የስዊድን ጋዜጠኖች በመለስ ዜናዊ አገዛዝ የተቀነባበረባቸውን የሽብርተኝነት ክስ ፈጠራ ነው ማለታቸው ተዘገበ

ጋዜጠኞቹ ያለፈው ማክሰኛ ህዳር 26 በዋለው የወያኔ ችሎት እንደገለጡት፣ ወደ ኦጋዴን ክልል የገቡት የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅትን ለመርዳት ሳይሆን በአካባቢው በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማራው ሉንዲን ኦይል የተባለውን የስዊዲሽ የነዳጅ ኩባንያ በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚከሰሰውን የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት አባላት በዘበኝነት መቅጠሩን ለማረጋገጥ ነው።

ጋዜጠኛ ማርቲን ሺቢዬና ጆሀን ፔርሰን እንዳሉት ከኦብነግ ጋር የነበራቸው ግንኙነት የጋዜጠኝነት ስነምግባርን በተከተለ መልኩ የተከናወነ ነው። ጋዜጠኞቹ ወታደራዊ ስልጠና አግኝተዋል በሚል የወያኔ አቃቢ ህግ ያቀረበውን ክስም ውድቅ አድረገውታል።

የወያኔ አቃቢ ህግ ያቀረበውና ማርቲን ሺቢዬ የጦር መሳሪያ ይዞ የሚታየው ፎቶ ግራፍ የተቀረጸው በአንድ ሆቴል ውስጥ ከአንድ የአልሸባብ ወታደርን ቃለ ምልልስ እያደረገ በነበረበት ጊዜ መሆኑን፣ ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል። የጋዜጠኞቹ ጠበቆች እንደሚሉት ሁለቱ ጋዜጠኞች ከዚህ ቀደም አስቸጋሪ በሆኑ የጦርነት ቦታዎች ሳይቀር በመጓዝ ዘገባዎች ያቀረቡ ናቸው። ከ800 በላይ በአለም ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ለሁለቱ ጋዜጠኞች ምስክር ለመሆን ፍላጎት ማሳየታቸውን በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ተናግረዋል።

የዘረኛው መለስ አገዛዝ ጋዜጠኞቹን ያሳጣ መስሎትና እነርሱን መያዣ በማድረግ ከምርጫ 97 ወዲህ ከስዊዲን መንግሥት ጋር የገባበትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማደሻ በደመነፍስ በወሰደው እርምጃ በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው አፈናና ግዲያ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት እንዲያገኝ አስደርጎአል።