቅርቡ ሥራ እንዲጀምሩ የሚል ዕቅድ አውጥተን በመጠባበቅ ላይ ነበርን። ሥራ ሳይጀምሩ ስድስት ወር የኾናቸውን ተጠባባቂ ለሥራ የተዘጋጁ ሞያተኞች ከወዲሁ እንድናሰናብታቸው እና ውል እንድናቋርጥ ከመስተዳድሩ ትዕዛዝ ደርሶናል ሲሉ ገልጸዋል።