አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ወያኔ ህዝብን ለማስፈራራት ሲል በ3 ተከታታይ የቴለቪዥን ዝግጅት ያሰራጨውን የፈጠራ ድራማ በጽኑ የሚኮንን መግለጫ አወጣ

አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ህዳር 20 ቀን 2004 ዓም በ “አኬልዳማ ” ድራማ የህዝብን የዲሞክራሲና የለውጥ ጥያቄ ማዳፈን አይቻልም” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ፤ “ደርግን የተካው ኢህአዴግ ትምህርት ወስዶ የተሻለ ስርዓት ይገነባል ተብሎ ቢጠበቅም፣ እሱም በተራው የለየለት አምባገነንና አፋኝ ስርዓት ለመሆን ብቅቶአል። በዚህም ምክንያት ጭቆና እንዲወገድ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሠረት በሚድረግ ጥረት ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ለሀገራቸው ልማትና ብልፅግና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ከመስራት ይልቅ ጥላቻና አምባገነንነት የአገዛዙ የአመራር ዘይቤ ሆኖአል” ብሎአል።

ደርግ ህወሓትን “ወንበዴ”፣ “ፀረ-ሰላም” እና “አስገንጣይ” የሚል ስም ሰጥቶት እንደነበር ይታወቃል” ያለው የአንድነት መግለጫ፤ ህወሓት/ኢህአዴግም በተራው ተቀናቃኞቹን “ፀረ-ሰላም”፣“ፀረ-ልማት” እና “አሸባሪ” ለማለት ወግ ደርሶታል ካለ ቦኋላ “አገዛዙ ትላንት ካሳለፈው የትግል ልምድ ሊማር ያለመቻሉን በግልፅ እንረዳለን፤ የሕዝብን ጥያቄ በሰላይ ጋጋታና በወታደር ብዛት ማዘግየት እንጂ መጨፍለቅ እንደማይቻል ከኢህአዴግ በላይ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ድርጅት ሊኖር ባልቻለ ነበር ሲል የመለስ ዜናዊ በጠመንጃ ጋጋታ የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም መዳከር ከንቱ እንደሆነ አስገንዝቦአል።

ወያኔ በዜጎች ላይ እየወሰደ ባለው አፈናና በህጋዊነት ተመዝግበው በመንቀሳቀስ ላይ ባሉት የፓርቲው አመራርና ተራ አባላት ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ያስቆጣው የአንድነት ፓርቲ ፤ “አገዛዙ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቃዋሚ አባለትና ጋዜጠኞች ላይ ሰፊ የእስርና የአፈና እርምጃ አጧጥፎ ቀጥሎበታል፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትንና የነፃው ሚድያ አባላትን ወደ እስር ቤት መወርወርና ማዋከብ የአገዛዙ የቀን ተቀን ስራ ሆኖአል በማለት ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ብዛት ያላቸው ጋዜጦኞች ለእስርና ለስደት እንደተዳረጉ፤ በዚህም የተነሳ በቅርቡ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጅግ ኤዲተር ዳዊት ከበደ ከሀገር ለመሰደድ እንደቻለ ገልጾአል፡፡

በጸረ ሽብርተኛ ህግ ተብዬው አዋጅ ህዝብን የፍርሃት ድባብ ውስጥ ለመክተት መለስ ዜናዊ፤ በረከት ስምዖንና ሽመልስ ከማል እየሰሩት ያለው ድራማ ከንቱነትን አስመልክቶ፤ “አገዛዙ በአሸባሪነት ስም እየወሰደ ያለው ቅጥ ያጣና ነውረኛ ርምጃ በዜጎች ዓይን ተቀባይና አሳማኝ ሊሆን እንዳልቻለ ተረድቷል ያለው የአንድነት መግለጫ ፤ “አገዛዙ ከህዝብ ያጣውን ተቃባይነትና አመኔታ ያገኘ መስሎት ርካሽ የሆነ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሕዝብን ለማሳመን አቅዶ ተነስቷል ብሎአል።

“የሕዝብን ጥያቄ በሰላይ ጋጋታና በወታደር ብዛት ማዘግየት እንጂ መጨፍለቅ እንደማይቻል ከኢህአዴግ በላይ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ድርጅት ሊኖር አይችልም፡” የሚለው አንድነት፣ በቅርቡ “አኬልዳማ” በሚል ርዕስ የቀረበው በጥላቻና በሽብር የተሞላ መርዘኛ የሆነ ፕሮፓጋንዳ በአንድ በኩል ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በፓርላማ ተገኝቶ በቂ ማሰረጃ ይዘን ነው ያሰርነው ላላውና ይህንንም ተከትሎ በተለያየ ሁኔታ ለሚደርሰው ነቀፌታና ተፅዕኖ ድጋፍ ለመሰጠት፤ በሌላ መልኩ ደግሞ በኑሮ ውድነትና በመልካም አሰተዳደር ዕጦት የተማረረ ህዝብ በሰሜን አፈሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ህዝባዊ እንቅሰቃሴ ፈለግ ይከተላል በሚል ፍርሃት ቀድሞ ለማሰፈራራትና ወዮልህ ለማለት፤አልሞ የተነሣ ነው፡ “ሲል ገልጣል።

አንድነት አያይዞም የኢ.ቲ.ቪ. የሶስት ቀናት ፕሮፓጋንዳ እርስ በርስ የሚቃረን፣ በጥላቻ የታጨቀና ግልፅ የስም ማጥፋት ወንጀል የተፈፀመበት፣ የአንድነት ፓርቲ አባላት ያልሆኑ ግለሰቦች እንደ ፓርቲው አባላት አድርጎ ያቀረበ ነው ሲል ኮንኖታል።

በመቀጠልም “ከዚህ ቀደም ብዛት ያላቸው የኢህአዴግ አባላትና አመራሮች ወደ ኦነግ ከመግባታቸው በተጨማሪ የደንህነትና የመከላከያ አባለት የነበሩ ዜጎች በገፍ ወደ ኦነግና ግንቦት 7 የገቡበት ሁኔታ እንዳለ የአደባባይ ምስጥር ነው ያለው የአንድነት መግለጫ በኢ.ቲ.ቪ. እይታና አመክንዮ ከተሄደ ኢህአዴግም ሆነ መከላከያ ሰራዊቱ አሸባሪዎች ናቸው ማለት ነው” በማለት የአንድነት ፓርቲ አባላት በሚተዳደሩበት ግልፅ ህገ-ደንብ መሠረት አንድ የአንድነት ፓርቲ አባል የሆነ ሰው የሌላ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችል አስታውቆአል፡፡

ወያኔ በአንድነት ፓርቲ ላይ እያካሄደ ያለው የሥም ማጥፋት ዘመቻ ያንገሸገሸው አንድነት፤ “ፓርቲያችንን በአሸባሪነት ስም ጥላሸት እየቀቡ ከሕዝብ ለመነጠል የሚደረግ እኩይ ተግባር ሊቆም ይገባል ” በማለት ያስጠነቅቅና፤ አገዛዙ በእንዲህ ዓይነቱ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ከሕዝብ የማገኘው ጥቅም አለ ብሎ ካሰበ ተሳስቷል ፤ የኢ.ቲ.ቪ. እንዲህ ዓይነት በጥላቻ የታጨቀ አሰነዋሪና የወረደ ዘገባ ማስተላለፉም ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት፣ የስነ ምግባርና የሞራል ውድቀት ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው “ብሎአል። አያይዞም ህወሓት በረሃ በነበረበት ዘመን ባንክ ይዘርፍ እንደነበር በየአደባባዩ በኩራት እንደሚናገር እየታወቀ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሌሎችን በዚህ መክሰሱ ጉዳዩን አስቂኝ አድርጎታል ብሎአል።

“አኬልዳማ” የተባለው የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ በቴሌቨዥን ፍርድ የተሰጠበት ተግባር መሆኑን የሚያስታውሰው አንድነት ፣ አገዛዙ በህግ ሳይሆን በራሱ ሚዛን አሻባሪ ብሎ ዜጎችን የሚፈርጅ ከሆነ፣ የፍርድ ቤት አስፈላጊነት ምኑ ላይ ነው? የፍርድ ቤት ነፃነትስ ከየት ይመጣል? ሲል ይጠይቃል።

የኢህአዴግ አሰኳል የሆነው ህወሓት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በኤርትራ ጉዳይ ላይ እያራመደው ያለው አቋም ሀገራችንን ትልቅ ዋጋ ማስከፈሉን፣ ሀገራችንን ወደብ አልባ እንድትሆን ያደረገው፣ ስልጣንን እንጂ የሀገርን ጥቅም ማዕከል አድርጎ ያለመሄድ በሽታ መሆኑን ያወሳው ፓርቲው፣ ኢህአዴግ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት በቁርጠኝነት የሚታገለውን አንድነት ፓርቲን ከሻቢያና ከሸብርተኝነት ጋራ ለማገናኘት መሞከር ታላቅ ሰህተት ከመሆንም አልፎ ይህን ክስ ለመሰንዘር የሞራል ብቃት የለውም፡፡ ሲል አጣጥሎታል።

አገዛዙ የሕዝብን የለውጥ ፍላጎት በስለላና በጦር ኃይል እጨፈልቃለሁ የሚል አምባገነናዊ አካሄድ የቁልቁል ጉዞ እንደሚወስደው የሚጠቅሰው አንድነት ፓርቲ ፣ የኢህአዴግ አባላትም አመራሩ እየተንደረደረ እየሄደበት ካለው የመቀመቅ ጉዞ፣ ሀገርንም ፓርቲውንም አይጠቅምምና ተመለስ ሊሉት ይገባል ሲል ምክሩን ለግሷል።

በመጨረሻም ፓርቲው “የአገዛዙ ሟርተኛ ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን የሚያሸብርና ወደ ደም መቃባት የሚወሰድ የእልህ ጉዞ መሆኑን ጠቅሶ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገራችን ካለችበት የፖለቲካ አዙሪት አንድትወጣ ከፍርሃት ራሳችንን አውጥተን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለዴሞክራሲና ለህግ የበላይነት የሚደረገውን ትግል እናግዝ ሲል ጥሪ አቅርቦአል።